ከዚህ ነገር በኍላም የእግዚአብሔር ቃል በራእይ ወደ አብራም መጣ፥ እንዲህ ሲል፤ አብራም ሆይ፥ አትፍራ፤ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤ ዋጋህም እጅግ ታላቅ ነው። አብራምም፤ አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ፥ ምንን ትሰጠኛለህ? እኔም ያለ ልጅ እሄዳለሁ፤ የቤቴም መጋቢ የደማስቆ ሰው ይህ ኤሊዔዘር ነው አለ። አብራምም ለእኔ ዘር አልሰጠኸኝም፤ እነሆም፥ በቤቴ የተወለደ ሰው ይወርስኛል አለ። እነሆም፥ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል መጣለት፥ ይህ አይወርስህም፤ ነገር ግን ከጉልበትህ የሚወጣው ይወርስሃል። ወደ ሜዳም አወጣውና፥ ወደ ሰማይ ተመልከት፥ ከዋክብትንም ልትቆጥራቸው ትችል እንደ ሆነ ቁጠርን አለው። ዘርህም እንደዚሁ ይሆናል አለው አብራምም በእግዚአብሔር አመነ፥ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት። ይህችን ምድር ትወርሳት ዘንድ እንድሰጥህ ከከለዳውያን ዑር ያወጣሁህ እግዚአሔር እኔ ነኝ አለው። አቤቱ እግዚአብሔር ሆይ እንድወርሳት በምን አውቃለሁ? አለ። እርሱም፥ የሦስት ዓመት ጊደር፥ የሦስት ዓመት ፍየልም፥ የሦስት በግም ዋኖስም ርግብም ያዝልኝ አለው። እነዚህንም ሁሉ ወሰደለት፥ በየሁለትም ከፈላቸው፥ የተከፈለትንም በየወገኑ ትይዩ አደረጋቸው ወፎችን ግን አልከፈለም። አሞራዎችም በሥጋው ላይ ወረዱ፥ አብራምም አበረራቸው። ፀሐይም በገባች ጊዜ በአብራም ከባድ እንቅልፍ መጣበት፤ እነሆም፥ ድንጋጤና ታላቅ ጨለማ ወደቀበት፤ አብራምንም አለው፤ ዘርህ ለእርሱ ባልሆነች ምድር ስደተኞች እንዲሆኑ በእርግጥ እወቅ ባሪያዎች አድርገውም አራት መቶ ዓመት ያስጨንቋቸዋል። ደግሞም በባርነት በገዙአቸው ሕዝብ ላይ እኔ እፈርዳለሁ ከዚያም በኍላ በብዙ ከብት ይወጣሉ። አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ በመልካም ሽምግልና ትቀበራለህ። በአራተኛው ትውልድ ግን ወደዚህ ይመለሳሉ የአሞራውያን ኃጢአት ገና አልተፈጸመምና። ፀሐይም በገባች ጊዜ ታላቅ ጨለማ ሆነ የምድጃ ጢስና የእሳት ነበልባል በዚያ በተከፈለው መካከል አለፈ። በዚያ ቀን እግዚአብሔር ለአብራም እንዲህ ብሎ ቃል ኪዳን አደረገ፤ ከግብፅ ወንዝ ጀምሮ እስከ ትልቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ይህችን ምድር ለዘርህ ሰጥቼአለሁ፤ ቄናውያንን፥ ቄኔዛውያንንም፥ ቀድሞንውያንንም፥ ኬጢያውይንንም ፌርዛውያንንም፥ ራፋይምንም፥ አሞራውያንንም፥ ከነዓናውያንንም ጌርጌሳውያንንም፥ ኢያቡሳውያንንም።
ኦሪት ዘፍጥረት 15 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 15:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos