ኦሪት ዘሌዋውያን 14:33-57

ኦሪት ዘሌዋውያን 14:33-57 አማ54

እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው፦ ወደምሰጣችሁ ርስት ወደ ከነዓን ምድር በገባችሁ ጊዜ፥ እኔም የለምጽ ደዌ በርስታችሁ ምድር በአንድ ቤት ባደረግሁ ጊዜ፥ ባለቤቱ መጥቶ ካህኑን፦ ደዌ በቤቴ ውስጥ እንዳለ ይመስለኛል ብሎ ይንገረው። ካህኑም በቤቱ ውስጥ ያለው ዕቃ ሁሉ እንዳይረክስ፥ እርሱ ደዌውን ለማየት ወደ ቤት ሳይገባ፥ ቤቱን ባዶ እንዲያደርጉት ያዝዛል፤ በኋላም ካህኑ ቤቱን ለማየት ይገባል። ደዌውንም ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በግንቡ ላይ በአረንጓዴና በቀይ ቢዥጐረጐር፥ መልኩም ወደ ግንቡ ውስጥ ቢጠልቅ፥ ካህኑ ከቤቱ ውስጥ ወደ ቤቱ በር ወጥቶ ሰባት ቀን ቤቱን ይዘጋዋል። ካህኑም በሰባተኛው ቀን ተመልሶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ግንብ ላይ ቢሰፋ፥ ካህኑ ደዌ ያለባቸውን ድንጋዮች እንዲያወጡ፥ ከከተማውም ወደ ውጭ ወደ ረከሰው ስፍራ እንዲጥሉአቸው ያዝዛል። ቤቱንም በውስጡ በዙሪያው ያስፍቀዋል፤ የፋቁትንም የምርጊቱን አፈር ከከተማው ወደ ውጭ ወደ ረከሰ ስፍራ ያፈስሱታል። በእነዚያም ድንጋዮች ስፍራ ሌሌች ድንጋዮች ያገባሉ፤ ሌላም ጭቃ ወስደው ቤቱን ይመርጉታል። ደዌውም ዳግም ቢመለስ፥ ድንጋዮቹም ከወጡ ቤቱም ከተፋቀና ከተመረገ በኋላ በቤቱ ውስጥ ቢሰፋ፥ ካህኑ ገብቶ ያያል፤ እነሆም፥ ደዌው በቤቱ ውስት ቢሰፋ፥ በቤቱ ውስጥ ያለው እየፋገ የሚሄድ ለምጽ ነው፤ ርኩስ ነው። ቤቱንም፥ ድንጋዮቹንም፥ እንጨቱንም፥ የቤቱንም ምርጊት ሁሉ ያፈርሳል፤ እነርሱንም ከከተማው ወደ ውጭ ወደ ርኩስ ስፍራ ያወጣል። በተዘጋበትም ጊዜ ሁሉ ወደ ቤቱ የሚገባ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል። በቤቱም የሚተኛ ልብሱን ያጥባል፤ በቤቱም የሚበላ ልብሱን ያጥባል። ካህኑም ገብቶ ቢያይ፥ እነሆም፥ ቤቱ ከተመረገ በኋላ ደዌው በቤቱ ውስጥ ባይሰፋ፥ ደዌው ስለ ሻረ ካህኑ ቤቱን፦ ንጹሕ ነው ይለዋል። ቤቱንም ለማንጻት ሁለት ወፎች፥ የዝግባም እንጨት፥ ቀይ ግምጃም፥ ሂሶጵም ይወስዳል። አንደኛውንም ወፍ በሸክላ ዕቃ ውስጥ ከምንጩ ውኃ በላይ ያርዳል። የዝግባውን እንጨት፥ ሂሶጱንም፥ ቀዩንም ግምጃ፥ ሕያውንም ወፍ ወስዶ በታረደው ወፍ ደምና በምንጩ ውኃ ውስጥ ይነክራቸዋል፥ ቤቱንም ሰባት ጊዜ ይረጨዋል። ቤቱንም በወፉ ደም በምንጩም ውኃ በሕያውም ወፍ በዝግባውም እንጨት በሂሶጱም በቀዩም ግምጃ ያነጻዋል። ሕያውንም ወፍ ከከተማ ወደ ሜዳ ይሰድደዋል፤ ለቤቱም ያስተሰርይለታል፥ ንጹሕም ይሆናል። ይህም ሕግ ነው ለሁሉ ዓይነት ለምጽ ደዌ፥ ለቈረቈርም፥ በልብስና በቤትም ላለ ለምጽ፥ ለእባጭም፥ ለብጕርም፥ ለቍቁቻም፤ በሚረክስና በሚነጻ ጊዜ እንዲያስታውቅ ይህ የለምጽ ሕግ ነው።