የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መጽሐፈ ዕዝራ 10:7-17

መጽሐፈ ዕዝራ 10:7-17 አማ05

ከምርኮ የተመለሱትም ሁሉ በኢየሩሳሌም ይሰበሰቡ ዘንድ በመላው ኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምድር ሁሉ ታወጀ። ይህም ሁሉ በሕዝቡ መሪዎች ምክርና ትእዛዝ የተወሰነ ነበር፤ በሦስት ቀን ጊዜ ውስጥ ወደዚህ ስብሰባ መምጣት ያልቻለ ማንም ሰው ቢኖር ንብረቱ ሁሉ እንደሚወረስና ከምርኮ ከተመቱት ሰዎች ጉባኤ እንደሚወገድ ተነገረው። ይህም ጥሪ እንደ ተላለፈ በሦስት ቀን ጊዜ ውስጥ በይሁዳና በብንያም ግዛት የሚኖሩት ሁሉ ዘጠነኛው ወር በገባ በሃያኛው ቀን ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው በቤተ መቅደሱ አደባባይ ተሰበሰቡ፤ ሰዎቹ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት በተሰበሰቡበት ጉዳይና በዝናቡ ምክንያት እየተንቀጠቀጡ ቆመው ነበር። ካህኑ ዕዝራም ቆሞ እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “እነሆ እምነታችሁን አጓድላችሁ ተገኝታችኋል፤ ባዕዳን ሴቶችንም በማግባታችሁ ምክንያት በእስራኤል ላይ የበደልን ዕዳ አምጥታችኋል። ከአሁን በኋላ እንግዲህ በቀድሞ አባቶቻችሁ አምላክ በእግዚአብሔር ፊት ኃጢአታችሁን ሁሉ ተናዘዙ፤ እርሱም ደስ የሚሰኝበትን ነገር ሁሉ አድርጉ፤ በምድራችን ከሚኖሩት ባዕዳን ሁሉ ራቁ፤ ያገባችኋቸውንም ባዕዳን ሴቶች ወዲያ አስወግዱ።” የተሰበሰቡትም ሰዎች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “አንተ የምትለውን ሁሉ እናደርጋለን!” አሉ። ንግግራቸውንም በመቀጠል እንዲህ አሉት፦ “እነሆ እዚህ የተሰበሰበው ሕዝብ ብዙ ነው፤ ከዚህም ጋር በከባድ ሁኔታ እየዘነበ ነው፤ መጠለያ በሌለበት በዚህ ስፍራ መቆም አልቻልንም፤ በዚህ ኃጢአት የተበከልነውም ብዙዎች በመሆናችን ይህን ሁሉ ነገር በአንድ ወይም በሁለት ቀኖች ውስጥ መፈጸም አይቻልም። ስለዚህ አለቆቻችን በዚሁ በኢየሩሳሌም ጉዳዩን ያጥኑት፤ ከዚህም በኋላ ባዕድ ሴት ያገባ ሁሉ እያንዳንዱ በሚሰጠው የቀጠሮ ቀን ከሚኖርባት ከተማ መሪዎችና ዳኞች ጋር እየመጣ ውሳኔውን ይቀበል፤ እግዚአብሔር የተቈጣበትም ሁኔታ ሁሉ በዚሁ ዐይነት ይበርዳል።” ይህም በተነገረ ጊዜ መሹላምና ሻበታይ ተብሎ የሚጠራው አንድ ሌዋዊ ድጋፍ ከሰጡአቸው ከዐሣሔል ልጅ ዮናታንና የቲቅዋ ልጅ ከሆነው ከያሕዘያ በቀር ሌላ ተቃዋሚ አልነበረም። ከምርኮ የተመለሱት ሁሉ ይህንኑ ዕቅድ ለመቀበል ተስማሙ፤ ስለዚህም ካህኑ ዕዝራ ከጐሣ መሪዎች መካከል መርጦ አስፈጻሚዎችን በመሾም ስም ዝርዝራቸውን መዝግቦ አኖረ፤ እነርሱም ዐሥረኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን ጉዳዩን መመርመር ጀመሩ። በሚቀጥለው ዓመት በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን ከባዕዳን ሴቶች ጋር የተጋቡትን ሰዎች ጉዳይ በሙሉ መርምረው ጨረሱ።