ኢዮብ 7:1-21

ኢዮብ 7:1-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

“ጥን​ቱን በም​ድር ላይ የሰው ሕይ​ወት ጥላ አይ​ደ​ለ​ምን? ኑሮ​ውስ እንደ ቀን ምን​ደኛ አይ​ደ​ለ​ምን? ወይም ጌታ​ውን እን​ደ​ሚ​ፈራ አገ​ል​ጋይ ጥላ​ው​ንም እን​ደ​ሚ​መኝ፥ ወይም ደመ​ወ​ዙን እን​ደ​ሚ​ጠ​ብቅ ምን​ደኛ አይ​ደ​ለ​ምን? እን​ዲሁ እኔ የከ​ንቱ ወራ​ትን ታገ​ሥሁ፥ የፃ​ዕ​ርም ሌሊት ተወ​ሰ​ነ​ች​ልኝ። በተ​ኛ​ሁም ጊዜ፦ መቼ ይነ​ጋል? እላ​ለሁ፤ በተ​ነ​ሣ​ሁም ጊዜ ዳግ​መኛ መቼ ይመ​ሻል? እላ​ለሁ፤ ከማታ እስከ ጥዋት ድረስ መከ​ራን ጠገ​ብሁ። ሥጋዬ በት​ልና በመ​ግል በስ​ብ​ሶ​አል፥ ቍስ​ሌን በገል እያ​ከ​ክሁ አለ​ቅሁ። ዐመ​ድም ሆንሁ። ሕይ​ወቴ እንደ ሸማኔ መወ​ር​ወ​ርያ፥ ቀላል ሆነች በከ​ንቱ ተስ​ፋም ጠፋሁ። ሕይ​ወቴ እስ​ት​ን​ፋስ እንደ ሆነች አስብ፤ ዐይ​ኔም መል​ካም ነገ​ርን ከእ​ን​ግ​ዲህ ወዲህ ዳግ​መኛ አታ​ይም። የሚ​ያ​የኝ ሰው ዐይን ከእ​ን​ግ​ዲህ ወዲህ አያ​የ​ኝም፤ ዐይ​ንህ በእኔ ላይ ይሆ​ናል፤ እኔም አል​ገ​ኝም። ደመና ከሰ​ማይ ተበ​ትኖ እን​ደ​ሚ​ጠፋ፥ እን​ዲሁ ወደ መቃ​ብር የሚ​ወ​ርድ ሰው ዳግ​መኛ አይ​ወ​ጣም። ወደ ቤቱም ዳግ​መኛ አይ​መ​ለ​ስም፥ ስፍ​ራ​ውም ዳግ​መኛ እር​ሱን አያ​ው​ቀ​ውም። ስለ​ዚ​ህም እኔ አፌን አል​ከ​ለ​ክ​ልም፤ በመ​ን​ፈሴ ጭን​ቀ​ትን እና​ገ​ራ​ለሁ፤ የነ​ፍ​ሴ​ንም ምሬት በኀ​ዘን እገ​ል​ጣ​ለሁ። ጠባቂ አዝ​ዘ​ህ​ብ​ኛ​ልና፥ እኔ ባሕር ወይስ አን​በሪ ነኝን? እኔም፦ አል​ጋዬ ያጽ​ና​ናኝ ይሆን? መኝ​ታ​ዬስ ደስ ያሰ​ኘኝ ይሆን? እላ​ለሁ። አን​ተም በሕ​ልም ታስ​ፈ​ራ​ራ​ኛ​ለህ፥ በራ​እ​ይም ታስ​ደ​ነ​ግ​ጠ​ኛ​ለህ፤ ሕይ​ወ​ትን ከመ​ን​ፈሴ ትለ​ያ​ለህ። አጥ​ን​ቶ​ቼ​ንም ከሞት ትጠ​ብ​ቃ​ለህ። እን​ድ​ታ​ገሥ ለዘ​ለ​ዓ​ለም እኖ​ራ​ለ​ሁን? ሕይ​ወቴ ከንቱ ነውና ከእኔ ራቅ። ሰው ምን​ድን ነው? ከፍ ከፍ ታደ​ር​ገው ዘንድ፥ ልቡ​ና​ው​ንም ትጐ​በ​ኘው ዘንድ፥ ማለዳ ማለ​ዳስ ትጐ​በ​ኘው ዘንድ፥ በዕ​ረ​ፍ​ቱም ትፈ​ር​ድ​ለት ዘንድ፥ የማ​ታ​ሳ​ር​ፈኝ እስከ መቼ ነው? ምራ​ቄ​ንስ እስ​ክ​ውጥ ድረስ የማ​ት​ለ​ቅ​ቀኝ እስከ መቼ ነው? የሰ​ውን ልብ፦ የም​ታ​ውቅ ሆይ፥ በድ​ዬስ እንደ ሆነ እን​ግ​ዲህ ምን ላደ​ር​ግ​ልህ እች​ላ​ለሁ? ስለ​ምን እኔን ለመ​ከራ አደ​ረ​ግ​ኸኝ? ስለ ምን በአ​ንተ ላይ እን​ድ​ና​ገር በአ​ም​ሳ​ልህ ፈጠ​ር​ኸኝ? ስለ ምንስ እኔ ሸክም ሆን​ሁ​ብህ? ስለ ምን መተ​ላ​ለ​ፌን ይቅር አት​ልም? ኀጢ​አ​ቴ​ንስ ስለ ምን አታ​ነ​ጻም? አሁን በም​ድር ውስጥ እተ​ኛ​ለሁ፤ በማ​ለ​ዳም አል​ነ​ቃም።”

ኢዮብ 7:1-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

“የሰው ሕይወት በምድር ላይ ብርቱ ተጋድሎ አይደለምን? ዘመኑስ እንደ ምንደኛ ዘመን አይደለምን? የምሽትን ጥላ እንደሚመኝ አገልጋይ፣ ደመወዙንም እንደሚናፍቅ ምንደኛ፣ እንዲሁ ከንቱ ወራት ታደሉኝ፣ የጕስቍልና ሌሊቶችም ተወሰኑልኝ። በተኛሁ ጊዜ ‘መቼ ነግቶ እነሣለሁ?’ እላለሁ፤ ሌሊቱ ይረዝማል፤ እስኪነጋም እገላበጣለሁ። አካሌ ቈስሎ ትልና ቅርፊት ለብሷል፤ ቈዳዬ አፈክፍኳል፤ ቍስሌም አመርቅዟል። “ዘመኔ ከሸማኔ መወርወሪያ ይልቅ ይፈጥናል፤ ያለ ተስፋም ያልቃል። ሕይወቴ ትንፋሽ ያህል እንደ ሆነች ዐስብ፤ ዐይኔም ከእንግዲህ ደስታን አያይም። አሁን የሚያየኝ ሰው ዐይን ከእንግዲህ አያየኝም፤ ትፈልገኛለህ፤ እኔ ግን የለሁም። ደመና በንኖ እንደሚጠፋ፣ ወደ መቃብር የሚወርድም አይመለስም። ወደ ቤቱ ዳግመኛ አይመለስም፤ ስፍራውም ከእንግዲህ አያውቀውም። “ስለዚህ ከቶ ዝም አልልም፤ በመንፈሴ ጭንቀት እናገራለሁ፤ በነፍሴም ምሬት አጕረመርማለሁ። በላዬ ጠባቂ ታደርግ ዘንድ፣ እኔ ባሕር ነኝን ወይስ የባሕር አውሬ? ዐልጋዬ ያጽናናኛል፣ መኝታዬም ማጕረምረሜን ይቀንስልኛል ባልሁ ጊዜ፣ አንተ በሕልም ታስፈራራኛለህ፤ በራእይም ታስደነግጠኛለህ፤ ስለዚህ እንዲህ ሆኖ ከመኖር፣ መታነቅና መሞትን እመርጣለሁ። ሕይወቴን እጸየፋለሁ፤ ዘላለም መኖር አልፈልግም፤ ዘመኔ እንደ እስትንፋስ ነውና ተወኝ። “ከፍ ከፍ ታደርገው ዘንድ፣ ልብህንም ትጥልበት ዘንድ ሰው ምንድን ነው? በየማለዳው ትመረምረዋለህ፤ በየጊዜውም ትፈትነዋለህ። ዐይንህን ከእኔ ላይ አታነሣምን? ምራቄን እንኳ እስክውጥ ፋታ አትሰጠኝምን? ሰውን የምትከታተል ሆይ፤ ኀጢአት ብሠራ፣ አንተን ምን አደርግሃለሁ? ለምን ዒላማህ አደረግኸኝ? ለምንስ ሸክም ሆንሁብህ? መተላለፌን ለምን ይቅር አትልም? ኀጢአቴንስ ለምን አታስወግድልኝም? ትቢያ ውስጥ የምጋደምበት ጊዜ ደርሷል፤ ትፈልገኛለህ፤ እኔ ግን የለሁም።”

ኢዮብ 7:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን? ወራቱም እንደ ምንደኛ ወራት አይደለምን? አገልጋይ ጥላ እንደሚመኝ፥ ምንደኛም ደመወዙን እንደሚጠብቅ፥ እንዲሁ ዕጣዬ የከንቱ ወራት ሆነብኝ፥ የድካምም ሌሊት ተወሰነችልኝ። በተኛሁ ጊዜ፦ መቼ እነሣለሁ? እላለሁ። ሌሊቱ ግን ይረዝማል፥ እስኪነጋ ድረስም እገለባበጣለሁ። ሥጋዬ ትልና ጓል ለብሶአል፥ ቁርበቴ ያፈከፍካል እንደ ገናም ይመግላል። ዘመኔ ከሸማኔ መወርወርያ ይልቅ ይቸኵላል፥ ያለ ተስፋም ያልቃል። ሕይወቴ እስትንፋስ እንደ ሆነ አስብ፥ ዓይኔ መልካም ነገርን ከእንግዲህ ወዲህ አያይም። የሚያየኝ ሰው ዓይን ከእንግዲህ ወዲህ አያየኝም፥ ዓይንህ በእኔ ላይ ይሆናል፥ እኔም አልገኝም። ደመና ተበትኖ እንደሚጠፋ፥ እንዲሁ ወደ ሲኦል የሚወርድ ዳግመኛ አይወጣም። ወደ ቤቱ ዳግመኛ አይመለስም፥ ስፍራውም ዳግመኛ አያውቀውም። ስለዚህም አፌን አልከለክልም፥ በመንፈሴ ጭንቀትን እናገራለሁ፥ በነፍሴ ምሬት በኀዘን አንጐራጕራለሁ። ጠባቂ ታስነሣብኝ ዘንድ፥ እኔ ባሕር ወይስ አንበሪ ነኝን? እኔም፦ አልጋዬ ያጽናናኛል፥ መኝታዬም የኀዘን እንጕርጕሮዬን ያቀልልኛል ባልሁ ጊዜ፥ አንተ በሕልም ታስፈራራኛለህ፥ በራእይም ታስደነግጠኛለህ፥ ነፍሴም ከአጥንቴ ይልቅ መታነቅንና ሞትን መረጠች። ሕይወቴን ናቅኋት፥ ለዘላለም ልኖር አልወድድም፥ የሕይወቴ ዘመን እስትንፋስ ነውና ተወኝ። ሰው ምንድር ነው ታከብረው ዘንድ፥ ልብህንስ ትጥልበት ዘንድ፥ ማለዳ ማለዳስ ትጐበኘው ዘንድ፥ ሁልጊዜስ ትፈታተነው ዘንድ? የማትተወኝ እስከ መቼ ነው? ምራቄንስ እስክውጥ ድረስ የማትለቅቀኝ እስከ መቼ ነው? ሰውን የምትጠብቅ ሆይ፥ በድዬስ እንደ ሆነ ምን ላድርግልህ? ስለ ምን እኔን ለአንተ ዓላማ አደረግኸኝ? ስለ ምን እኔ ሸክም ሆንሁብህ? ስለ ምን መተላለፌን ይቅር አትልም? ኃጢአቴንስ ስለ ምን አታስወግድልኝም? አሁን በምድር ውስጥ እተኛለሁ፥ ማለዳ ትፈልገኛለህ፥ አታገኘኝም።

ኢዮብ 7:1-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

“ሰዎች ሁሉ በምድር ላይ እንደ ግዳጅ ሠራተኞች አይደሉምን? ቀኖቻቸው እንደ ቅጥር ሠራተኞች ቀኖች አይደሉምን? እነርሱም በጥላ ሥር ለማረፍ እንደሚፈልጉ አገልጋዮችና ደመወዛቸውን ለመቀበል እንደሚጠባበቁ ሙያተኞች አይደሉምን? የድካም ወሮቹ ለእኔ ጥቅም የለሽ ሆኑ፤ የችግር ሌሊቶቹም ለእኔ የጭንቅ ሌሊት ሆኑብኝ። በምተኛበት ጊዜ መቼ እነሣ ይሆን ብዬ አስባለሁ፤ ሌሊቱ ግን ይረዝምብኛል፤ እኔም እስኪነጋ ድረስ ስገላበጥ ዐድራለሁ። መላ ሰውነቴ በትል ተሞልቶአል፤ ሥጋዬም በቅርፊት ተሸፍኖአል፤ ፈንድቶም ይመግላል። የዕድሜዬ ቀኖች ከሸማኔ መወርወሪያ ይልቅ ይፈጥናሉ፤ ያለ አንዳች ተስፋም ወደ ፍጻሜ ይደርሳሉ። አምላክ ሆይ! ሕይወቴ ከትንፋሽ ያጠረ መሆኑን አስታውስ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ መልካም ነገርን አላይም። “አሁን የሚያየኝ ዳግመኛ አያየኝም፤ ቢፈልገኝም እንኳ ሊያገኘኝ አይችልም። ደመና ተበትኖ እንደሚጠፋ ሁሉ፥ ሞቶ ወደ ሙታን ዓለም የሚሄድ ሰው ተመልሶ አይመጣም፤ እንደገናም ወደ ቤቱ አይመለስም፤ የሚያውቁት ሁሉ ይረሱታል። ከእንግዲህ ወዲህ ዝም አልልም! ከመንፈስ ጭንቀቴ የተነሣ እናገራለሁ፤ ከነፍሴ ምሬት የተነሣ አጒረመርማለሁ። “ይህን ያኽል ተጠባባቂ ያደረግህብኝ እኔ ባሕር ነኝን? ወይስ ዓሣ አንበሪ? ‘አልጋዬ ያጽናናኛል፤ መኝታዬ ሕመሜን ያስታግሥልኛል፤’ ብዬ አሰብኩ፤ አንተ ግን በሕልም ታስፈራኛለህ፤ በቅዠትም ታስደነግጠኛለህ። ይህን ሥቃይ የበዛበት ሰውነት ተሸክሜ ከመኖር ታንቄ መሞትን እመርጣለሁ። ተስፋ ቈርጬአለሁ፤ መኖርም አልፈልግም፤ የሕይወቴም ዘመን አጭር ስለ ሆነ ተወኝ። “ግምት ትሰጠው ዘንድና ታስበው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? በየማለዳውስ ትመረምረው ዘንድ በየጊዜውስ ትፈትነው ዘንድ ሰው ምንድን ነው? ምራቄን እስክውጥ እንኳ ለጥቂት ጊዜም አትተወኝምን? አንተ ሰዎችን በመቈጣጠር የምትከታተል አምላክ ሆይ፥ እኔ ኃጢአት በመሥራቴ አንተ ምን ተበደልክ? ስለምን ዒላማ አደረግኸኝ? ይህን ያኽል ከባድ ሸክም ሆንኩብህን? ከቶ ኃጢአቴን ይቅር አትልልኝምን? የማደርገውንስ በደል አትደመስስልኝምን? ወደ መቃብር መውረጃዬ ደርሶአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ብትፈልገኝ እንኳ አልገኝም።”

ኢዮብ 7:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

“የሰው ሕይወት በምድር ላይ ብርቱ ሰልፍ አይደለምን? ቀኖቹ እንደ ምንደኛ ቀኖች አይደሉምን? አገልጋይ ጥላ እንደሚመኝ፥ ምንደኛም ደመወዙን እንደሚጠብቅ፥ እንዲሁ ዕጣዬ የከንቱ ወራት ሆነብኝ፥ የድካምም ሌሊት ተወሰነችልኝ። በተኛሁ ጊዜ፦ መቼ እነሣለሁ? እላለሁ። ሌሊቱ ግን ይረዝማል፥ እስኪ ነጋ ድረስም እገለባበጣለሁ። ሥጋዬ ትልና ጓል ለብሶአል፥ ቆዳዬ ያፈከፍካል እንደገናም ይመግላል። ቀኖቼ ከሸማኔ መወርወርያ ይልቅ ይቸኩላሉ፥ ያለ ተስፋም ያልቃሉ።” “ሕይወቴ እስትንፋስ እንደሆነ አስታውስ፥ ዓይኔ መልካም ነገርን ከእንግዲህ ወዲህ አያይም። የሚያየኝ ሰው ዐይን ከእንግዲህ ወዲህ አያየኝም፥ ዓይንህ በእኔ ላይ ይሆናል፥ እኔም አልገኝም። ደመና ተበትኖ እንደሚጠፋ፥ እንዲሁ ወደ ሲኦል የሚወርድ ዳግመኛ አይወጣም። ወደ ቤቱ ዳግመኛ አይመለስም፥ ስፍራውም ዳግመኛ አያውቀውም።” “ስለዚህም ከመናገር አፌን አልከለክልም፥ በመንፈሴ ጭንቀትን እናገራለሁ፥ በነፍሴ ምሬት በኀዘን አንጐራጉራለሁ። እኔ ባሕር ነኝ ወይስ ዓሣ አንበሪ? ባላዬ ጠባቂ የምታኖርብኝ? እኔም፦ አልጋዬ ያጽናናኛል፥ መኝታዬም የኀዘን እንጉርጉሮዬን ያቀልልኛል ባልሁ ጊዜ፥ አንተ በሕልም ታስፈራራኛለህ፥ በራእይም ታስደነግጠኛለህ፥ ከዚህ ሥጋ ይልቅ ነፍሴ መታነቅንና ሞትን መረጠች። ሕይወቴን ናቅኋት፥ ለዘለዓለም ልኖር አልወድድም፥ ቀኖቼ እስትንፋስ ናቸውና ተወኝ። ሰው ምንድነው ታከብረው ዘንድ፥ ልብህንስ ትጥልበት ዘንድ፥ ማለዳ ማለዳስ ትጐበኘው ዘንድ፥ ሁልጊዜስ ትፈታተነው ዘንድ? የማትተወኝ እስከ መቼ ነው? ምራቄንስ እስክውጥ ድረስ የማትለቅቀኝ እስከ መቼ ነው? ሰውን የምትጠብቅ ሆይ፥ በድዬስ እንደሆነ ምን ላድርግልህ? ስለምን እኔን ዒላማ አደረግኸኝ? ስለምን እኔ ሸክም ሆንሁብህ? ስለምን መተላለፌን ይቅር አትልም? ኃጢአቴንስ ስለምን አታስወግድልኝም? አሁን በምድር ውስጥ እተኛለሁ፥ ትፈልገኛለህ፥ እኔ ግን የለሁም።”