መጽሐፈ መክብብ 8
8
1እንደ ጠቢብ የሆነ ሰው ማን ነው? ነገርንስ መተርጐም የሚያውቅ ማን ነው? የሰው ጥበብ ፊቱን ታበራለች፥ የፊቱንም ድፍረት ትለውጣለች። 2እኔ፦ በእግዚአብሔር መሐላ ምክንያት የንጉሥን ትእዛዝ ጠብቅ እልሃለሁ። 3የወደደውን ሁሉ ያደርጋልና ከፊቱ ትወገድ ዘንድ አትቸኵል፥ ክፉንም በማድረግ አትጽና። 4የንጉሥ ቃል ኃይለኛ ነውና፥ ይህንስ ለምን ታደርጋለህ? ማን ይለዋል? 5ትእዛዝን የሚጠብቅ ክፉን ነገር አያውቅም፥ የጠቢብም ልብ ጊዜንና ፍርድን ያውቃል። 6የሰው መከራ በእርሱ ላይ እጅግ ስለ ሆነ ለነገር ሁሉ ጊዜና ፍርድ አለውና። 7የሚሆነውንም አያውቅም፥ እንዴትስ እንደሚሆን የሚነግረው ማን ነው? 8መንፈስን ለማስቀረት በመንፈስ ላይ ሥልጣን ያለው ሰው የለም፥ በሞቱም ቀን ሥልጣን የለውም፥ በሰልፍም ስንብቻ የለም፥ ኃጢአትም ሠሪውን አያድነውም። 9ይህን ሁሉ አየሁ፥ ከፀሐይም በታች ወደ ተደረገው ሥራ ሁሉ ልቤን ሰጠሁ፥ ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዢ የሚሆንበት ጊዜ አለ።
10እንዲሁም ኀጥኣን ተቀብረው አየሁ፥ ወደ ዕረፍትም ገቡ፥ ነገር ግን ቅን አድራጊዎች ከቅድስት ስፍራ ወጡ፥ በከተማይቱም ውስጥ ተረሱ፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው። 11በክፉ ሥራ ላይ ፈጥኖ ፍርድ አይፈረድምና ስለዚህ በሰው ልጆች ውስጥ ልባቸው ክፉን ለመሥራት ጠነከረ። 12ኃጢአተኛ መቶ ጊዜ ክፉን ቢሠራ ዘመኑም ረጅም ቢሆን፥ እግዚአብሔርን ለሚፈሩት በፊቱም ለሚፈሩት ደኅንነት እንዲሆን አውቃለሁ፥ 13ለኀጥእ ግን ደኅንነት የለውም፥ በእግዚአብሔርም ፊት አይፈራምና ዘመኑ እንደ ጥላ አትረዝምም።
14በምድር የሚደረግ ከንቱ ነገር አለ፥ በኀጥኣን የሚደረገው ሥራ የሚደርስባቸው ጻድቃን አሉ፥ ለጻድቃንም የሚደረገው ሥራ የሚደርስላቸው ኀጥኣን አሉ፥ ይህም ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ። 15ከሚበላውና ከሚጠጣው ደስም ከሚለው በቀር ለሰው ከፀሐይ በታች ሌላ መልካም ነገር የለውምና እኔ ደስታን አመሰገንሁ፥ ከፀሐይም በታች ከድካሙ እግዚአብሔር በሰጠው በሕይወቱ ዘመን ይህ ደስታው ከእርሱ ጋር ይኖራል።
16ጥበብን አውቅ ዘንድ በምድር የሚሆነውንም ድካም አይ ዘንድ ልቤን ሰጠሁ፥ በቀንና በሌሊት እንቅልፍን በዓይኑ የማያይ አለና፥ 17ከፀሐይም በታች የተደረገውን ሥራ መርምሮ ያገኝ ዘንድ ለሰው እንዳይቻለው የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ አየሁ። ሰውም ሊፈልግ እጅግ ቢደክም መርምሮ አያገኘውም፥ ደግሞ ጠቢብ ሰው፦ ይህን አወቅሁ ቢል እርሱ ያገኘው ዘንድ አይችልም።
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 8: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ