መክብብ 2:1-16
መክብብ 2:1-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እኔ በልቤ፥ “ና በደስታም እፈትንሃለሁ፥ እነሆ፥ መልካምንም እይ” አልሁ፤ ይህም እነሆ፥ ከንቱ ነበረ። ሣቅን፥ “ሽንገላ ነህ፤ ደስታንም፦ ምን ታደርጋለህ?” አልሁት። የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከፀሐይ በታች የሚሠሩት መልካም ነገር ምን እንደ ሆነ እስካይ ድረስ ልቤ በጥበብ እየመራኝ፥ ሰውነቴን በወይን ደስ ለማሰኘት፥ ስንፍናንም ለመያዝ በልቤ መረመርሁ። እኔ ሥራዬን አበዛሁ፥ ቤቶችንም ለእኔ ሠራሁ፥ ወይንም ተከልሁ። የወይንና የአትክልት ቦታን አደረግሁ፥ ወይንና ልዩ ልዩ ፍሬ ያለባቸውንም ዛፎች ተከልሁባቸው። የሚያፈራ እንጨትንና የተተከሉትን ዛፎች አጠጣበት ዘንድ የውኃ ማጠራቀሚያን አደረግሁ። ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮችን ገዛሁ፤ በቤት የተወለዱ አገልጋዮችም ነበሩኝ፤ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ብዙ የበጎችና የከብቶች መንጋዎች ነበሩኝ። ብርንና ወርቅን፥ የከበረውንም የነገሥታትንና የአውራጆችን መዝገብ ለራሴ ሰበሰብሁ፤ ሴቶችና ወንዶች አዝማሪዎችን፥ የሰዎች ልጆችንም ተድላ አደረግሁ፤ የወይን ጠጅ ጠማቂዎችንና አሳላፊዎችንም አበዛሁ። ከእኔም አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ከበርሁ፥ ታላቅም ሆንሁ። ጥበቤም ከእኔ ጋር ጸናችልኝ። ዐይኖቼ ከፈለጉት ሁሉ አላጣሁም፥ ልቤንም ከደስታ ሁሉ አልከለከልሁትም፤ ልቤ በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና፤ ከድካሜም ሁሉ ይህ ዕድል ፋንታዬ ሆነ። እጄ የሠራቻትን ሥራዬን ሁሉ፥ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፤ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም። እኔም ጥበብን፥ ሽንገላንና ስንፍናን አይ ዘንድ ተመለከትሁ ፥ ምክርን የሚከተል፥ ምሳሌንስ ሁሉ የሚያደርግላት ሰው ማን ነው? እኔም ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ እንዲሁ ከአላዋቂ ይልቅ ለብልህ ብልጫ እንዳለው ተመለከትሁ። የጠቢብ ዐይኖች በራሱ ላይ ናቸውና፤ አላዋቂ ግን በጨለማ ይሄዳል፤ ደግሞ የሁለቱም መጨረሻቸው አንድ እንደ ሆነ አስተዋልሁ። እኔም በልቤ፥ “አላዋቂን የሚያገኘው እንዲሁ እኔንም ያገኘኛል፤ እኔም ለምን እጅግ ጠቢብ ሆንሁ?” አልሁ፤ የዚያን ጊዜም በልቤ፥ “ይህ ደግሞ ከንቱ ነው” አልሁ፥ አላዋቂ በከንቱ መናገርን ያበዛልና። ለብልህ ከአላዋቂ ጋር ለዘለዓለም መታሰቢያ የለውም፤ እነሆ፥ ዘመን ይመጣልና ሁሉም ይረሳል፤ ብልህስ ከአላዋቂ ጋር እንዴት ይሞታል?
መክብብ 2:1-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እኔም በልቤ፣ “መልካም የሆነውን ለማወቅ፣ በተድላ እፈትንሃለሁ” አልሁ፤ ነገር ግን ያም ከንቱ ነበረ። ደግሞም፣ “ሣቅ ሞኝነት ነው፤ ተድላስ ምን ይጠቅማል?” አልሁ። አሁንም አእምሮዬ በጥበብ እየመራኝ ራሴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሠኘት፣ ሞኝነትንም ለመያዝ ሞከርሁ፤ ሰዎች በዐጭር የሕይወት ዘመናቸው ከሰማይ በታች ባለው ላይ ቢሠሩት ሊጠቅማቸው የሚችል ምን እንደ ሆነ ለማየት ፈለግሁ። ታላላቅ ነገሮችን አከናወንሁ፤ ለራሴ ቤቶችን ሠራሁ፤ ወይንንም ተከልሁ፤ አትክልትን ተከልሁ፤ የመዝናኛ ስፍራዎችን አዘጋጀሁ፤ በእነዚህም ላይ ፍሬ የሚያፈሩ የዛፍ ዐይነቶችን ሁሉ ተከልሁባቸው፤ የሚለመልሙ ዛፎችን፣ ለቦይ የሚሆኑ የውሃ ማጠራቀሚያዎችን ሠራሁ። ወንድና ሴት ባሪያዎችን ገዛሁ፤ በቤቴም የተወለዱ ሌሎች ባሪያዎች ነበሩኝ። ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ይልቅ ብዙ የከብት፣ የበግና የፍየል መንጋዎች ነበሩኝ። ለራሴም ብርንና ወርቅን፣ የነገሥታትና የአውራጃዎችን ሀብት አካበትሁ፤ ወንድና ሴት አዝማሪዎች፣ የሰው መደሰቻ የሆኑ ቅምጦች ነበሩኝ። ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ እጅግ ታላቅ ሆንሁ፤ በዚህ ሁሉ ጥበቤ ከእኔ ጋራ ነበረች። ዐይኔ የፈለገውን ሁሉ አልከለከልሁትም፤ ለልቤም ምድራዊ ደስታን አልነፈግሁትም፤ ልቤ በሠራሁት ሁሉ ደስ አለው፤ ይህም የድካሜ ሁሉ ዋጋ ነበረ። ሆኖም እጆቼ የሠሩትን ሁሉ፣ ለማግኘትም የደከምሁትን ድካም ሁሉ ሳስብ፣ ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር፤ ከፀሓይ በታች ምንም ትርፍ አልነበረም። ከዚያም ጥበብን፣ እብደትንና ሞኝነትን ለመመርመር ሐሳቤን መለስሁ፤ አስቀድሞ ከተደረገው በቀር፣ ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ሊያደርግ ይችላል? ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ ሁሉ፣ ጥበብም ከሞኝነት እንደሚበልጥ ተመለከትሁ። የጠቢብ ሰው ዐይኖች ያሉት በራሱ ውስጥ ነው፤ ሞኝ ግን በጨለማ ውስጥ ይራመዳል፤ ሆኖም የሁለቱም ዕድል ፈንታ፣ አንድ መሆኑን ተገነዘብሁ። ከዚያም በልቤ፣ “የሞኙ ዕድል ፈንታ በእኔም ላይ ይደርሳል፤ ታዲያ ጠቢብ በመሆኔ ትርፌ ምንድን ነው?” አልሁ። በልቤም፣ “ይህም ደግሞ ከንቱ ነው” አልሁ። ጠቢቡም ሰው እንደ ሞኙ ለዘላለም አይታወስምና፤ በሚመጡት ዘመናት ሁለቱም ይረሳሉ። ለካ፣ ጠቢቡም እንደ ሞኙ መሞቱ አይቀርም!
መክብብ 2:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እኔ በልቤ፦ ና በደስታም እፈትንሃለሁ፥ መልካምንም ቅመስ አልሁ፥ ይህም ደግሞ እነሆ ከንቱ ነበረ። ሳቅን፦ ዕብድ ነህ፥ ደስታንም፦ ምን ታደርጋለህ? አልሁት። የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከፀሐይ በታች ሊሠሩት መልካም ነገር ምን እንደ ሆነ እስካይ ድረስ ልቤ በጥበብ እየመራኝ፥ ሰውነቴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሰኘት ስንፍናንም ለመያዝ በልቤ መረመርሁ። ትልቅ ሥራን ሠራሁ፥ ቤቶችንም አደረግሁ፥ ወይንም ተከልሁ፥ አትክልትንና ገነትን አደረግሁ፥ ልዩ ልዩ ፍሬ ያለባቸውንም ዛፎች ተከልሁባቸው፥ በዱር የተተከሉትን ዛፎች አጠጣበት ዘንድ የውኃ ማጠራቀሚያ አደረግሁ። ወንዶችንና ሴቶችን ባሪያዎች ገዛሁ፥ የቤት ውልድ ባሪያዎችም ነበሩኝ፥ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ብዙ ከብቶችና መንጋዎች ነበሩኝ። ብርንና ወርቅን የከበረውንም የነገሥታትና የአውራጆችን መዝገብ ሰበሰብሁ፥ አዝማሪዎችንና አርሆዎችን የሰዎች ልጆችንም ተድላ እጅግ የበዙ ሴቶችንም አከማቸሁ። ታላቅም ሆንሁ፥ ከእኔም አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ከበርሁ፥ ደግምም ጥበቤ ከእኔ ጋር ጸንታ ቀረች። ዓይኖቼንም ከፈለጉት ሁሉ አልከለከልኋቸውም፥ ልቤም በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና ልቤን ከደስታ ሁሉ አላራቅሁትም፥ ከድካሜም ሁሉ ይህ እድል ፈንታዬ ሆነ። እጄ የሠራቻትን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፥ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም። እኔም ጥበብን ዕብደትንና ስንፍናን አይ ዘንድ ተመለከትሁ፥ በፊት ከተደረገው በቀር፥ ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ያደርጋል? እኔ ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ እንዲሁ ጥበብ ከስንፍና እንዲበልጥ አየሁ። የጠቢብ ዓይኖች በራሱ ላይ ናቸው፥ ሰነፍ ግን በጨለማ ይሄዳል፥ ደግሞ ለሁለቱ መጨረሻቸው አንድ እንደ ሆነ አስተዋልሁ። እኔም በልቤ፦ ለሰነፍ የሚደርሰው ለእኔም ይደርሳል ለምን እጅግ ጠቢብ ሆንሁ? አልሁ። የዚያን ጊዜም በልቤ፦ ይህ ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ። በሚመጣው ዘመን ነገር ሁሉ የተረሳ ይሆናልና ለዘላለም የሚሆን የጠቢብና የሰነፍ መታሰቢያ አይገኝም። አዬ ጉድ! ጠቢብ ከሰነፍ ጋር እንዴት ይሞታል!
መክብብ 2:1-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ራሴን ለማስደሰትና የደስታንም ትርጒም መርምሬ ለማወቅ ወሰንኩ፤ ነገር ግን ይህም ከንቱ ሆኖ አገኘሁት። ሳቅ ከሞኝነት ያልተሻለ፥ ተድላ ደስታም ዋጋ የሌለው ነገር መሆኑን አስተዋልኩ። ይህም ሁሉ ሆኖ ጥበብን ለማግኘት ባለኝ ምኞት በመመራት ልቤን በወይን ጠጅ እያስደሰትኩ የምዝናናበት ጊዜ እንዲኖረኝ ለማድረግ በሞኝነት ወሰንኩ፤ ሰዎች ሁሉ በምድር ላይ በሚኖሩበት በአጭር ዕድሜአቸው ሊያገኙት የሚገባ የተሻለ መልካም ዕድል ይህ ብቻ መሆኑን አሰብኩ። ደግሞም አንድ ትልቅ ነገር ፈጸምኩ፤ ይኸውም፥ መኖሪያ ቤቶችን ሠራሁ፤ ወይን ተከልኩ፤ የተለያዩ የፍራፍሬ ዛፎች፥ የአበባና የአትክልት ቦታዎችን አዘጋጀሁ፤ የሚያድጉ ዛፎችን ለማጠጣት የውሃ ግድቦችን ሠራሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ባርያዎችን ገዛሁ፤ ሌሎች የቤት ውልድ አገልጋዮችም ነበሩኝ፤ ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይበልጥ ብዙ የከብት፥ የፍየልና የበግ መንጋ አረባሁ። እኔ በምገዛው አገር ሁሉ ከልዩ ልዩ አውራጃዎች የከበሩ የቤተ መንግሥት መዛግብትን በመሰብሰብ ብዙ ወርቅና ብር አከማቸሁ፤ እኔን የሚያሞግሡ ወንዶችና ሴቶች አዝማሪዎችንም አዘጋጀሁ፤ ለሰው ተድላና ደስታን ሊሰጡ የሚችሉ እጅግ ብዙ ሴቶችንም ሰበሰብኩ። ከዚህም የተነሣ ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይበልጥ የከበርኩ ታላቅ ሰው ሆንኩ፤ ጥበቤም ከእኔ ጋር ጸንታ ኖረች። ዐይኔ ያየውንና ልቤ የተመኘውን ሁሉ አገኘሁ፤ ለሰውነቴም የሚያስፈልገውን ደስታ ሁሉ አልነፈግሁትም፤ ደክሜ በሠራሁት ነገር ሁሉ ስለምደሰትበት እንግዲህ የእኔ ዕድል ፈንታ ይህ ነበር። ይህን ሁሉ ካደረግሁ በኋላ ያንን የሠራሁትን ነገር ሁሉ ምን ያኽል እንደ ደከምኩበት ስመለከት ከቊጥር የማይገባ ዋጋቢስ መሆኑን ተረዳሁ፤ እንዲያውም ምንም የማይጠቅምና ነፋስን እንደ መጨበጥ የሚያስቈጥር ሆኖ አገኘሁት። መቼም ንጉሥ መሥራት የሚችለው ከእርሱ በፊት የነበሩት ነገሥታት የሠሩትን በመከተል ነው፤ ስለዚህ እኔም ጥበብ፥ ሞኝነትና እብደት ምን እንደ ሆኑ መርምሬ ለማወቅ ማሰብ ጀመርኩ። እንዲህም አልኩ “በእርግጥ ብርሃን ከጨለማ እንደሚሻል ጥበብም ከሞኝነት መሻልዋን ተመለከትኩ። ጥበበኞች ሰዎች መነሻና መድረሻቸውን ያውቃሉ፤ ሞኞች ግን ይህን ሁሉ አያውቁም፤” ይሁን እንጂ ጥበበኛም ሆነ ሞኝ ሁለቱም የሚኖራቸው ዕድል አንድ ዐይነት መሆኑን ተረዳሁ። ስለዚህም “ለሞኝ የሚደርሰው ዕድል ለእኔም ይደርሳል፤ ታዲያ፥ ይህን ያኽል ጥበበኛ የመሆኔ ትርፉ ምንድን ነው?” ብዬ በልቤ አሰብኩ። ወዲያውኑ “ይህ ሁሉ ከንቱ ነው!” አልኩ። ጥበበኛንም ሆነ ሞኝን ሁለቱንም ለረጅም ጊዜ የሚያስታውሳቸው አይገኝም፤ በሚመጣው ዘመን ሁላችንም የተረሳን ሆነን እንቀራለን፤ ጥበበኞችም ሆንን ሞኞች፥ ሁላችንንም ሞት ይጠብቀናል።
መክብብ 2:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እኔ በልቤ እራሴን እንዲህ አልኩት፦ “ና ደስታን በማቅመስ ልፈትንህ፥ መልካምንም ቅመስ፤” ይህም ደግሞ እነሆ ከንቱ ነበረ። “ሳቅን፦ ዕብደት፥ ደስታንም፦ ዋጋ ቢስ” አልሁት። ልቤ በጥበብ እየመራኝ፥ ሰውነቴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሰኘት አላዋቂነትንም ለመያዝ በልቤ መረመርሁ፤ ይህም የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከፀሐይ በታች ሊሠሩት የሚገባ መልካም ነገር ምን እንደሆነ እስካይ ድረስ ነው። ትልቅ ሥራን ሠራሁ፤ ለራሴ ቤቶችን ገነባሁ፥ ወይንንም ተከልሁ፥ የአትክልት ሥፍራዎችንና ገነትን አሰናዳሁ፥ ልዩ ልዩ ፍሬ ያለባቸውንም ዛፎች ተከልሁባቸው፥ በዱር የተተከሉትን ዛፎች አጠጣበት ዘንድ የውኃ ማጠራቀሚያ ሠራሁ። ወንዶችንና ሴቶችን ባርያዎች ገዛሁ፥ የቤት ውልድ ባርያዎችም ነበሩኝ፥ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ብዙ ከብቶችና መንጋዎች ነበሩኝ። ብርንና ወርቅን የከበረውንም የነገሥታትና የአውራጆችን መዝገብ ሰበሰብሁ፥ ወንዶችና ሴቶች አዝማሪዎችን፥ ለሰዎች ልጆች ተድላ የሚሰጡ እጅግ የበዙ ሴቶችንም አከማቸሁ። ታላቅም ሆንሁ፥ ከእኔም አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ከበርሁ፥ ደግምም ጥበቤ ከእኔ ጋር ጸናች። ዐይኖቼ የፈለጉትን እንዳያዩ አልከለከልኋቸውም፥ ልቤም በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና ልቤን ከደስታ ሁሉ አላራቅሁትም፥ ከድካሜም ሁሉ ይህ እድል ፈንታዬ ሆነ። እጄ የሠራቻትን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፥ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም። እኔም ጥበብን ዕብደትንና አለማወቅን ለመመርመር ወሰንኩ፥ በፊት የተደረገውን መድገም ካልሆነ በቀር፥ ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ያደርጋል? እኔ ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ እንዲሁ ጥበብ ከአለማወቅ እንደሚበልጥ አየሁ። የጠቢብ ዐይኖች በራሱ ላይ ናቸው፥ አላዋቂ ግን በጨለማ ይሄዳል፥ ሆኖም የሁለቱም መጨረሻቸው አንድ እንደሆነ አስተዋልሁ። እኔም በልቤ፦ በአላዋቂ ላይ የሚደርሰው በእኔም ላይ ይደርሳል፤ ለምን እጅግ ጠቢብ ሆንሁ? አልሁ። የዚያን ጊዜም በልቤ፦ ይህ ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ። በሚመጣው ዘመን ነገር ሁሉ የተረሳ ይሆናልና ለዘለዓለም የሚሆን የጠቢብና የአላዋቂ መታሰቢያ አይገኝም። አዬ ጉድ! ጠቢብ ከአላዋቂ ጋር እንዴት ይሞታል!