ዘሌዋውያን 7:11-38

ዘሌዋውያን 7:11-38 NASV

“ ‘አንድ ሰው ለእግዚአብሔር የኅብረት መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ፣ ሊከተለው የሚገባው ሥርዐት ይህ ነው፤ “ ‘መሥዋዕቱን የሚያቀርበው ለምስጋና መግለጫ ከሆነ፣ ከምስጋና መሥዋዕቱ ጋራ ያለ እርሾ የተጋገረና በዘይት የተለወሰ ኅብስት እርሾ ሳይገባበት፣ በሥሡ ተጋግሮ፣ ዘይት የተቀባ ቂጣ በሚገባ ታሽቶ፣ በዘይት የተለወሰም የላመ ዱቄት ኅብስት ዐብሮ ያቅርብ። ለምስጋና ከሚሆነው የኅብረት መሥዋዕት ጋራ፣ በእርሾ የተጋገረ ኅብስት ያቅርብ። ከእያንዳንዱም ዐይነት አንዳንድ አንሥቶ ለእግዚአብሔር የተለየ ቍርባን በማድረግ ያቅርብ፤ ይህም የኅብረት መሥዋዕቱን ደም ለሚረጨው ካህን ይሰጥ። ለምስጋና የሚሆነው የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ፣ በቀረበበት ዕለት ይበላ እንጂ አንዳች አይደር። “ ‘መሥዋዕቱ ስእለት በመፈጸሙ ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ከሆነ፣ በቀረበበት ዕለት ይበላ፤ የተረፈውም ሁሉ በማግስቱም ይበላ። እስከ ሦስት ቀን የቈየ ማንኛውም የመሥዋዕቱ ሥጋ ይቃጠል። ማንኛውም የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ በሦስተኛው ቀን ከተበላ ተቀባይነት የለውም፤ ርኩስ በመሆኑ ላቀረበው ሰው ዋጋ አይኖረውም፤ ከዚያም የበላ ሰው የበደል ዕዳ ይሆንበታል። “ ‘ርኩስ ከሆነ ነገር ጋራ የተነካካ ሥጋ ይቃጠል እንጂ አይበላ። ሌላውን ሥጋ ግን በሥርዐቱ መሠረት ንጹሕ የሆነ ማንኛውም ሰው ይብላ፤ ነገር ግን ንጹሕ ያልሆነ ማንኛውም ሰው ለእግዚአብሔር የቀረበውን የትኛውንም የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፣ ከሕዝቡ ፈጽሞ ይወገድ። ማንኛውም ሰው የሰውን ርኩሰት ወይም ርኩስ እንስሳን ወይም ማንኛውንም ርኩስ ነገር ቢነካና ለእግዚአብሔር ከቀረበው የኅብረት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ፣ ያ ሰው ፈጽሞ ከሕዝቡ ይወገድ።’ ” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘የበሬ ወይም የላም፣ የበግ ወይም የፍየል ሥብ አትብሉ። ሞቶ የተገኘ ወይም አውሬ የገደለው ከብት ሥብ ለሌላ ተግባር ይዋል እንጂ አይበላ። ለእግዚአብሔር በእሳት ከሚቀርብ እንስሳ ሥብ የሚበላ ማንኛውም ሰው ከሕዝቡ ይወገድ። በየትኛውም ቦታ ብትኖሩ የማንኛውንም የወፍ ዘር ወይም የእንስሳ ደም አትብሉ። ማንኛውም ሰው ደም ቢበላ፣ ያ ሰው ከሕዝቡ ይወገድ።’ ” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘የኅብረት መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የሚያቀርብ ማንኛውም ሰው ስለ ራሱ መሥዋዕት አድርጎ ከዚሁ ላይ ለእግዚአብሔር ያቅርብ። በእሳት ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕት በራሱ እጅ ያቅርበው፤ ሥቡን ከፍርምባው ጋራ ያቅርብ፤ ፍርምባውን መሥዋዕት አድርጎ በእግዚአብሔር ፊት ይወዝውዘው። ካህኑ ሥቡን በመሠዊያው ላይ ያቃጥል፤ ፍርምባው ግን ለአሮንና ለልጆቹ ይሰጥ። የኅብረት መሥዋዕታችሁን የቀኝ ወርች ለካህኑ የተለየ አድርጋችሁ ስጡት። የኅብረት መሥዋዕቱን ደምና ሥብ የሚያቀርበው የአሮን ልጅ ቀኝ ወርቹን የራሱ ድርሻ አድርጎ ይውሰድ። ከእስራኤላውያን የኅብረት መሥዋዕት ላይ የተወዘወዘውን ፍርምባና የቀረበውን ወርች ወስጃለሁ፤ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹም ከእስራኤላውያን የሚያገኙት መደበኛ ድርሻቸው እንዲሆን ሰጥቻቸዋለሁ።’ ” ካህናት ሆነው እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ በቀረቡ ቀን፣ በእሳት ለእግዚአብሔር ከቀረበው መሥዋዕት ላይ ለአሮንና ለልጆቹ የተመደበላቸው ድርሻ ይህ ነው። ካህናቱ በተቀቡበት ቀን፣ እስራኤላውያን መደበኛ ድርሻ አድርገው ከትውልድ እስከ ትውልድ ይህን እንዲሰጧቸው እግዚአብሔር አዘዘ። እንግዲህ የሚቃጠል መሥዋዕት፣ የእህል ቍርባን፣ የኀጢአት መሥዋዕት፣ የበደል መሥዋዕት፣ የክህነት ሹመት መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት ሥርዐት ይህ ነው፤ ይህም፣ በሲና ምድረ በዳ እስራኤላውያን መሥዋዕታቸውን ለእግዚአብሔር እንዲያቀርቡ ባዘዛቸው ቀን በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ የሰጠው ሥርዐት ነው።