ኦሪት ዘሌዋውያን 7:11-38

ኦሪት ዘሌዋውያን 7:11-38 አማ05

“ለእግዚአብሔር ስለሚቀርበው የአንድነት መሥዋዕት ሕግ ይህ ነው፤ አንድ ሰው ይህን መባ ለእግዚአብሔር የምስጋና መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ቢፈልግ፥ ከሚሠዋው እንስሳ ጋር እርሾ ያልነካው በዘይት ተለውሶ የተጋገረ ዳቦ፥ እርሾ ያልገባበት በስሱ ተጋግሮ ዘይት የተቀባ ዳቦ፥ በላመ ዱቄት በዘይት ተለውሶ የተጋገረ ዳቦ ያቅርብ። ከአንድነት መሥዋዕት በተጨማሪ ለመባ የሚሆን በእርሾ ተቦክቶ የተጋገረ ኅብስት ያቅርብ። ከእያንዳንዱ የኅብስት ዐይነት አንዱን ክፍል ለእግዚአብሔር የተለየ መባ አድርጎ ያቀርባል፤ ያም መባ የእንስሳውን ደም ወስዶ በመሠዊያው ጐን የኅብረት መሥዋዕት አድርጎ ለረጨው ካህን ድርሻ ይሁን፤ የእንስሳውም ሥጋ በዚያው በተሠዋበት ቀን መበላት አለበት፤ ከዚያ ተርፎ የሚያድር ምንም ነገር አይኑር። “አንድ ሰው የሚያቀርበው የአንድነት መሥዋዕት ስእለት ስለ ተፈጸመለት ወይም የበጎ ፈቃድ ስጦታ ቢሆን ሁሉም በዚያው በቀረበበት ዕለት ይበላ፤ ከዚያም የተረፈ ቢኖር በማግስቱ ይበላ። ከመሥዋዕቱ ተርፎ እስከ ሦስት ቀን የቈየው ሥጋ ግን በእሳት ይቃጠል፤ ከተረፈው ሥጋ ምንም ያኽል በሦስተኛው ቀን ቢበላ የዚያን ሰው መሥዋዕት እግዚአብሔር አይቀበልለትም፤ መሥዋዕቱም እንደ ቀረበ ሆኖ አይቈጠርለትም፤ እንዲያውም እንደ ረከሰ ሆኖ ይቈጠራል፤ እርሱንም የበላ ሰው የበደሉን ፍዳ ይቀበላል። ንጹሕ የሆነውን ሥጋ ማንኛውም የረከሰ ነገር ቢነካው መቃጠል እንጂ መበላት የለበትም፤ “ንጹሕ የሆነ ሰው ይህን ንጹሕ የሆነውን ሥጋ ይብላ፤ ነገር ግን አንድ ሰው ንጹሕ ሳይሆን የአንድነቱን መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ ከእግዚአብሔር ሕዝብ መለየት አለበት፤ ማንም ሰው ንጹሕ ያልሆነው ከሰው ወይም ከእንስሶች የሚወጣ ማንኛውንም ርኩስ ነገር ነክቶ ይህን የአንድነት መሥዋዕት ሥጋ ቢበላ ያ ሰው ከእግዚአብሔር ሕዝብ ይለይ። ” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤላውያን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ የቀንድ ከብት፥ የበግና፥ የፍየልን ስብ የሚበላ አይኑር፤ ሞቶ የተገኘ እንስሳ ወይም አውሬ የገደለው እንስሳ ስቡ ለሌላ አገልግሎት ይዋል እንጂ ማንም ሰው አይብላው። የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ ለእግዚአብሔር የቀረበውን እንስሳ ስብ የሚበላ ሰው ከእግዚአብሔር ሕዝብ ይለይ፤ እንዲሁም እስራኤላውያን የትም ቦታ ቢኖሩ በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ የወፍም ሆነ የእንስሳ ደም አይብሉ፤ ማንኛውንም ደም የሚበላ ሰው ሁሉ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ይለይ።” እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ለእስራኤል ሕዝብ እንዲህ በላቸው፤ ማንም ሰው የአንድነት መሥዋዕት ቢያቀርብ ከእርሱ ከፍሎ ለእግዚአብሔር የተለየ መባ ያምጣ፤ እርሱንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ያቅርብ፤ የእንስሳውንም ስብ ከፍርምባው ጋር በመወዝወዝ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርጎ ያቅርብ። ካህኑ ስቡን በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤ ፍርምባው ግን ለካህናቱ ይሰጥ፤ ከአንድነቱ መሥዋዕት በቀኝ በኩል ያለው ወርች ድርሻው ሆኖ ለካህኑ ይሰጥ፤ የቀኙ ወርች የአንድነቱን መሥዋዕት ደምና ስብ ለሚያቀርበው ካህን ድርሻ ይሁን፤ ከእስራኤላውያን የአንድነት መሥዋዕት መካከል የተወዘወዘውን ፍርንባና የሚቀርበውን ወርች ከእስራኤላውያን እንደሚቀርብላቸው ቋሚ ድርሻ አድርጌ ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጥቻቸዋለሁ። ይህም እግዚአብሔር አሮንንና ልጆቹን ካህናት አድርጎ በሾመበት ቀን ለእግዚአብሔር ከቀረበው ከሚቃጠል መሥዋዕት ለካህናት ድርሻ ሆኖ የተለየ ነው፤ በዚያን ቀን እግዚአብሔር ይህን የመሥዋዕት ክፍል ለካህናቱ እንዲሰጡአቸው የእስራኤልን ሕዝብ አዘዘ፤ ይህም በሚመጡት ዘመናት ሁሉ የካህናቱ ድርሻ እንዲሆን ቋሚ ሥርዓት አደረገው።” እንግዲህ ስለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ስለ እህል መባ፥ ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት፥ ስለ በደል ማስተስረያ መሥዋዕት ስለ ክህነት ሹመት መሥዋዕትና የአንድነት መሥዋዕት የሚፈጸሙትም የሥርዓት መመሪያዎች እነዚሁ ናቸው። በዚያም በረሓ በሆነው በሲና ተራራ እስራኤላውያን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ባዘዛቸው በዚያ ቀን እግዚአብሔር ለሙሴ እነዚህን ትእዛዞች ሰጠው።