ትንቢተ ኤርምያስ 10:1-13

ትንቢተ ኤርምያስ 10:1-13 አማ54

እናንተ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ እግዚአብሔር በእናንተ ላይ የተናገረውን ቃል ስሙ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአሕዛብን መንገድ አትማሩ ከሰማይ ምልክትም አትፍሩ፥ አሕዛብ ይፈሩታልና። የአሕዛብ ልማድ ከንቱ ነውና፥ ዛፍ ከዱር ይቈረጣል፥ በሠራተኛም እንጅ በመጥረቢያ ይሠራል። በብርና በወርቅ ያስጌጡታል፥ እንዳይናወጥም በችንካርና በመዶሻ ይቸነክሩታል። እንደ ተቀረጸ ዓምድ ናቸው እነርሱም አይናገሩም፥ መራመድም አይቻላቸውምና ይሸከሙአቸዋል። ክፉ መሥራትም አይቻላቸውምና፥ ደግምም መልካም ይሠሩ ዘንድ አይችሉምና አትፍሩአቸው። አቤቱ፥ እንደ አንተ ያለ የለም፥ አንተ ታላቅ ነህ ስምህም በኃይል ታላቅ ነው። የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ፥ በአሕዛብ ጥበበኞች ሁሉ መካከል በመንግሥታቸውም ሁሉ እንደ አንተ ያለ ስለሌለ፥ አንተን መፍራት ይገባልና አንተን የማይፈራ ማን ነው? በአንድ ጊዜ ሰንፈዋል፥ ደንቍረውማል፥ ጣዖታት የሚያስተምሩት የእንጨት ነገር ብቻ ነው። የሠራተኛና የአንጥረኛ እጅ ሥራ የሆነ ከተርሴስ ጥፍጥፍ ብር ከአፌዝም ወርቅ ይመጣል፥ ልብሳቸውም ሰማያዊና ቀይ ግምጃ ነው፥ ሁሉም የብልሃተኞች ሥራ ናቸው። እግዚአብሔር ግን እውነተኛ አምላክ ነው፥ እርሱም ሕያው አምላክና የዘላለም ንጉሥ ነው፥ ከቍጣው የተነሣ ምድር ትንቀጠቀጣለች፥ አሕዛብም መዓቱን አይችሉም። እናንተም፦ ሰማይንና ምድርን ያልፈጠሩ እነዚህ አማልክት ከምድር ላይ ከሰማይም በታች ይጠፋሉ ትሉአቸዋላችሁ። ምድርን በኃይሉ የፈጠረ፥ ዓለሙን በጥበቡ የመሠረተ ሰማያትንም በማስተዋሉ የዘረጋ እርሱ ነው። ድምፁን ባሰማ ጊዜ ውኆች በሰማይ ይሰበሰባሉ፥ ከምድርም ዳር ደመናትን ከፍ ያደርጋል፥ ለዝናቡም መብረቅን ያደርጋል፥ ነፋስንም ከቤተ መዛግብቱ ያወጣል።