ኦሪት ዘፍጥረት 40:1-15

ኦሪት ዘፍጥረት 40:1-15 አማ54

ከዚህ ነገር በኍላም እንዲህ ሆነ የግብፅ ንጉሥ የጠጅ አሳላፊና የእንጀራ አበዛ ጌታቸውን የግብፅ ንጉሥን በደሉ። ፈርዖንም በሁለቱ ሹማምቱ በጠጅ አሳላፊዎቹ አለቃና በእንጀራ አበዛዎቹ አለቃ ላይ ተቆጣ፤ ዮሴፍ ታሰሮ በነበረበትም በግዛት ስፍራ በዘበኞቹ አለቃ ቤት አስጠበቃቸው። የዘበኞቹም አለቃ ለዮሴፍ አሳልፎ ሰጣቸው እርሱም ያገልግላቸው ነበር በግዞት ቤትም አያሌ ቀን ተቀመጡ። በግዞት ቤት የነበሩት የግብፅ ንጉሥ ጠጅ አሳላፊና እንጀራ አበዛ ሁለቱም በአንዲት ሌሊት እንደ ሕልሙ ትርጓሜ እየራሳቸው ሕልምን አለሙ። ዮሴፍም ማልዶ ወደ እነርሱ ገባ እነሆም አዝነው አያቸው። በጌታው ቤት ከእርሱ ጋር በግዞት የነበሩትንም የፈርዖንን ሹማምት እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው፦ እናንተ ዛሬ ስለ ምን አዝናችኍል? እነርሱም፦ ሕልምን አልመን የሚተረጕምልን አጣን አሉት ዮሴፍም አላቸው፦ ሕልምን የሚተረጕም እግዚአብሔር የሰጠው አይደለምን? እስቲ ንገሩኝ። የጠጅ አሳላፊዎች አለቃም ለዮሴፍ ሕልሙን እንዲህ ብሎ ነገረው፦ በሕልሜ የወይን ዛፍ በፊቴ ሆና አየሁ በዛፊቱም ሦስት አረግ አለበት እርስዋም ቅጠልን አበባ አወጣች፥ ዘለላም አንጠለጠለች፥ የዘለላዋም ፍሬ በሰለ የፈርዖን፥ ጽዋ በእጄ ነበረ ፍሬውንም ወስጄ በፈርዖን ጽዋ ጨመቅሁት ጽዋውንም ለፈርዖን በእጁ ሰጠሁት። ዮሴፍም አለው፦ የዚህ ትርጓሜው ይህ ነው፤ ሦስት አረግ ሦስት ቀን ነው እስከ ሦስት ቀን ድረስ ፈርዖን ራስህን ከፍ ያደርጋል፥ ወደ ቀደመው ሹመትህም ይመልስሃል ጠጅ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ስታድርግ እንደ ነበረው እንደ ቀድሞው ሥርዓትም የፈርዓንን ጽዋ በእጁ ትሰጣለህ። ነገር ግን በጎ ነገር በተደረግልህ ጊዜ እኔን አስበኝ ምሕረትንም አድርግልኝ የእኔንም ነገር ለፈርዖን ነግረህ ከዚህ ቤት አውጣኝ፤ እኔን ከዕብራውያን አገር ሰርቀው አምጥተውኛልና ከዚህም ደግሞ በግዞት ያኖሩኝ ዘንድ ምንም አላደረግሁም።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}