የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ኢዮብ 13

13
1እነሆ፥ ይህን ሁሉ ዓይኔ አየች፥
ጆሮዬም ሰምታ አስተዋለችው።
2እናንተ የምታውቁትን እኔ ደግሞ አውቃለሁ፥
ከእናንተ የማንስ አይደለሁም።
3ነገር ግን ሁሉን ለሚችል አምላክ መናገር እፈልጋለሁ፥
ከእግዚአብሔርም ጋር ለመዋቀስ እሻለሁ።
4እናንተ ግን በሐሰት ለባጮች ናችሁ፥
ሁላችሁ የማትጠቅሙ ባለ መድኃኒቶች ናችሁ።
5ምነው ዝም ብላችሁ ብትኖሩ!
ይህ ጥበብ በሆነላችሁ ነበር።
6አሁንም ክርክሬን ስሙ፥
የከንፈሬንም ሙግት አድምጡ።
7በውኑ ስለ እግዚአብሔር ሐሰትን ትናገራላችሁን?
ስለ እርሱም ሽንገላን ታወራላችሁን?
8ለፊቱስ ታደላላችሁን?
ስለ እግዚአብሔርስ ትከራከራላችሁን?
9ቢመረምራችሁስ መልካም ይሆንልችኋልን?
ወይስ በሰው እንደምትሳለቁ ትሳለቁበታላችሁን?
10በስውር ለሰው ፊት ብታደሉ
ዘለፋ ይዘልፋችኋል።
11ክብሩስ አያስፈራችሁምን?
ግርማውስ አይወድቅባችሁምን?
12ምስሌዎቻችሁ የአመድ ምሳሌዎች ናቸው፥
ምሽጎቻችሁ የጭቃ ምሽጎች ናቸው።
13ዝም በሉ፥ እናገርም ዘንድ ተዉኝ፥
የሆነው ነገር ይምጣብኝ።
14ሥጋዬን በጥርሴ እይዛለሁ፥
ሕይወቴንም በእጄ አኖራለሁ።
15እነሆ፥ ቢገድለኝ ስንኳ እርሱን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ፥
ነገር ግን መንገዴን በፊቱ አጸናለሁ።
16ዝንጉ ሰው በፊቱ አይገባምና
እርሱ መድኃኒት ይሆንልኛል።
17ነገሬን ተግታችሁ ስሙ፥
ምስክርነቴንም በጆሮአችሁ አድምጡ።
18እነሆ፥ ሙግቴን አዘጋጅቻለሁ።
እንደምጸድቅም አውቃለሁ።
19ከእኔስ ጋር የሚፋረድ ማን ነው?
አሁን እኔ ዝም ብል እሞታለሁ።
20ነገር ግን ሁለት ነገር አታድርግብኝ፥
የዚያን ጊዜ ከፊትህ አልሰወርም፥
21እጅህን ከእኔ አርቅ፥
ግርማህም አታስደንግጠኝ።
22ከዚያም በኋላ ጥራኝ፥ እኔም እመልስልሃለሁ።
ወይም እኔ ልናገር፥ አንተም መልስልኝ።
23ያለብኝስ በደልና ኃጢአት ምን ያህል ነው?
መተላለፌንና ኃጢአቴን አስታውቀኝ።
24ፊትህን ከእኔ የሰወርህ፥
እንደ ጠላትህም የቈጠርኸኝ ስለ ምን ነው?
25የረገፈውን ቅጠል ታስጨንቃለህን?
ወይስ የደረቀውን ዕብቅ ታሳድዳለህን?
26የመረረ ነገር ጽፈህብኛልና፥
የሕፃንነቴንም ኃጢአት ታወርሰኛለህ።
27እግሬንም በእግር ግንድ አግብተሃል፥
መንገዴንም ሁሉ መርምረሃል፥
የእግሬን ፍለጋ ወስነሃል።
28እኔ እንደሚጠፋ በስባሳ ነገር፥
ብልም እንደሚበላው ልብስ ነኝ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ