ትንቢተ ኤርምያስ 8
8
1በዚያን ዘመን፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የይሁዳን ነገሥታት አጥንትና የመኳንንቶቹን አጥንት፥ የካህናቱን አጥንትና የነቢያቱን አጥንት፥ የኢየሩሳሌምንም ሰዎች አጥንት ከመቃብራቸው ያወጣሉ። 2በወደዱአቸውና ባመለኩአቸው፥ በተከተሉአቸውና በፈለጉአቸው፥ በሰገዱላቸውም በፀሐይና በጨረቃ በሰማይም ሠራዊት ሁሉ ፊት ይዘረጉአቸዋል፥ አያከማቹአቸውም አይቀብሩአቸውምም፥ በምድርም ፊት ላይ እንደ ጕድፍ ይሆናሉ። 3እኔም ባሳደድኋቸው ስፍራ ሁሉ የቀሩ፥ ከዚህች ክፉ ወገን የተረፉ ቅሬታዎች ሁሉ፥ ከሕይወት ይልቅ ሞትን ይመርጣሉ።
4እንዲህም ትላቸዋለሁ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የወደቁ አይነሡምን? የሳተስ አይመለስምን? 5እንግዲህ ይህ የኢየሩሳሌም ሕዝብ ዘወትር ስለ ምን ወደ ኋላው ይመለሳል? ተንኰልን ይዞአል ሊመለስም እንቢ ብሎአል። 6አደመጥሁ ሰማሁም፥ ቅንን ነገር አልተናገሩም፥ ማናቸውንም፦ ምን አድርጌአለሁ? ብሎ ከክፋቱ ንስሐ የገባ የለም፥ ወደ ሰልፍም እንደሚሮጥ ፈረስ እያንዳንዱ በየመንገዱ ይሄዳል። 7ሽመላ በሰማይ ጊዜዋን አውቃለች፥ ዋኖስና ጨረባ ዋልያም የመምጣታቸውን ጊዜ ይጠብቃሉ፥ ሕዝቤ ግን የእግዚአብሔርን ፍርድ አላወቁም።
8እናንተስ፦ ጥበበኞች ነን የእግዚአብሔርም ሕግ ከእኛ ጋር ነው እንዴት ትላላችሁ? እነሆ፥ የጸሐፊ ብርዕ ሐሰተኛ ነው በሐሰትም አድርጎአል። 9ጥበበኞች አፍረዋል ደንግጠውማል ተማርከውማል፥ እነሆ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ጥለዋል፥ ምን ዓይነት ጥበብ አላቸው? 10ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሁሉ ስስትን ያስባሉና፥ ከነቢዩም ጀምሮ እስከ ካህኑ ድረስ ሁሉ በተንኰል ያደርጋሉና ስለዚህ ሚስቶቻቸውን ለሌሎች፥ እርሻቸውንም ለሚወርሱባቸው እሰጣለሁ። 11የሕዝቤንም ሴት ልጅ ስብራት በጥቂቱ ይፈውሳሉ፥ ሰላም ሳይሆን፦ ስለም ሰላም ይላሉ። 12አስጸያፊ ነገርን ስለ ሠሩ አፍረዋልን? ምንም አላፈሩም፥ እፍረትንም አላወቁም፥ ስለዚህ ከሚወድቁ ጋር ይወድቃሉ፥ በጐበኘኋቸው ጊዜ ይዋረዳሉ፥ ይላል እግዚአብሔር። 13ፈጽሜ አጠፋችኋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በወይን ላይ ፍሬ፥ በበለስ ዛፍ ላይ በለስ አይሆንም፥ ቅጠልም ይረግፋል፥ የሚያልፉባቸውንም ሰጠኋቸው።
14ዝም ብለን ለምን እንቀመጣለን? እግዚአብሔርን ስለ በደልን አምላካችን እግዚአብሔር አጥፍቶናልና፥ የሐሞትንም ውኃ አጠጥቶናልና ተሰብስባችሁ ወደ ተመሸጉ ከተሞች እንግባ በዚያም እንጥፋ።። 15ሰላምን በተስፋ ተጠባበቅን፥ መልካምም አልተገኘም፥ መጠገንን በተስፋ ተጠባበቅን፥ እነሆም፥ ድንጋጤ ሆነ። 16የፈረሰኞቹ ድምጽ ከዳን ተሰማ፥ ከአርበኞች ፈረሶች ማሽካካት የተነሣ ምድር ሁሉ ተንቀጠቀጠች፥ መጡም ምድሪቱንና በእርስዋም ያለውን ሁሉ፥ ከተማይቱንና የተቀመጡባትንም በሉ። 17እነሆ፥ አስማት የማይከለክላቸውን እባቦችንና እፉኝቶችን እሰድድባችኋለሁ፥ እነርሱም ይነድፉአችኋል።
18ኀዘኔ የማይጽናና ነው፥ ልቤም በውስጤ ደክሞአል። 19እነሆ፦ እግዚአብሔር በጽዮን የለምን? ወይስ ንጉሥዋ በእርስዋ ዘንድ የለምን? የሚል የወገኔ ሴት ልጅ ጩኸት ድምፅ ከሩቅ አገር ተሰማ። በተቀረጹ ምስሎቻቸውና በባዕድ ከንቱነትስ ያስቈጡኝ ስለ ምንድር ነው? 20መከሩ አልፎአል፥ በጋው ሄዶአል፥ እኛም አልዳንነም። 21በሕዝቤ ሴት ልጅ ስብራት እኔ ተሰብሬአለሁ ጠቍሬማለሁ፥ አድናቆትም ይዞኛል። 22በገለዓድ የሚቀባ መድኃኒት የለምን? ወይስ በዚያ ሐኪም የለምን? የወገኔ ሴት ልጅ ፈውስ ስለ ምን አልሆነም?
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 8: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ