ኦሪት ዘጸአት 7:14-25

ኦሪት ዘጸአት 7:14-25 አማ54

እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፦ “የፈርዖን ልብ ደነደነ፤ ሕዝቡንም ለመልቀቅ እንቢ አለ። ማልደህ ወደ ፈርዖን ሂድ፤ እነሆ ወደ ውኃ ይወጣል፤ ትገናኘውም ዘንድ አንተ በወንዝ ዳር ትቆማለህ፤ እባብም ሆና የተለወጠችውን በትር በእጅህ ትወስዳለህ። እንዲህም ትለዋለህ፦ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር፦ በምድረ በዳ እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ’ ብሎ ወደ አንተ ላከኝ፤ እነሆም እስከ ዛሬ አልሰማህም። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ በዚህ ታውቃለህ፤ እነሆ እኔ የወንዙን ውኃ በእጄ ባለችው በትር እመታለሁ፤ ውኃውም ተለውጦ ደም ይሆናል። በወንዙም ያሉት ዓሦች ይሞታሉ፤ ወንዙም ይገማል፤ ግብፃውያንም የወንዙን ውኃ ለመጠጣት ይጠላሉ።’” እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “አሮንን፥ ‘በትርህን ውሰድ፤ ደምም እንዲሆኑ በግብፅ ውኆች በወንዞቻቸውም በመስኖቻቸውም በኩሬዎቻቸውም በውኃ ማከማቻዎቻቸውም ሁሉ ላይ እጅህን ዘርጋ’ በለው፤ በግብፅም አገር ሁሉ በእንጨት ዕቃና በድንጋይ ዕቃ ሁሉ ደም ይሆናል።” ሙሴና አሮንም እግዚአብሔር እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ በትሩንም አነሣ፤ በፈርዖንና በባሪያዎቹም ፊት የወንዙን ውኃ መታ፤ የወንዙም ውኃ ሁሉ ተለውጦ ደም ሆነ። በወንዙም የነበሩ ዓሦች ሞቱ፤ ወንዙም ገማ፤ ግብፃውያንም ከወንዙ ውኃ ይጠጡ ዘንድ አልቻሉም፤ ደሙም በግብፅ አገር ሁሉ ነበረ። የግብፅም ጠንቍዮች በአስማታቸው እንዲሁ አደረጉ፤ እግዚአብሔርም እንደተናገረ የፈርዖን ልብ ጸና፤ አልሰማቸውምም። ፈርዖንም ተመልሶ ወደ ቤቱ ገባ፤ ይህንም ደግሞ በልቡ አላኖረውም። ግብፃውያንም ሁሉ የወንዙን ውኃ ይጠጡ ዘንድ አልቻሉምና በወንዙ አጠገብ ውኃ ሊጠጡ ቆፈሩ። እግዚአብሔርም ወንዙን ከመታ በኋላ ሰባት ቀን ተፈጸመ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}