ትንቢተ ኤርምያስ 7
7
1ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው። 2በእግዚአብሔር ቤት በር ቁም፥ ይህንም ቃል እንዲህ ብለህ ተናገር፦ እግዚአብሔርን ልታመልኩ በእነዚህ በሮች የምትገቡ ከይሁዳ ያላችሁ ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ። 3የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ መንገዳችሁንና ሥራችሁን አሳምሩ በዚህም ስፍራ አሳድራችኋለሁ። 4የእግዚአብሔር መቅደስ፥ የእግዚአብሔር መቅደስ፥ የእግዚአብሔር መቅደስ ይህ ነው እያላችሁ በሐሰት ቃል አትታመኑ። 5መንገዳችሁንና ሥራችሁን ፈጽማችሁ ብታሳምሩ፥ በሰውና በጎረቤቱ መካከል ቅን ፍርድ ብትፈርዱ፥ 6መጻተኛውንና ድሀ አደጉን መበለቲቱንም ባትገፉ፥ በዚህም ስፍራ ንጹሕ ደምን ባታፈስሱ፥ ክፉም ሊሆንባችሁ እንግዶችን አማልክት ባትከተሉ፥ 7ከዘላለም እስከ ዘላለም ለአባቶቻችሁ በሰጠኋቸው ምድር በዚህ ስፍራ አሳድራችኋለሁ።
8እነሆ፥ በማትረቡበት በሐሰት ቃል ታምናችኋል። 9ትሰርቃላችሁ፥ ትገድላላችሁ፥ ታመነዝራላችሁ፥ በሐሰትም ትምላላችሁ፥ ለበኣልም ታጥናላችሁ፥ የማታውቋቸውንም እንግዶች አማልክት ትከተላላችሁ፥ 10መጣችሁም፥ ስሜም በተጠራበት በዚህ ቤት በፊቴ ቆማችሁ፦ ይህን አስጸያፊ የሆነ ነገርን ሁሉ አላደረግንም አላችሁ። 11ይህስ ስሜ የተጠራበት ቤት በዓይናችሁ የሌቦች ዋሻ ሆኖአልን? እነሆ፥ እኔ አይቻለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።
12ነገር ግን በቀድሞ ዘመን ስሜን ወዳሳደርሁበት በሴሎ ወደ ነበረው ስፍራዬ ሂዱ፥ ከሕዝቤም ከእስራኤል ክፋት የተነሣ ያደረግሁበትን እዩ። 13አሁንም ይህን ነገር ሁሉ ስላደረጋችሁ፥ በማለዳም ተነሥቼ በተናገርኋችሁ ጊዜ ስላልሰማችሁ፥ በጠራኋችሁም ጊዜ ስላልመለሳችሁ፥ 14ስለዚህ በሴሎ እንዳደረግሁ እንዲሁ ስሜ በተጠራበት በምትታመኑበት ቤት ለእናንተና ለአባቶቻችሁም በሰጠኋችሁ ስፍራ አደርጋለሁ። 15የኤፍሬምንም ዘር ሁሉ፥ ወንድሞቻችሁን ሁሉ እንደ ጣልሁ፥ እንዲሁ ከፊቴ እጥላችኋለሁ።
16እንግዲህም አልሰማህምና ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ ስለ እነርሱም ልመናና ጸሎት አታድርግ፥ አትማልድላቸው። 17እነርሱስ በይሁዳ ከተሞች ውስጥና በኢየሩሳሌም አደባባይ ላይ የሚያደርጉትን አታይምን? 18ያስቈጡኝ ዘንድ፥ ለሰማይ ንግሥት እንጐቻ እንዲያደርጉ ለሌሎችም አማልክት የመጠጥ ቍርባን እንዲያፈስሱ ልጆች እንጨት ይሰበስባሉ፥ አባቶችም እሳት ያነድዳሉ፥ ሴቶችም ዱቄት ይለውሳሉ። 19እኔን ያስቈጣሉን? ይላል እግዚአብሔር፥ ለፊታቸውስ እፍረት አይደለምን? 20እንግዲህም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ ቍጣዬና መዓቴ በዚህ ስፍራ ላይ፥ በሰውና በእንስሳ ላይ፥ በዱር ዛፎችና በምድር ፍሬ ላይ ይፈስሳል፥ ይነድዳል፥ አይጠፋምም።
21እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ለሌላ መሥዋዕታችሁ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁን ጨምሩ፥ ሥጋውንም ብሉ። 22ከግብጽ ምድር ባወጣኋችሁ ቀን ስለሚቃጠል መሥዋዕትና ስለ ሌላ መሥዋዕት ለአባቶቻችሁ አልተናገርሁምና፥ አላዘዝኋቸውምም። 23ነገር ግን፦ ቃሌን ስሙ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ እናንተም ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፥ መልካምም ይሆንላችሁ ዘንድ ባዘዝኋችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ ብዬ በዚህ ነገር አዘዝኋቸው። 24ነገር ግን በክፉ ልባቸው አሳብና እልከኝነት ሄዱ ወደ ፊትም ሳይሆን ወደ ኋላቸው ሄዱ እንጂ አልሰሙም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም። 25አባቶቻችሁ ከግብጽ ምድር ከወጡበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በየዕለቱ እየማለድሁ ባሪያዎቼን ነቢያትን ሁሉ ልኬባችሁ ነበር። 26ነገር ግን አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙኝም ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም፥ አባቶቻቸውም ካደረጉት ይልቅ የባሰ አደረጉ።
27በዚህም ቃል ሁሉ ትነግራቸዋለህ፥ ነገር ግን አይሰሙህም፥ ትጠራቸውማለህ፥ ነገር ግን አይመልሱልህም። 28አንተም፦ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቃል ያልሰማ፥ ተግሣጽንም ያልተቀበለ ሕዝብ ይህ ነው፥ እውነት ጠፍቶአል ከአፋቸውም ተቈርጦአል ትላቸዋለህ።
29እግዚአብሔር የቍጣውን ትውልድ ጥሎአልና፥ ትቶታልምና ጠጕርሽን ቍረጪ፥ ጣዪውም፥ በወናዎች ኮረብቶችም ላይ አሙሺ። 30የይሁዳ ልጆች በፊቴ ክፉን ነገር ሠርተዋል፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ያረክሱትም ዘንድ ስሜ በተጠራበት ቤት ርኵሰታቸውን አኑረዋል። 31እኔም ያላዘዝሁትንና በልቤ ያላሰብሁትን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ዘንድ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ያለችውን የቶፌትን መስገጃዎች ሠረተዋል። 32ስለዚህ፥ እነሆ፥ ስፍራ ከማጣት የተነሣ በቶፌት ይቀበራሉና የእርድ ሸለቆ ይባላል እንጂ ቶፌት ወይም የሄኖም ልጅ ሸለቆ ዳግመኛ የማይባልበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል እግዚአብሔር። 33የዚህም ሕዝብ ሬሳ ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት መብል ይሆናል፥ የሚያስፈራራቸውም የለም። 34ምድሪቱም ባድማ ትሆናለችና ከይሁዳ ከተሞችና ከኢየሩሳሌም አደባባይ የእልልታን ድምፅና የደስታን ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራን ድምፅና የሴት ሙሽራን ድምፅ አጠፋለሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 7: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ