የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኢዮብ 1:1-12

ኢዮብ 1:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አው​ስ​ጢድ በሚ​ባል ሀገር ስሙ ኢዮብ የተ​ባለ አንድ ሰው ነበረ፤ ያም ሰው ቅን፥ ንጹ​ሕና ጻድቅ፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም የሚ​ፈራ፥ ከክፉ ሥራም ሁሉ የራቀ ነበር። ሰባ​ትም ወን​ዶች፥ ሦስ​ትም ሴቶች ልጆች ነበ​ሩት። ከብ​ቶ​ቹም፦ ሰባት ሺህ በጎች፥ ሦስት ሺህ ግመ​ሎች፥ አም​ስት መቶም ጥማድ በሬ፥ አም​ስት መቶም እን​ስት አህ​ዮች ነበሩ፤ እጅግ ብዙም አገ​ል​ጋ​ዮች ነበ​ሩት፤ ሥራ​ውም በም​ድር ላይ ታላቅ ነበረ፤ ያም ሰው በም​ሥ​ራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ገናና ነበረ። ወን​ዶች ልጆ​ቹም ሄደው በየ​ተራ በእ​ያ​ን​ዳ​ን​ዳ​ቸው ቤት ግብዣ ያደ​ርጉ ነበር፤ ሦስቱ እኅ​ቶ​ቻ​ቸ​ው​ንም ከእ​ነ​ርሱ ጋር ይወ​ስ​ዱ​አ​ቸው ነበር፤ ከእ​ነ​ር​ሱም ጋር ይበ​ሉና ይጠጡ ነበር። የግ​ብ​ዣ​ውም ቀኖች በተ​ፈ​ጸሙ ጊዜ ኢዮብ ይል​ክና ይቀ​ድ​ሳ​ቸው ነበር፤ በማ​ለ​ዳም ገሥ​ግሦ፦ ስለ ልጆቹ በቍ​ጥ​ራ​ቸው መሥ​ዋ​ዕት ያቀ​ርብ ነበር፤ አንድ ወይ​ፈን ስለ ነፍ​ሳ​ቸው የኀ​ጢ​አት መሥ​ዋ​ዕት ያቀ​ርብ ነበር፤ ኢዮብ፥ “ምና​ል​ባት ልጆቼ በል​ባ​ቸው በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ላይ ክፉ ነገር ያስቡ ይሆ​ናል” ይል ነበ​ርና። ከዕ​ለ​ታት አንድ ቀንም እን​ዲህ ሆነ፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መላ​እ​ክት በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ለመ​ቆም መጡ፤ ሰይ​ጣ​ንም ደግሞ ከእ​ነ​ርሱ ጋር መጣ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሰይ​ጣ​ንን፥ “ከወ​ዴት መጣህ?” አለው። ሰይ​ጣ​ንም፥ “ምድ​ርን ሁሉ ዞር​ሁ​አት፥ ከሰ​ማይ በታ​ችም ተመ​ላ​ለ​ስ​ሁና መጣሁ።” ብሎ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መለሰ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሰይ​ጣ​ንን አለው፥ “በባ​ሪ​ያዬ በኢ​ዮብ ላይ የም​ታ​ስ​በው ነገር እን​ዳ​ይ​ኖር ተጠ​ን​ቀቅ! በም​ድር ላይ እንደ እርሱ ቅን፥ ንጹ​ሕና ጻድቅ፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ር​ንም የሚ​ፈራ፥ ከክፉ ሥራም ሁሉ የራቀ ሰው የለ​ምና።” ሰይ​ጣ​ንም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት እን​ዲህ ብሎ መለሰ፥ “በውኑ ኢዮብ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን የሚ​ያ​መ​ል​ከው በከ​ንቱ ነውን? አንተ ቤቱን በው​ስ​ጥም በው​ጭም፥ በዙ​ሪ​ያው ያለ​ው​ንም ሁሉ አል​ሞ​ላ​ህ​ለ​ት​ምን? የእ​ጁ​ንም ሥራ ባር​ከ​ህ​ለ​ታል፥ ከብ​ቱ​ንም በም​ድር ላይ አብ​ዝ​ተ​ህ​ለ​ታል። ነገር ግን እጅ​ህን ዘር​ግ​ተህ ያለ​ውን ሁሉ ዳስስ፤ በእ​ው​ነት በፊ​ትህ ይሰ​ድ​ብ​ሃል።” እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሰይ​ጣ​ንን፥ “እነሆ፥ ለእ​ርሱ ያለ​ውን ሁሉ በእ​ጅህ ሰጠ​ሁህ፥ ነገር ግን በእ​ርሱ ላይ እጅ​ህን አት​ዘ​ርጋ” አለው። ሰይ​ጣ​ንም ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ወጣ።

ኢዮብ 1:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዖፅ በሚባል አገር የሚኖር ኢዮብ የተባለ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ነበር። እርሱም ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ነበሩት። ሀብቱም ሰባት ሺሕ በጎች፣ ሦስት ሺሕ ግመሎች፣ አምስት መቶ ጥማድ በሬዎችና አምስት መቶ እንስት አህዮች ነበረ፤ እጅግ ብዙ ባሮችም ነበሩት፤ በምሥራቅ አገር ከሚኖሩትም ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ታላቅ ሰው ነበረ። ወንዶች ልጆቹም ተራ በተራ በየቤታቸው ግብዣ ያደርጉ ነበር፤ ከእነርሱም ጋር እንዲበሉና እንዲጠጡ ሦስቱን እኅቶቻቸውን ይጋብዙ ነበር። የግብዣው ጊዜ ካለፈ በኋላ ኢዮብ ልኮ ያስመጣቸውና፣ “ምናልባት ልጆቼ ኀጢአት ሠርተው፣ እግዚአብሔርንም በልባቸው ረግመው ይሆናል” በማለት ጧት በማለዳ ስለ እያንዳንዳቸው የሚቃጠል መሥዋዕት በማቅረብ ያነጻቸው ነበር፤ ኢዮብ ይህን ዘወትር ያደርግ ነበር። አንድ ቀን መላእክት በእግዚአብሔር ፊት ሊቆሙ በመጡ ጊዜ፣ ሰይጣንም መጥቶ በመካከላቸው ቆመ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “ከወዴት መጣህ?” አለው። ሰይጣንም፣ “በምድር ሁሉ ዞርሁ፤ ወዲያና ወዲህም ተመላለስሁባት” ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ሰው የለም” አለው። ሰይጣንም፣ ለእግዚአብሔር እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራው እንዲሁ ነውን? በእርሱና በቤተ ሰቦቹ፣ ባለው ንብረትስ ሁሉ ዙሪያ ዐጥር ሠርተህለት የለምን? የበጎቹና የላሞቹ መንጋ ምድርን ሁሉ እስኪሞሉ ድረስ የእጁን ሥራ ባርከህለታል። እስቲ፣ እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ንካበት፤ በርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።” እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “እነሆ፤ እርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው፤ እርሱን ራሱን ግን እንዳትነካው” አለው። ከዚህ በኋላ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ሄደ።

ኢዮብ 1:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ዖፅ በሚባል አገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፥ ያም ሰው ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ነበረ። ሰባትም ወንዶች ሦስትም ሴቶች ልጆች ተወልደውለት ነበር። ሀብቱም ሰባት ሺህ በጎች፥ ሦስት ሺህም ግመሎች፥ አምስት መቶም ጥማድ በሬ፥ አምስት መቶም እንስት አህዮች ነበረ፥ እጅግ ብዙም ባሪያዎች ነበሩት፥ ያም ሰው በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ ነበረ። ወንዶች ልጆቹም ሄደው በየተራ በያንዳንዳቸው ቤት ግብዣ ያደርጉ ነበር፥ ሦስቱ እኅቶቻቸውም ከእነርሱ ጋር ይበሉና ይጠጡ ዘንድ እነርሱ ልከው ይጠሩአቸው ነበር። የግብዣውም ቀኖች ባለፉ ጊዜ ኢዮብ፦ ምናልባት ልጆቼ በድለው፥ እግዚአብሔርንም በልባቸው ሰድበው ይሆናል ብሎ ይልክና ይቀድሳቸው ነበር፥ ኢዮብም ማልዶ ተነሣ፥ እንደ ቍጥራቸውም ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ። እንዲሁ ኢዮብ ሁልጊዜ ያደርግ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፥ የአምላክ ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ለመቆም መጡ፥ ሰይጣንም ደግሞ በመካከላቸው መጣ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም፦ ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ በውኑ ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም አለው። ሰይጣንም ለእግዚአብሔር እንዲህ ብሎ መለሰለት፦ በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን? እርሱንና ቤቱን በዙሪያውም ያሉትን ሁሉ አላጠርህለትምን? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፥ ከብቱም በምድር ላይ በዝቶአል። ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳብስ፥ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል። እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ እነሆ ለእርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው፥ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጅህን አትዘርጋ አለው። ሰይጣንም ከእግዚአብሔር ፊት ወጣ።

ኢዮብ 1:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ዑፅ ተብላ በምትጠራ አገር ኢዮብ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ከክፉ ነገር ሁሉ ርቆ እግዚአብሔርን የሚፈራ፥ ምንም ነውር የሌለበት፥ ቅን ሰው ነበር። ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆችም ነበሩት። በሀብትም በኩል ሰባት ሺህ በጎች፥ ሦስት ሺህ ግመሎች፥ አምስት መቶ ጥማድ በሬዎችና አምስት መቶ አህዮች ነበሩት፤ እንዲሁም እጅግ ብዙ አገልጋዮች ነበሩት፤ በምሥራቅ አገር ካሉት ሰዎች ሁሉ እርሱን የሚያኽል ሀብታምና ታላቅ ሰው አልነበረም። የኢዮብ ወንዶች ልጆች በእያንዳንዳቸው ቤት በተራ ግብዣ እያዘጋጁ በአንድነት ተሰብስበው ይደሰቱ ነበር፤ ሦስቱንም እኅቶቻቸውን እያስጠሩ ከእነርሱ ጋር አብረው ይበሉና ይጠጡ ነበር። የግብዣዎቹ ቀኖች ከተፈጸሙ በኋላ ኢዮብ በማለዳ ተነሥቶ ልጆቹን ያስጠራና በእያንዳንዱ ልጁ ስም መሥዋዕት ያቀርብ ነበር፤ ይህንንም የሚያደርገው “ምናልባት ከልጆቼ አንዱ እግዚአብሔርን በመስደብ በድሎ ይሆናል!” በሚል ስጋት ልጆቹን ከኃጢአት ለማንጻት ነበር። ኢዮብ ይህን ሥርዓት ሳያቋርጥ ዘወትር ይፈጽም ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን የሰማይ መላእክት በእግዚአብሔር ፊት በቀረቡ ጊዜ ሰይጣንም አብሮአቸው ቀረበ። እግዚአብሔርም “ከወዴት መጣህ?” ብሎ ሰይጣንን ጠየቀው። ሰይጣንም “በምድር ዙሪያ ወዲያና ወዲህ እመላለስ ነበር” አለ። እግዚአብሔር ሰይጣንን “አገልጋዬን ኢዮብን ልብ ብለህ አየኸውን? እርሱን የመሰለ ታማኝና ደግ ሰው በምድር ላይ አይገኝም፤ እርሱ ከክፋት ሁሉ ርቆ እኔን የሚፈራ ቀጥተኛ ሰው ነው” አለ። ሰይጣንም እንዲህ አለ፦ “ኢዮብ አንተን እግዚአብሔርን የሚፈራ ያለ ምክንያት ነውን? እርሱ አንተን የሚፈራህ እርሱንና ልጆቹን፥ ያለውንም ንብረት ሁሉ በደኅና ስለ ጠበቅህለት፥ የሚሠራውንም ሁሉ ስለ ባረክህለትና ብዙ የከብት መንጋ ስለ ሰጠኸው አይደለምን? ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ብታጠፋበት ፊት ለፊት ይሰድብሃል።” እግዚአብሔርም ሰይጣንን “እሺ፤ እንግዲያውስ በኢዮብ ላይ ብቻ አንዳች ጒዳት አታድርስበት እንጂ ባለው ሀብት ሁሉ ላይ የፈለግኸውን ማድረግ ትችላለህ” አለው። ከዚህ በኋላ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ሄደ።

ኢዮብ 1:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ዖፅ በሚባል አገር ስሙ ኢዮብ የተባለ አንድ ሰው ነበረ፤ ያም ሰው ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ነበረ። ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆችም ነበሩት። ሰባት ሺህ በጎች፥ ሦስት ሺህ ግመሎች፥ አምስት መቶ ጥማድ በሬዎች፥ አምስት መቶ እንስት አህዮችና እጅግ ብዙም አገልጋዮች ነበሩት። ያም ሰው በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ ነበረ። ወንዶች ልጆቹም ሄደው በየተራ በያንዳንዳቸው ቤት ግብዣ ያሰናዱ ነበር፥ ሦስቱ እኅቶቻቸውም ከእነርሱ ጋር ይበሉና ይጠጡ ዘንድ ልከው ይጠሩአቸው ነበር። የግብዣውም ቀኖች ባለፉ ጊዜ ኢዮብ፦ “ምናልባት ልጆቼ በድለው፥ እግዚአብሔርንም በልባቸው ሰድበው ይሆናል” ብሎ ይልክና ይቀድሳቸው ነበር፥ ኢዮብም ማልዶ ይነሣና እንደ ቁጥራቸውም ሁሉ የሚቃጠል መሥዋዕት ያቀርብ ነበር። ኢዮብም ሁልጊዜ እንዲህ ያደርግ ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን እንዲህ ሆነ፤ የአምላክ ልጆች በጌታ ፊት ለመቆም መጡ፥ ሰይጣንም ደግሞ በመካከላቸው መጣ። ጌታም ሰይጣንን፦ “ከወዴት መጣህ?” አለው። ሰይጣንም፦ “ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርሷም ተመላለስሁ” ብሎ ለጌታ መለሰ። ጌታም ሰይጣንን፦ “በውኑ አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም” አለው። ሰይጣንም ለጌታ እንዲህ ብሎ መለሰለት፦ “በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን? እርሱንና ቤቱን በዙሪያውም ያሉትን ሁሉ አላጠርህለትምን? የእጁን ሥራ ባርከህለታል፥ ንብረቱም በምድር ላይ በዝቶአል። ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳስስ፥ በእውነት በፊትህ ይሰድብሃል።” ጌታም ሰይጣንን፦ “እነሆ ለእርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው፥ ነገር ግን በእርሱ ላይ እጅህን አትዘርጋ” አለው። ሰይጣንም ከጌታ ፊት ወጣ።