የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 7:1-21

መጽሐፈ ኢዮብ 7:1-21 አማ54

በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን? ወራቱም እንደ ምንደኛ ወራት አይደለምን? አገልጋይ ጥላ እንደሚመኝ፥ ምንደኛም ደመወዙን እንደሚጠብቅ፥ እንዲሁ ዕጣዬ የከንቱ ወራት ሆነብኝ፥ የድካምም ሌሊት ተወሰነችልኝ። በተኛሁ ጊዜ፦ መቼ እነሣለሁ? እላለሁ። ሌሊቱ ግን ይረዝማል፥ እስኪነጋ ድረስም እገለባበጣለሁ። ሥጋዬ ትልና ጓል ለብሶአል፥ ቁርበቴ ያፈከፍካል እንደ ገናም ይመግላል። ዘመኔ ከሸማኔ መወርወርያ ይልቅ ይቸኵላል፥ ያለ ተስፋም ያልቃል። ሕይወቴ እስትንፋስ እንደ ሆነ አስብ፥ ዓይኔ መልካም ነገርን ከእንግዲህ ወዲህ አያይም። የሚያየኝ ሰው ዓይን ከእንግዲህ ወዲህ አያየኝም፥ ዓይንህ በእኔ ላይ ይሆናል፥ እኔም አልገኝም። ደመና ተበትኖ እንደሚጠፋ፥ እንዲሁ ወደ ሲኦል የሚወርድ ዳግመኛ አይወጣም። ወደ ቤቱ ዳግመኛ አይመለስም፥ ስፍራውም ዳግመኛ አያውቀውም። ስለዚህም አፌን አልከለክልም፥ በመንፈሴ ጭንቀትን እናገራለሁ፥ በነፍሴ ምሬት በኀዘን አንጐራጕራለሁ። ጠባቂ ታስነሣብኝ ዘንድ፥ እኔ ባሕር ወይስ አንበሪ ነኝን? እኔም፦ አልጋዬ ያጽናናኛል፥ መኝታዬም የኀዘን እንጕርጕሮዬን ያቀልልኛል ባልሁ ጊዜ፥ አንተ በሕልም ታስፈራራኛለህ፥ በራእይም ታስደነግጠኛለህ፥ ነፍሴም ከአጥንቴ ይልቅ መታነቅንና ሞትን መረጠች። ሕይወቴን ናቅኋት፥ ለዘላለም ልኖር አልወድድም፥ የሕይወቴ ዘመን እስትንፋስ ነውና ተወኝ። ሰው ምንድር ነው ታከብረው ዘንድ፥ ልብህንስ ትጥልበት ዘንድ፥ ማለዳ ማለዳስ ትጐበኘው ዘንድ፥ ሁልጊዜስ ትፈታተነው ዘንድ? የማትተወኝ እስከ መቼ ነው? ምራቄንስ እስክውጥ ድረስ የማትለቅቀኝ እስከ መቼ ነው? ሰውን የምትጠብቅ ሆይ፥ በድዬስ እንደ ሆነ ምን ላድርግልህ? ስለ ምን እኔን ለአንተ ዓላማ አደረግኸኝ? ስለ ምን እኔ ሸክም ሆንሁብህ? ስለ ምን መተላለፌን ይቅር አትልም? ኃጢአቴንስ ስለ ምን አታስወግድልኝም? አሁን በምድር ውስጥ እተኛለሁ፥ ማለዳ ትፈልገኛለህ፥ አታገኘኝም።