ኢዮብ 1
1
መግቢያ
1ዖፅ በሚባል አገር የሚኖር ኢዮብ የተባለ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ነበር። 2እርሱም ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆች ነበሩት። 3ሀብቱም ሰባት ሺሕ በጎች፣ ሦስት ሺሕ ግመሎች፣ አምስት መቶ ጥማድ በሬዎችና አምስት መቶ እንስት አህዮች ነበረ፤ እጅግ ብዙ ባሮችም ነበሩት፤ በምሥራቅ አገር ከሚኖሩትም ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ታላቅ ሰው ነበረ።
4ወንዶች ልጆቹም ተራ በተራ በየቤታቸው ግብዣ ያደርጉ ነበር፤ ከእነርሱም ጋር እንዲበሉና እንዲጠጡ ሦስቱን እኅቶቻቸውን ይጋብዙ ነበር። 5የግብዣው ጊዜ ካለፈ በኋላ ኢዮብ ልኮ ያስመጣቸውና፣ “ምናልባት ልጆቼ ኀጢአት ሠርተው፣ እግዚአብሔርንም በልባቸው ረግመው ይሆናል” በማለት ጧት በማለዳ ስለ እያንዳንዳቸው የሚቃጠል መሥዋዕት በማቅረብ ያነጻቸው ነበር፤ ኢዮብ ይህን ዘወትር ያደርግ ነበር።
የመጀመሪያው የኢዮብ ፈተና
6አንድ ቀን መላእክት#1፥6 በዕብራይስጡ የእግዚአብሔር ልጆች ይላል። በእግዚአብሔር ፊት ሊቆሙ በመጡ ጊዜ፣ ሰይጣንም#1፥6 ሰይጣን ማለት ከሳሽ ማለት ነው። መጥቶ በመካከላቸው ቆመ። 7እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “ከወዴት መጣህ?” አለው።
ሰይጣንም፣ “በምድር ሁሉ ዞርሁ፤ ወዲያና ወዲህም ተመላለስሁባት” ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ።
8 እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “አገልጋዬን ኢዮብን ተመለከትኸውን? በምድር ላይ እንደ እርሱ ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ሰው የለም” አለው።
9ሰይጣንም፣ ለእግዚአብሔር እንዲህ ሲል መለሰለት፤ “ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራው እንዲሁ ነውን? 10በእርሱና በቤተ ሰቦቹ፣ ባለው ንብረትስ ሁሉ ዙሪያ ዐጥር ሠርተህለት የለምን? የበጎቹና የላሞቹ መንጋ ምድርን ሁሉ እስኪሞሉ ድረስ የእጁን ሥራ ባርከህለታል። 11እስቲ፣ እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ንካበት፤ በርግጥ ፊት ለፊት ይረግምሃል።”
12 እግዚአብሔርም ሰይጣንን፣ “እነሆ፤ እርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው፤ እርሱን ራሱን ግን እንዳትነካው” አለው።
ከዚህ በኋላ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ሄደ።
13አንድ ቀን የኢዮብ ወንዶችና ሴቶች ልጆች በታላቅ ወንድማቸው ቤት ተሰብስበው ይበሉና የወይን ጠጅ ይጠጡ ነበር፤ 14መልእክተኛም ወደ ኢዮብ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በሬዎች እያረሱ፣ አህዮችም በአጠገባቸው እየጋጡ ሳሉ፣ 15ሳባውያን ጥቃት አድርሰውባቸው ይዘዋቸው ሄዱ፤ አገልጋዮቹንም በሰይፍ ገደሉ። እኔም ብቻዬን አመለጥሁ፤ ልነግርህም መጣሁ።”
16እርሱም እየተናገረ ሳለ፣ ሌላ መልእክተኛ መጥቶ፣ “የእግዚአብሔር እሳት ከሰማይ ወረደች፤ በጎችንና አገልጋዮችንም በላች፤ እኔም ብቻዬን አመለጥሁ፤ ልነግርህም መጣሁ” አለው።
17እርሱም እየተናገረ ሳለ፣ ሌላ መልእክተኛ መጥቶ፣ “ከለዳውያን በሦስት ቡድን መጥተው ጥቃት አደረሱ፤ ግመሎችህንም ይዘው ሄዱ፤ አገልጋዮቹን በሰይፍ ገደሉ፤ እኔም ብቻዬን አመለጥሁ፤ ልነግርህም መጣሁ” አለው።
18እርሱም እየተናገረ ሳለ፣ ሌላ መልእክተኛ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “ወንዶችና ሴቶች ልጆችህ በታላቅ ወንድማቸው ቤት ተሰብስበው እየበሉና እየጠጡ ሳሉ፣ 19እነሆ፤ ታላቅ ዐውሎ ነፋስ ከምድረ በዳ መጣ፤ የቤቱንም አራት ማእዘናት መታ፤ እርሱም በልጆቹ ላይ ወድቆ ገደላቸው። እኔም ብቻዬን አመለጥሁ፤ ልነግርህም መጣሁ።” 20ኢዮብም ተነሣ፤ ልብሱን ቀደደ፤ ራሱን ተላጨ፤ በምድርም ላይ ተደፍቶ ሰገደ፤ 21እንዲህም አለ፤
“ዕራቍቴን ከእናቴ ማሕፀን ወጣሁ፤
ዕራቍቴንም እሄዳለሁ።#1፥21 ወይም ወደዚያ እመለሳለሁ
እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔር ነሣ፤
የእግዚአብሔር ስም ቡሩክ ይሁን።”
22በዚህ ሁሉ፣ ኢዮብ አልበደለም፤ በእግዚአብሔርም ላይ ክፉ አልተናገረም።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ አዲሱ መደበኛ ትርጕም™
የቅጅ መብት © 2001 በ Biblica, Inc.
ፈቃድ የተገኘባቸው ናቸው። መብቱ በመላው ዓለም በሕግ የተጠበቀ።
Holy Bible, New Amharic Standard Version™ (Addisu Medebegna Tirgum™)
Copyright © 2001 by Biblica, Inc.
Used with permission. All rights reserved worldwide.