ከዚህም በኋላ የግብጽ ንጉሥ የመጠጥ አሳላፊና እንጀራ ቤቱ ጌታቸውን የግብጽን ንጉሥ በደሉት። ፈርዖንም በመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃና በእንጀራ ቤቱ አዛዥ፣ በሁለቱም ሹማምቱ ላይ ክፉኛ ተቈጣ፤ በዘበኞቹ አለቃ ቤት ወዳለው ዮሴፍ ወደ ተጋዘበትም እስር ቤት አስገባቸው። የዘበኞቹም አለቃ እስረኞቹን ለዮሴፍ አስረከባቸው፤ ዮሴፍም በሚያስፈልጋቸው ይረዳቸው ነበር። እስር ቤት ገብተው ጥቂት እንደ ቈዩም፣ ታስረው የነበሩት የግብጽ የንጉሥ የመጠጥ አሳላፊዎች አለቃና የእንጀራ ቤቱ አዛዥ፣ በአንድ ሌሊት የየራሳቸውን ሕልም አዩ፤ የሁለቱም ሕልም ለየራሱ የተለየ ፍች ነበረው። በማግስቱም ጧት ዮሴፍ ወደ እነርሱ ሲገባ ተክዘው አገኛቸው። ስለዚህም፣ “ምነው ዛሬስ ፊታችሁ ላይ ሐዘን ይነበባል?” በማለት ዐብረውት በጌታው ግቢ የታሰሩትን የፈርዖን ሹማምት ጠየቃቸው። እነርሱም “ሁለታችንም ሕልም አየን፤ ነገር ግን የሚተረጕምልን ሰው አጣን” ሲሉ መለሱለት። ዮሴፍም፣ “ሁልጊዜስ ቢሆን የሕልም ትርጓሜ ከእግዚአብሔር የሚገኝ አይደለምን? እስኪ ያያችሁትን ሕልም ንገሩኝ” አላቸው። ስለዚህ የመጠጥ አሳላፊዎቹ አለቃ እንዲህ ሲል ሕልሙን ለዮሴፍ ነገረው፤ “ከፊት ለፊቴ አንዲት የወይን ተክል አየሁ፤ ተክሏም ሦስት ሐረጎች ነበሯት፤ ወዲያው አቈጥቍጣ አበበች፤ ዘለላዎቿም ተንዠርግገው በሰሉ። የፈርዖንንም ጽዋ ይዤ ነበረ፤ የወይኑን ፍሬ ለቅሜ በጽዋው ውስጥ ጨምቄ ጽዋውን በእጁ ሰጠሁት።” ዮሴፍም እንዲህ አለው፤ “እንግዲህ የሕልሙ ትርጓሜ ይህ ነው፤ ሦስቱ ሐረግ ሦስት ቀን ነው፤ በሦስት ቀን ውስጥ ፈርዖን ከእስር ቤት ያወጣሃል፣ ወደ ቀድሞ ሹመትህም ይመልስሃል፤ በፊት የመጠጥ አሳላፊ በነበርህበት ጊዜ ታደርግ እንደ ነበረው ሁሉ የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጣለህ። እንግዲህ፣ በጎ ነገር በገጠመህ ጊዜ፣ እኔን ዐስበህ ቸርነት አድርግልኝ፤ ስለ እኔም ለፈርዖን ንገርልኝ፤ ከዚህም እስር ቤት አስወጣኝ፤ ከዕብራውያን ምድር ወደዚህ የመጣሁት በዐፈና ነው፤ አሁንም ቢሆን እዚህ እስር ቤት የተጣልሁት አንዳች ጥፋት ኖሮብኝ አይደለም።”
ዘፍጥረት 40 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 40
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 40:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች