ትንቢተ ኤርምያስ 10:1-13

ትንቢተ ኤርምያስ 10:1-13 አማ05

የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እነሆ እግዚአብሔር የሚነግራችሁን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የአሕዛብን አካሄድ አትከተሉ፤ መቼም አሕዛብ ያልተለመደ አዲስ ነገር በሰማይ ባዩ ጊዜ በፍርሃት መንቀጥቀጥ ልማዳቸው ነው፤ እናንተ ግን በዚህ አትሸበሩ። የአሕዛብ ልማዳዊ እምነት ከንቱ ነው፤ ዛፍ ከደን ይቈረጣል፤ አናጢ በመሮ ቅርጽ ያወጣለታል፤ በብርና በወርቅ ያስጌጡታል፤ እንዳይወድቅም በምስማር ያጠብቁታል። እንደነዚህ ያሉት ምስሎች በዱባ ተክል ውስጥ ለወፍ ማስፈራሪያ እንደሚተከሉ ነገሮች ናቸው፤ መናገር አይችሉም፤ መራመድ ስለማይችሉ ሰዎች ይሸከሙአቸዋል፤ ጒዳት ማድረስም ሆነ ጥቅም ማስገኘት ስለማይችሉ፥ ፈጽሞ አትፍሩአቸው።” እግዚአብሔር ሆይ! አንተን የሚመስል ማንም የለም፤ አንተ ኀያል ነህ፤ ስምህም ታላቅና አስፈሪ ነው። የመንግሥታት ሁሉ ንጉሥ ስለ ሆንክ አንተን የማይፈራ ማን ነው? በአሕዛብ ጠቢባንም ሆነ በንጉሦቻቸው መካከል አንተን የሚመስል ስለሌለ ክብር ይገባሃል። ሁሉም ሞኞችና አላዋቂዎች ሆነው ነው እንጂ ከእንጨት ከተሠሩ ምስሎች ከቶ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? ምስሎቻቸው ከተርሴስ በመጣ ጥሬ ብርና ከኡፋዝ በተገኘ ወርቅ ተለብጠዋል፤ በብልኀተኞችም ሥራ አጊጠዋል፤ ጥበበኞች ሸማኔዎች በሠሩአቸውም የወይን ጠጅና ሐምራዊ ልብስ ተሸፍነዋል። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ግን እውነተኛ አምላክ ነህ፤ አንተ ሕያው አምላክ፥ ዘለዓለማዊ ንጉሥ ነህ፤ አንተ በምትቈጣበት ጊዜ ዓለም ይናወጣል፤ የአሕዛብ መንግሥታትም የአንተን ቊጣ ችለው አይቆሙም። “ጣዖቶች ሰማይንና ምድርን ያልፈጠሩ መሆናቸውንና አንተ እግዚአብሔር ጣዖቶችን ሁሉ እንደምትደመስስ ንገራቸው” አልከኝ። እግዚአብሔር በኀይሉ ምድርን ሠራ፤ በጥበቡም ዓለምን ፈጠረ፤ በማስተዋሉም ሰማያትን ዘረጋ፤ በእርሱ ትእዛዝ ከሰማይ በላይ ያሉ ውሃዎች የመናወጥ ድምፅ ያሰማሉ፤ እርሱ ደመናዎችን ከምድር ዳርቻ ያመጣል፤ በዝናብ ጊዜም መብረቅ እንዲበርቅ ያደርጋል፤ ነፋስንም ከማከማቻው ይልካል።