ምርኮኞቹም ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሰበሰቡ፥ እንደ አለቆቹና እንደ ሽማግሌዎችም ምክር በሦስት ቀን ውስጥ ያልመጣ ሁሉ ንብረቱ ሁሉ እንዲወረስ፥ እርሱም ከምርኮው ጉባኤ እንዲለይ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አዋጅ ነገሩ። ሦስት ቀንም ሳያልፍ በዘጠነኛው ወር ከወሩም በሀያኛው ቀን የይሁዳና የብንያም ሰዎች ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሁሉ ስለዚህ ነገርና ስለ ታላቁ ዝናብ እየተንቀጠቀጡ በእግዚአብሔር ቤት ፊት ባለው አደባባይ ተቀመጡ። ካህኑም ዕዝራ ተነሥቶ፦ “ተላልፋችኋል፤ የእስራኤልን በደል ታበዙ ዘንድ እንግዶችን ሴቶች አግብታችኋል። አሁንም ለአባቶቻችሁ አምላክ ለእግዚአብሔር ተናዘዙ፤ ደስ የሚያሰኘውንም አድርጉ፤ ከምድርም አሕዛብና ከእንግዶች ሴቶች ተለዩ” አላቸው። ጉባኤውም ሁሉ በታላቅ ድምፅ መልሰው እንዲህ አሉ፦ “እንደ ተናገርኸን እናደርግ ዘንድ ይገባናል። ነገር ግን የሕዝቡ ቍጥር ብዙ ነው፤ ጊዜውም የትልቅ ዝናብ ጊዜ ነው፤ በሜዳም ልንቆም አንችልም፤ በዚህም ነገር እጅግ በድለናልና ይህ ሥራ የአንድ ወይም የሁለት ቀን ሥራ አይደለም። አለቆቻችንም በጉባኤው ሁሉ ፋንታ ይቁሙ፤ ስለዚህም ነገር የአምላካችን ጽኑ ቍጣ ከእኛ ይመለስ ዘንድ እንግዶቹን ሴቶች ያገቡት በከተሞቻችን ያሉት ሁሉ በተቀጠረው ጊዜ ይምጡ፤ ከእነርሱም ጋር የከተማ ሁሉ ሽማግሌዎችና ፈራጆች ይምጡ።” ነገር ግን የአሣሄል ልጅ ዮናታንና የቴቁዋ ልጅ የሕዝያ ይህን ነገር ተቃወሙ፤ ሜሱላምና ሌዋዊዉ ሳባታይ ረዱአቸው። ምርኮኞቹም እንዲህ አደረጉ፤ ካህኑ ዕዝራም የአባቶችም ቤቶች አለቆች በየአባቶቻቸው ቤቶች ተለዩ፤ ሁሉም በየስማቸው ተጻፉ፤ በአሥረኛውም ወር በመጀመሪያው ቀን ነገሩን ይመረምሩ ዘንድ ተቀመጡ። እስከ መጀመሪያው ወር እስከ መጀመሪያው ቀን ድረስ ሠርተው፥ እንግዶቹን ሴቶች ያገቡትን ሰዎች ሁሉ መርምረው ጨረሱ።
መጽሐፈ ዕዝራ 10 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ዕዝራ 10:7-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos