ዖፅ በሚባል አገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፥ ያም ሰው ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ነበረ። ሰባትም ወንዶች ሦስትም ሴቶች ልጆች ተወልደውለት ነበር። ሀብቱም ሰባት ሺህ በጎች፥ ሦስት ሺህም ግመሎች፥ አምስት መቶም ጥማድ በሬ፥ አምስት መቶም እንስት አህዮች ነበረ፥ እጅግ ብዙም ባሪያዎች ነበሩት፥ ያም ሰው በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ ነበረ። ወንዶች ልጆቹም ሄደው በየተራ በያንዳንዳቸው ቤት ግብዣ ያደርጉ ነበር፥ ሦስቱ እኅቶቻቸውም ከእነርሱ ጋር ይበሉና ይጠጡ ዘንድ እነርሱ ልከው ይጠሩአቸው ነበር። የግብዣውም ቀኖች ባለፉ ጊዜ ኢዮብ፦ ምናልባት ልጆቼ በድለው፥ እግዚአብሔርንም በልባቸው ሰድበው ይሆናል ብሎ ይልክና ይቀድሳቸው ነበር፥ ኢዮብም ማልዶ ተነሣ፥ እንደ ቍጥራቸውም ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። እንዲሁ ኢዮብ ሁልጊዜ ያደርግ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፥ የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፥ ሰይጣንም ደግሞ በመካከላቸው መጣ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም፦ ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም አለው። ሰይጣንም ለእግዚአብሔር እንዲህ ብሎ መለሰለት፦ በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን? እርሱንና ቤቱን በዙሪያውም ያሉትን ሁሉ አላጠርህለትምን? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፥ ከብቱም በምድር ላይ በዝቶአል። ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳብስ፥ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ እነሆ ለእርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው፥ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጅህን አትዘርጋ አለው። ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ።
መጽሐፈ ኢዮብ 1 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢዮብ 1:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች