በሰው ዘንድ፦ ሰው ሚስቱን ቢፈታ፥ ከእርሱም ዘንድ ሄዳ ሌላ ወንድ ብታገባ፥ በውኑ ደግሞ ወደ እርሱ ትመለሳለችን? ያች ሴት እጅግ የረከሰች አይደለችምን? ይባላል። አንቺ ከብዙ ውሽሞች ጋር አመንዝረሻል፥ ወደ እኔም ትመለሻለሽን? ይላል እግዚአብሔር። ዓይንሽን አንሥተሽ ወደ ወናዎች ኮረብቶች ተመልከቺ፥ ያልተጋደምሽበት ስፍራ ወዴት አለ? ዓረባዊ በምድረ በዳ እንደሚቀመጥ አንቺ በመንገድ ላይ ተቀምጠሽ ትጠብቂያቸው ነበር፥ በግልሙትናሽና በኃጢአትሽ ምድሪቱን አረከስሽ። ስለዚህ ካፊያ ተከለከለ፥ የኋለኛውም ዝናብ ጠፋ፥ የጋለሞታም ሴት ፊት ነበረብሽ፥ ታፍሪም ዘንድ እንቢ ብለሻል። አሁንም፦ አንተ አባቴ ሆይ፥ የብላቴንነቴ ወዳጅ ነህ ብለሽ አልጮኽሽልኝምን? ለዘላለም ይቈጣልን? እስከ ፍጻሜስ ድረስ ይጠብቀዋልን? እነሆ፥ እንዲህ ብለሽ ተናገርሽ፥ እንደ ተቻለሽም መጠን ክፉን ነገር አደረግሽ። እግዚአብሔርም በንጉሡ በኢዮስያስ ዘመን እንዲህ አለኝ፦ ከዳተኛይቱ እስራኤል ያደረገችውን አየህን? ወደ ረዘመው ተራራ ሁሉ ከለመለመ ዛፍም ሁሉ በታች ሄደች በዚያም ጋለሞተች። ይህንም ሁሉ ካደረገች በኋላ፦ ወደ እኔ ትመለሳለች ብዬ ነበር፥ ነገር ግን አልተመለሰችም፥ አታላይ እኅትዋም ይሁዳ አየች። ከዳተኛይቱም እስራኤል ስላመነዘረች ስለዚህ ፈትቻታለሁ የፍችዋንም ወረቀት ሰጥቻታለሁ፥ አታላይ እኅትዋ ይሁዳ ግን እንዳልፈራች እርስዋም ደግሞ ሄዳ እንደ ጋለሞተች አየሁ። በግልሙትናዋም በመቅለልዋም ምድሪቱ ረከሰች፥ እርስዋም ከድንጋይና ከግንድ ጋር አመነዘረች። በዚህም ሁሉ አታላይቱ ይሁዳ በሐሰት እንጂ በፍጹም ልብዋ ወደ እኔ አልተመለሰችም። እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ ከአታላይቱ ከይሁዳ ይልቅ ከዳተኛይቱ እስራኤል ጸደቀች። ሂድና ይህን ቃል ወደ ሰሜን ተናገር፥ እንዲህም በል፦ ከዳተኛይቱ እስራኤል ሆይ፥ ተመለሽ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ መሐሪ ነኝና፥ ለዘላለምም አልቈጣምና በእናንተ ላይ ፊቴን አላደርግም፥ ይላል እግዚአብሔር። በአምላክሽ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፅሽ፥ መንገድሽንም ከለመለመ ዛፍ ሁሉ በታች ለእንግዶች እንደ ዘረጋሽ፥ ቃሌንም እንዳልሰማሽ ኃጢአትሽን ብቻ እወቂ ይላል እግዚአብሔር። ከዳተኞች ልጆች ሆይ፥ እኔ ባላችሁ ነኝና ተመለሱ ይላል እግዚአብሔር፥ አንዱንም ከአንዲት ከተማ ሁለቱንም ከአንድ ወገን እወስዳችኋለሁ፥ ወደ ጽዮንም አመጣችኋለሁ፥ እንደ ልቤም በግ ጠባቆችን እሰጣችኋለሁ፥ በእውቀትና በማስተዋልም ይጠብቁአችኋል። በበዛችሁም ጊዜ በምድርም ላይ በረባችሁ ጊዜ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በዚያ ዘመን፦ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ብለው ከእንግዲህ ወዲህ አይጠሩም፥ ልብ አያደርጉትም፥ አያስቡትምም፥ አይሹትምም፥ ከእንግዲህ ወዲህም አይደረግም። በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን የእግዚአብሔር ዙፋን ብለው ይጠሩአታል፥ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርስዋ ይሰበሰባሉ፥ ከእንግዲህም ወዲህ ክፉውን እልከኛ ልባቸውን ተከትለው አይሄዱም። በዚያም ዘመን የይሁዳ ቤት ወደ እስራኤል ቤት ይሄዳል፥ በአንድም ሆነው ከሰሜን ምድር ርስት አድርጌ ለአባቶቻቸው ወደ ሰጠኋት ምድር ይመጣሉ።
ትንቢተ ኤርምያስ 3 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኤርምያስ 3:1-18
10 ቀናት
"ሰዎች በትዳር ላይ የተለያየ አመለካከት አላቸው። አንዳንዶች ኋላ ቀር ሀሳብ አድርገው ይመለከቱታል፤ ሌሎች ደግሞ ጥልቅ የሆነ የፍቅር ስሜት ነው ብለው ይገልጹታል፤ ሌሎች ደግሞ በትዳር ጓደኛቸው ታማኝ አለመሆን ወይም በወላጆቻቸው መፋታት ጉዳት የደረሰባቸው ከሆኑ ለትዳር ያላቸው አመለካከት መልካምነት የሌለው ይሆናል። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ሁሉ አስተያየቶች ወይም ልምምዶች በላይ የእግዚአብሔር ቃል ስለ ጋብቻ ብዙ የሚናገረው ነገር አለው። በዚህ የንባብ እቅድ ውስጥ እግዚአብሔር ስለ ጋብቻ ያለው አመለካከት ምን እንደሆነ መረዳት ትችላለህ።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች