ከዚህም በኋላ፣ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል እንዲህ ሲል በራእይ ወደ አብራም መጣ፤ “አብራም ሆይ፤ አትፍራ፤ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤ ታላቅ ዋጋህም እኔው ነኝ።” አብራምም፣ “እግዚአብሔር (አዶናይ ያህዌ) አምላክ ሆይ፤ ያለ ልጅ የቀረሁ ስለሆንሁ፣ የቤቴ ወራሽ የደማስቆ ሰው ኤሊዔዘር ነው፤ ታዲያ ምን ትሰጠኛለህ?” አለው። “አንተ ልጆች ስላልሰጠኸኝ፣ ከቤቴ አገልጋይ አንዱ ወራሼ መሆኑ አይቀርም።” በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል እንዲህ ሲል መጣለት፤ “ይህ ሰው ወራሽህ አይሆንም፤ ነገር ግን ከአብራክህ የሚከፈል ልጅ ወራሽህ ይሆናል።” ወደ ውጭም አውጥቶ፣ “ቀና ብለህ ወደ ሰማይ ተመልከት፤ እስቲ መቍጠር ከቻልህ፣ ከዋክብቱን ቍጠራቸው፤ ዘርህም እንዲሁ ይበዛል” አለው። አብራም እግዚአብሔርን (ያህዌ) አመነ፤ እርሱም ጽድቅ አድርጎ ቈጠረለት። ደግሞም እግዚአብሔር፣ “ይህችን ምድር ላወርስህ፣ ከከለዳውያን ምድር፣ ከዑር ያወጣሁህ እግዚአብሔር (ያህዌ) እኔ ነኝ” አለው። አብራምም፣ “እግዚአብሔር (አዶናይ ያህዌ) አምላክ ሆይ፤ ይህችን ምድር እንደምወርሳት በምን ዐውቃለሁ?” አለ። እግዚአብሔርም (ያህዌ) “እያንዳንዳቸው ሦስት ዓመት የሆናቸው አንዲት ጊደር፣ አንድ ፍየልና አንድ በግ፣ በተጨማሪም አንድ ዋኖስና አንድ ርግብ አብረህ አቅርብልኝ” አለው። አብራምም እነዚህን ሁሉ አቀረበለት፤ ቈርጦም ሁለት ቦታ ከከፈላቸው በኋላ፣ እያንዳንዱን ክፍል በሌላው ወገን ትይዩ አስቀመጠ፤ ዋኖሷንና ርግቧን ግን ለሁለት አልከፈላቸውም። አሞሮችም ሥጋውን ለመብላት ወረዱ፤ አብራም ግን አባረራቸው። ፀሓይ ልትገባ ስትል አብራም እንቅልፍ ወሰደው፤ የሚያስፈራም ድቅድቅ ጨለማ መጣበት። እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ “ዘርህ በባዕድ አገር ስደተኛ እንደሚሆን በርግጥ ዕወቅ፤ አራት መቶ ዓመትም በባርነት ተረግጦ ይገዛል። ነገር ግን በባርነት የሚገዛቸውን ሕዝብ እፈርድበታለሁ፤ ከዚያም ብዙ ሀብት ይዘው ይወጣሉ። አንተ ግን ወደ አባቶችህ በሰላም ትሄዳለህ፤ ዕድሜም ጠግበህ ወደ መቃብር ትወርዳለህ፤ በአራተኛውም ትውልድ ዘርህ ወደዚህ ምድር ይመለሳል፤ የአሞራውያን ኀጢአት ገና ጽዋው አልሞላምና።” ፀሓይ ገብታ ከጨለመ በኋላ የምድጃ ጢስና የሚንበለበል ፋና ታየ፤ በተከፈለውም ሥጋ መካከል ዐለፈ። በዚያ ዕለት እግዚአብሔር (ያህዌ) ለአብራም እንዲህ ሲል ኪዳን ገባለት፤ “ከግብፅ ወንዝ ጀምሮ እስከ ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ያለውን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ፤ የምሰጣቸውም የቄናውያንን፣ የቄኔዛውያንን፣ የቃድሞናውያንን፣ የኬጢያውያንን፣ የፌርዛውያንን፣ የራፋይምን፣ የአሞራውያንን፣ የከነዓናውያንን፣ የጌርጌሳውያንንና የኢያቡሳውያንን ምድር ነው።”
ዘፍጥረት 15 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 15
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 15:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos