ኦሪት ዘፍጥረት 40:1-15

ኦሪት ዘፍጥረት 40:1-15 አማ05

ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን የወይን ጠጅ አሳላፊና የእንጀራ ቤት ኀላፊ ንጉሡን የሚያሳዝን በደል ፈጸሙ። ፈርዖን በወይን ጠጅ አሳላፊውና በእንጀራ ቤት ኀላፊው እጅግ ተቈጣ። ስለዚህ ዮሴፍ ታስሮ ወደሚገኝበት ወደ ዘበኞች አለቃ ቤት ተወስደው እንዲታሰሩ አደረገ። የእስር ቤቱም አዛዥ ለዮሴፍ አስረከባቸው፤ ዮሴፍም ያገለግላቸው ነበር። በእስር ቤትም ለጥቂት ጊዜ ቈዩ። የንጉሡ የወይን ጠጅ አሳላፊና የእንጀራ ቤት ኀላፊ ሁለቱም በእስር ቤት ሳሉ በአንድ ሌሊት ሕልም አዩ፤ የእያንዳንዳቸው ሕልም የተለያየ ትርጒም ነበረው። በማግስቱ ጠዋት ዮሴፍ እነርሱ ወዳሉበት ክፍል በገባ ጊዜ ተክዘው አገኛቸውና፥ “ዛሬ በፊታችሁ ላይ ሐዘን የሚታየው ለምንድን ነው?” አላቸው። እነርሱም “እያንዳንዳችን ሕልም አየን፤ ነገር ግን የእያንዳንዳችንን ሕልም የሚተረጒም ማንም የለም” አሉት። ዮሴፍም “ሕልም የመተርጐም ችሎታ የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ የእያንዳንዳችሁን ሕልም ንገሩኝ” አላቸው። የወይን ጠጅ አሳላፊው እንዲህ በማለት ሕልሙን ተናገረ፤ “በሕልሜ አንድ የወይን ተክል አየሁ፤ በተክሉም ላይ ሦስት ሐረጎች ነበሩ፤ ቅጠሉ ለምልሞ ወዲያው አበባ አወጣ፤ የወይን ዘለላውም ወዲያው በሰለ፤ የፈርዖን ጽዋ በእጄ ነበረ፤ የወይኑን ፍሬ ወስጄ በጽዋው ውስጥ ጨመኩና ጽዋውን ለፈርዖን ሰጠሁት።” ዮሴፍም እንዲህ አለ፤ “የሕልሙ ትርጕም ይህ ነው፤ ሦስቱ የወይን ሐረጎች ሦስት ቀኖች ናቸው፤ በሦስት ቀን ጊዜ ውስጥ ንጉሡ ከእስራት ይፈታሃል፤ በደልህንም ይቅር ብሎ ወደ ቀድሞው ማዕርግህ ይመልስሃል፤ ቀድሞ የመጠጥ ቤት ኀላፊ ሆነህ ታደርገው እንደ ነበር የፈርዖንን ጽዋ በእጁ ትሰጠዋለህ። ነገር ግን ሁሉ ነገር በተቃናልህ ጊዜ እኔን አስታውሰህ እርዳኝ፤ ለፈርዖንም አሳስበህ ከእዚህ ከእስር ቤት እንድወጣ አድርገኝ። እኔ ከዕብራውያን አገር ወደዚህ የመጣሁት ወድጄ ሳይሆን ተሸጬ ነው፤ እዚህም አገር ከመጣሁ ወዲህ በእስር ቤት የምገኘው ምንም በደል ሳልፈጽም ነው።”

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}