የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 38

38
1እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ እንዲህም አለ፦
2ያለ እውቀት በሚነገር ቃል
ምክርን የሚያጨልም ይህ ማነው?
3እንግዲህ እንደ ሰው ወገብህን ታጠቅ፥
እጠይቅሃለሁ፥ አንተም ተናገረኝ።
4ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርህ?
ታስተውል እንደ ሆንህ ተናገር።
5ብታውቅስ መሠፈሪያዋን የወሰነ፥
በላይዋስ የመለኪያ ገመድ የዘረጋ ማን ነው?
6-7አጥቢያ ኮከቦች በአንድነት ሲዘምሩ፥
የእግዚአብሔርም ልጆች ሁሉ እልል ሲሉ፥
መሠረቶችዋ በምን ላይ ተተክለው ነበር?
የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው?
8ከማኅፀን እንደሚወጣ በወጣ ጊዜ
ባሕርን በመዝጊያዎች የዘጋ ማን ነው?
9ደመናውን ለልብሱ፥
ጨለማንም ለመጠቅለያው አደረግሁ፥
10ድንበሩን በዙሪያው አድርጌ፥
መወርወሪያዎቹንና መዝጊያዎቹን አኑሬ፦
11እስከዚህ ድረስ ድረሺ፥ አትለፊ፥
በዚህም ለትዕቢተኛው ማዕበልሽ ገደብ ይሁን አልሁ።
12-13የምድርን ዳርቻ ይይዝ ዘንድ፥
ከእርስዋም በደለኞች ይናወጡ ዘንድ፥
በውኑ ከተወለድህ ጀምሮ ማለዳን አዝዘሃልን?
ለወገግታም ስፍራውን አስታውቀኸዋልን?
14ጭቃ ከማኅተም በታች እንደሚለወጥ እንዲሁ እርስዋ ትለወጣለች፥
ነገርም ሁሉ እንደ ልብስ ተቀልሞአል።
15ከበደለኞች ብርሃናቸው ተከልክሎአል፥
ከፍ ያለውም ክንድ ተሰብሮአል።
16ወደ ባሕር ምንጭስ ውስጥ ገብተሃልን?
በቀላዩስ መሠረት ውስጥ ተመላልሰሃልን?
17የሞት በሮች ተገልጠውልሃልን?
የሞትንስ ጥላ ደጆች አይተሃልን?
18ምድርንስ በስፋትዋ አስተውለሃታልን?
ሁሉን አውቀህ እንደ ሆነ ተናገር።
19-20ወደ ዳርቻው ትነዳው ዘንድ፥
ወደ ቤቱም የሚያደርሰውን ጐዳና ታውቅ ዘንድ፥
የብርሃን መኖሪያ መንገድ የት ነው?
የጨለማውስ ቦታ ወዴት አለ?
21በዚያን ጊዜ ተወልደህ ነበርና፥
የዕድሜህም ቍጥር ብዙ ነውና፥
በእውነት አንተ ሳታውቅ አትቀርም።
22በውኑ ወደ በረዶው ቤተ መዛግብት ገብተሃልን?
የበረዶውንስ ቅንጣት ቤተ መዛግብት አይተሃልን?
23ይኸውም ለመከራ ጊዜ ለሰልፍና ለጦርነት ቀን የጠበቅሁት ነው።
24ብርሃንስ በምን መንገድ ይከፈላል?
የምሥራቅስ ነፋስ በምድር ላይ እንዴት ይበተናል?
25-26ባድማውንና ውድማውን እንዲያጠግብ፥
27ሣሩንም እንዲያበቅል፥
ማንም በሌለባት ምድር ላይ፥
ሰውም በሌለባት ምድረ በዳ ላይ ዝናብን ያዘንብ ዘንድ፥
ለፈሳሹ ውኃ መንዶልዶያውን፥
ወይስ ለሚያንጐደጕድ መብረቅ መንገድን ያበጀ ማን ነው?
28በውኑ ለዝናብ አባት አለውን?
ወይስ የጠልን ነጠብጣብ የወለደ ማን ነው?
29በረዶስ ከማን ማኅፀን ወጣ?
የሰማዩንስ አመዳይ ማን ወለደው?
ውኆች እንደ ድንጋይ ጠነከሩ፥
30የቀላዩም ፊት ረግቶአል።
31በውኑ የሰባቱን ከዋክብት ዘለላ ታስር ዘንድ፥
ወይስ ኦሪዮን የሚባለውን ኮከብ ትፈታ ዘንድ ትችላለህን?
32ወይስ ማዛሮት የሚባሉትን ከዋክብት በጊዜያቸው ታወጣ ዘንድ፥
ወይስ ድብ የሚባለውን ኮከብ ከልጆቹ ጋር ትመራ ዘንድ ትችላለህን?
33የሰማይን ሥርዓት ታውቃለህን?
በምድርስ ለይ እንዲሠለጥን ልታደርግ ትችላለህን?
34የውኆች ብዛት ይሸፍንህ ዘንድ።
ቃልህን ወደ ደመናት ታነሣ ዘንድ ትችላለህን?
35መብረቆች ሄደው፦ እነሆ፥ እዚህ አለን ይሉህ ዘንድ፥
ልትልካቸው ትችላለህን?
36በውስጡስ ጥበብን ያኖረ፥
ለሰውስ ልብ ማስተዋልን የሰጠ ማን ነው?
37-38የሰማይን ደመና በጥበቡ ሊቈጥር የሚችል ማን ነው?
ትቢያ በተበጠበጠ ጊዜ፥
ጓሎቹም በተጣበቁ ጊዜ፥
የሰማይን ረዋት ሊያዘነብል የሚችል ማን ነው?
39-40በዋሾቻቸው ውስጥ ተጋድመው፥
በጫካም ውስጥ አድብተው ሳሉ፥
ለአንበሳይቱ አደን ታድናለህን?
የልጆችዋንስ ነፍስ ታጠግብ ዘንድ ትችላለህን?
41ልጆቹ ወደ እግዚአብሔር ሲጮኹ
የሚበሉትም አጥተው ሲቅበዘበዙ፥
ለቍራ መብልን የሚሰጠው ማን ነው?

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ