የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 7:1-21

መጽሐፈ ኢዮብ 7:1-21 አማ05

“ሰዎች ሁሉ በምድር ላይ እንደ ግዳጅ ሠራተኞች አይደሉምን? ቀኖቻቸው እንደ ቅጥር ሠራተኞች ቀኖች አይደሉምን? እነርሱም በጥላ ሥር ለማረፍ እንደሚፈልጉ አገልጋዮችና ደመወዛቸውን ለመቀበል እንደሚጠባበቁ ሙያተኞች አይደሉምን? የድካም ወሮቹ ለእኔ ጥቅም የለሽ ሆኑ፤ የችግር ሌሊቶቹም ለእኔ የጭንቅ ሌሊት ሆኑብኝ። በምተኛበት ጊዜ መቼ እነሣ ይሆን ብዬ አስባለሁ፤ ሌሊቱ ግን ይረዝምብኛል፤ እኔም እስኪነጋ ድረስ ስገላበጥ ዐድራለሁ። መላ ሰውነቴ በትል ተሞልቶአል፤ ሥጋዬም በቅርፊት ተሸፍኖአል፤ ፈንድቶም ይመግላል። የዕድሜዬ ቀኖች ከሸማኔ መወርወሪያ ይልቅ ይፈጥናሉ፤ ያለ አንዳች ተስፋም ወደ ፍጻሜ ይደርሳሉ። አምላክ ሆይ! ሕይወቴ ከትንፋሽ ያጠረ መሆኑን አስታውስ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ መልካም ነገርን አላይም። “አሁን የሚያየኝ ዳግመኛ አያየኝም፤ ቢፈልገኝም እንኳ ሊያገኘኝ አይችልም። ደመና ተበትኖ እንደሚጠፋ ሁሉ፥ ሞቶ ወደ ሙታን ዓለም የሚሄድ ሰው ተመልሶ አይመጣም፤ እንደገናም ወደ ቤቱ አይመለስም፤ የሚያውቁት ሁሉ ይረሱታል። ከእንግዲህ ወዲህ ዝም አልልም! ከመንፈስ ጭንቀቴ የተነሣ እናገራለሁ፤ ከነፍሴ ምሬት የተነሣ አጒረመርማለሁ። “ይህን ያኽል ተጠባባቂ ያደረግህብኝ እኔ ባሕር ነኝን? ወይስ ዓሣ አንበሪ? ‘አልጋዬ ያጽናናኛል፤ መኝታዬ ሕመሜን ያስታግሥልኛል፤’ ብዬ አሰብኩ፤ አንተ ግን በሕልም ታስፈራኛለህ፤ በቅዠትም ታስደነግጠኛለህ። ይህን ሥቃይ የበዛበት ሰውነት ተሸክሜ ከመኖር ታንቄ መሞትን እመርጣለሁ። ተስፋ ቈርጬአለሁ፤ መኖርም አልፈልግም፤ የሕይወቴም ዘመን አጭር ስለ ሆነ ተወኝ። “ግምት ትሰጠው ዘንድና ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? በየማለዳውስ ትመረምረው ዘንድ በየጊዜውስ ትፈትነው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ምራቄን እስክውጥ እንኳ ለጥቂት ጊዜም አትተወኝምን? አንተ ሰዎችን በመቈጣጠር የምትከታተል አምላክ ሆይ፥ እኔ ኃጢአት በመሥራቴ አንተ ምን ተበደልክ? ስለምን ዒላማ አደረግኸኝ? ይህን ያኽል ከባድ ሸክም ሆንኩብህን? ከቶ ኃጢአቴን ይቅር አትልልኝምን? የማደርገውንስ በደል አትደመስስልኝምን? ወደ መቃብር መውረጃዬ ደርሶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ብትፈልገኝ እንኳ አልገኝም።”