መጽሐፈ ኢዮብ 1:1-12

መጽሐፈ ኢዮብ 1:1-12 አማ05

ዑፅ ተብላ በምትጠራ አገር ኢዮብ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ እርሱም ከክፉ ነገር ሁሉ ርቆ እግዚአብሔርን የሚፈራ፥ ምንም ነውር የሌለበት፥ ቅን ሰው ነበር። ሰባት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆችም ነበሩት። በሀብትም በኩል ሰባት ሺህ በጎች፥ ሦስት ሺህ ግመሎች፥ አምስት መቶ ጥማድ በሬዎችና አምስት መቶ አህዮች ነበሩት፤ እንዲሁም እጅግ ብዙ አገልጋዮች ነበሩት፤ በምሥራቅ አገር ካሉት ሰዎች ሁሉ እርሱን የሚያኽል ሀብታምና ታላቅ ሰው አልነበረም። የኢዮብ ወንዶች ልጆች በእያንዳንዳቸው ቤት በተራ ግብዣ እያዘጋጁ በአንድነት ተሰብስበው ይደሰቱ ነበር፤ ሦስቱንም እኅቶቻቸውን እያስጠሩ ከእነርሱ ጋር አብረው ይበሉና ይጠጡ ነበር። የግብዣዎቹ ቀኖች ከተፈጸሙ በኋላ ኢዮብ በማለዳ ተነሥቶ ልጆቹን ያስጠራና በእያንዳንዱ ልጁ ስም መሥዋዕት ያቀርብ ነበር፤ ይህንንም የሚያደርገው “ምናልባት ከልጆቼ አንዱ እግዚአብሔርን በመስደብ በድሎ ይሆናል!” በሚል ስጋት ልጆቹን ከኃጢአት ለማንጻት ነበር። ኢዮብ ይህን ሥርዓት ሳያቋርጥ ዘወትር ይፈጽም ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን የሰማይ መላእክት በእግዚአብሔር ፊት በቀረቡ ጊዜ ሰይጣንም አብሮአቸው ቀረበ። እግዚአብሔርም “ከወዴት መጣህ?” ብሎ ሰይጣንን ጠየቀው። ሰይጣንም “በምድር ዙሪያ ወዲያና ወዲህ እመላለስ ነበር” አለ። እግዚአብሔር ሰይጣንን “አገልጋዬን ኢዮብን ልብ ብለህ አየኸውን? እርሱን የመሰለ ታማኝና ደግ ሰው በምድር ላይ አይገኝም፤ እርሱ ከክፋት ሁሉ ርቆ እኔን የሚፈራ ቀጥተኛ ሰው ነው” አለ። ሰይጣንም እንዲህ አለ፦ “ኢዮብ አንተን እግዚአብሔርን የሚፈራ ያለ ምክንያት ነውን? እርሱ አንተን የሚፈራህ እርሱንና ልጆቹን፥ ያለውንም ንብረት ሁሉ በደኅና ስለ ጠበቅህለት፥ የሚሠራውንም ሁሉ ስለ ባረክህለትና ብዙ የከብት መንጋ ስለ ሰጠኸው አይደለምን? ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ብታጠፋበት ፊት ለፊት ይሰድብሃል።” እግዚአብሔርም ሰይጣንን “እሺ፤ እንግዲያውስ በኢዮብ ላይ ብቻ አንዳች ጒዳት አታድርስበት እንጂ ባለው ሀብት ሁሉ ላይ የፈለግኸውን ማድረግ ትችላለህ” አለው። ከዚህ በኋላ ሰይጣን ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ ሄደ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}