መጽሐፈ ኢዮብ 7
7
1በምድር ላይ የሰው ሕይወት ብርቱ ሰልፍ አይደለምን?
ወራቱም እንደ ምንደኛ ወራት አይደለምን?
2አገልጋይ ጥላ እንደሚመኝ፥
ምንደኛም ደመወዙን እንደሚጠብቅ፥
3እንዲሁ ዕጣዬ የከንቱ ወራት ሆነብኝ፥
የድካምም ሌሊት ተወሰነችልኝ።
4በተኛሁ ጊዜ፦ መቼ እነሣለሁ? እላለሁ።
ሌሊቱ ግን ይረዝማል፥
እስኪነጋ ድረስም እገለባበጣለሁ።
5ሥጋዬ ትልና ጓል ለብሶአል፥
ቁርበቴ ያፈከፍካል እንደ ገናም ይመግላል።
6ዘመኔ ከሸማኔ መወርወርያ ይልቅ ይቸኵላል፥
ያለ ተስፋም ያልቃል።
7ሕይወቴ እስትንፋስ እንደ ሆነ አስብ፥
ዓይኔ መልካም ነገርን ከእንግዲህ ወዲህ አያይም።
8የሚያየኝ ሰው ዓይን ከእንግዲህ ወዲህ አያየኝም፥
ዓይንህ በእኔ ላይ ይሆናል፥ እኔም አልገኝም።
9ደመና ተበትኖ እንደሚጠፋ፥
እንዲሁ ወደ ሲኦል የሚወርድ ዳግመኛ አይወጣም።
10ወደ ቤቱ ዳግመኛ አይመለስም፥
ስፍራውም ዳግመኛ አያውቀውም።
11ስለዚህም አፌን አልከለክልም፥
በመንፈሴ ጭንቀትን እናገራለሁ፥
በነፍሴ ምሬት በኀዘን አንጐራጕራለሁ።
12ጠባቂ ታስነሣብኝ ዘንድ፥
እኔ ባሕር ወይስ አንበሪ ነኝን?
13እኔም፦ አልጋዬ ያጽናናኛል፥
መኝታዬም የኀዘን እንጕርጕሮዬን ያቀልልኛል ባልሁ ጊዜ፥
14አንተ በሕልም ታስፈራራኛለህ፥
በራእይም ታስደነግጠኛለህ፥
15ነፍሴም ከአጥንቴ ይልቅ
መታነቅንና ሞትን መረጠች።
16ሕይወቴን ናቅኋት፥ ለዘላለም ልኖር አልወድድም፥
የሕይወቴ ዘመን እስትንፋስ ነውና ተወኝ።
17ሰው ምንድር ነው ታከብረው ዘንድ፥
ልብህንስ ትጥልበት ዘንድ፥
18ማለዳ ማለዳስ ትጐበኘው ዘንድ፥
ሁልጊዜስ ትፈታተነው ዘንድ?
19የማትተወኝ እስከ መቼ ነው?
ምራቄንስ እስክውጥ ድረስ የማትለቅቀኝ እስከ መቼ ነው?
20ሰውን የምትጠብቅ ሆይ፥ በድዬስ እንደ ሆነ ምን ላድርግልህ?
ስለ ምን እኔን ለአንተ ዓላማ አደረግኸኝ?
ስለ ምን እኔ ሸክም ሆንሁብህ?
21ስለ ምን መተላለፌን ይቅር አትልም?
ኃጢአቴንስ ስለ ምን አታስወግድልኝም?
አሁን በምድር ውስጥ እተኛለሁ፥
ማለዳ ትፈልገኛለህ፥ አታገኘኝም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 7: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ