መጽሐፈ ኢዮብ 12
12
1ኢዮብም መለሰ እንዲህም አለ፦
2በእርግጥ እናንተ ዓይነተኞች ሰዎች ናቸሁ፥
ጥበብም ከእናንተ ጋር ይሞታል።
3ነገር ግን እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ማስተዋል አለኝ፥
ከእናንተም የማንስ አይደለሁም፥
እንደዚህ ያለውን ነገር የማያውቅ ማን ነው?
4እግዚአብሔርን የጠራሁ እርሱም የመለሰልኝ እኔ
ለባልንጀራው መሳለቂያ እንደሚሆን ሰው ሆኛለሁ፥
ጻድቅና ፍጹም ሰው መሳለቂያ ሆኖአል።
5ተዘልሎ በሚቀመጥ ሰው አሳብ መከራ ይናቃል፥
ነገር ግን እግሩን ሊያድጠው ተዘጋጅቶአል።
6የቀማኞች ድንኳን በደኅንነት ይኖራል፥
እግዚአብሔርንም የሚያስቈጡ ተዘልለው ተቀምጠዋል፥
እግዚአብሔር ሁሉን በእጃቸው አምጥቶላቸዋል።
7አሁን ግን እንስሶችን ጠይቅ፥ ያስተምሩህማል፥
የሰማይንም ወፎች ጠይቅ፥ ይነግሩህማል።
8ወይም ለምድር ተናገር፥ እርስዋም ታስተምርሃለች፥
የባሕርም ዓሣዎች ይነግሩሃል።
9የእግዚአብሔር እጅ ይህን እንዳደረገ
ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው?
10የሕያዋን ሁሉ ነፍስ
የሰውም ሁሉ መንፈስ በእጁ ናት።
11ምላስ መብልን እንደሚቀምስ፥
ጆሮ ቃልን የሚለይ አይደለምን?
12በሽምግልና ጊዜ ጥበብ፥
በዘመንስ ርዝመት ማስተዋል ይገኛል።
13በእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ኃይል አለ፥
ለእርሱ ምክርና ማስተዋል አለው።
14እነሆ፥ ይፈርሳል፥ የፈረሰውም ተመልሶ አይሠራም፥
በሰውም ቢዘጋበት የሚከፍትለት የለም።
15እነሆ፥ ውኆቹን ይከለክላል፥ እነርሱም ይደርቃሉ።
እንደ ገና ይሰዳቸዋል፥ ምድሪቱንም ይገለብጣሉ።
16ኃይልና ጥበብ በእርሱ ዘንድ ናቸው፥
የሚስተውና የሚያስተው ለእርሱ ናቸው።
17መካሮችንም እንደ ዘረፋ ይወስዳቸዋል፥
ፈራጆችንም ያሳብዳል።
18የነገሥታትንም እስራት ይፈታል፥
ወገባቸውንም በመታጠቂያ ያስራቸዋል።
19ካህናትን እንደ ዘረፋ ይወስዳቸዋል፥
ኃያላንንም ይገለብጣቸዋል።
20ከታመኑ ሰዎችም ቋንቋን ያርቃል፥
የሽማግሌዎችንም ማስተዋል ይወስድባቸዋል።
21በአለቆች ላይ ንቀትን ያፈስሳል፥
የብርቱዎችንም መታጠቂያ ያላላል።
22ጥልቅ ነገር ከጨለማ ይገልጣል፥
የሞትንም ጥላ ወደ ብርሃን ያወጣል።
23አሕዛብን ከፍ ከፍ ያደርጋል፥ እነርሱንም ያጠፋል፥
አሕዛብንም ያሰፋል፥ እነርሱንም ያፈልሳቸዋል።
24ከምድር አሕዛብ አለቆች ዘንድ ማስተዋልን ይወስዳል፥
መንገድም በሌለበት በረሃ ያቅበዘብዛቸዋል።
25ብርሃንም ሳይኖር በጨለማ ይርመሰመሳሉ፥
እንደ ሰካራም ይቅበዘበዛሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 12: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ