መጽሐፈ መክብብ 2:1-16

መጽሐፈ መክብብ 2:1-16 አማ54

እኔ በልቤ፦ ና በደስታም እፈትንሃለሁ፥ መልካምንም ቅመስ አልሁ፥ ይህም ደግሞ እነሆ ከንቱ ነበረ። ሳቅን፦ ዕብድ ነህ፥ ደስታንም፦ ምን ታደርጋለህ? አልሁት። የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከፀሐይ በታች ሊሠሩት መልካም ነገር ምን እንደ ሆነ እስካይ ድረስ ልቤ በጥበብ እየመራኝ፥ ሰውነቴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሰኘት ስንፍናንም ለመያዝ በልቤ መረመርሁ። ትልቅ ሥራን ሠራሁ፥ ቤቶችንም አደረግሁ፥ ወይንም ተከልሁ፥ አትክልትንና ገነትን አደረግሁ፥ ልዩ ልዩ ፍሬ ያለባቸውንም ዛፎች ተከልሁባቸው፥ በዱር የተተከሉትን ዛፎች አጠጣበት ዘንድ የውኃ ማጠራቀሚያ አደረግሁ። ወንዶችንና ሴቶችን ባሪያዎች ገዛሁ፥ የቤት ውልድ ባሪያዎችም ነበሩኝ፥ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ብዙ ከብቶችና መንጋዎች ነበሩኝ። ብርንና ወርቅን የከበረውንም የነገሥታትና የአውራጆችን መዝገብ ሰበሰብሁ፥ አዝማሪዎችንና አርሆዎችን የሰዎች ልጆችንም ተድላ እጅግ የበዙ ሴቶችንም አከማቸሁ። ታላቅም ሆንሁ፥ ከእኔም አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ከበርሁ፥ ደግምም ጥበቤ ከእኔ ጋር ጸንታ ቀረች። ዓይኖቼንም ከፈለጉት ሁሉ አልከለከልኋቸውም፥ ልቤም በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና ልቤን ከደስታ ሁሉ አላራቅሁትም፥ ከድካሜም ሁሉ ይህ እድል ፈንታዬ ሆነ። እጄ የሠራቻትን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፥ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም። እኔም ጥበብን ዕብደትንና ስንፍናን አይ ዘንድ ተመለከትሁ፥ በፊት ከተደረገው በቀር፥ ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ያደርጋል? እኔ ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ እንዲሁ ጥበብ ከስንፍና እንዲበልጥ አየሁ። የጠቢብ ዓይኖች በራሱ ላይ ናቸው፥ ሰነፍ ግን በጨለማ ይሄዳል፥ ደግሞ ለሁለቱ መጨረሻቸው አንድ እንደ ሆነ አስተዋልሁ። እኔም በልቤ፦ ለሰነፍ የሚደርሰው ለእኔም ይደርሳል ለምን እጅግ ጠቢብ ሆንሁ? አልሁ። የዚያን ጊዜም በልቤ፦ ይህ ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ። በሚመጣው ዘመን ነገር ሁሉ የተረሳ ይሆናልና ለዘላለም የሚሆን የጠቢብና የሰነፍ መታሰቢያ አይገኝም። አዬ ጉድ! ጠቢብ ከሰነፍ ጋር እንዴት ይሞታል!