እኔ በልቤ እራሴን እንዲህ አልኩት፦ “ና ደስታን በማቅመስ ልፈትንህ፥ መልካምንም ቅመስ፤” ይህም ደግሞ እነሆ ከንቱ ነበረ። “ሳቅን፦ ዕብደት፥ ደስታንም፦ ዋጋ ቢስ” አልሁት። ልቤ በጥበብ እየመራኝ፥ ሰውነቴን በወይን ጠጅ ደስ ለማሰኘት አላዋቂነትንም ለመያዝ በልቤ መረመርሁ፤ ይህም የሰው ልጆች በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ከፀሐይ በታች ሊሠሩት የሚገባ መልካም ነገር ምን እንደሆነ እስካይ ድረስ ነው። ትልቅ ሥራን ሠራሁ፤ ለራሴ ቤቶችን ገነባሁ፥ ወይንንም ተከልሁ፥ የአትክልት ሥፍራዎችንና ገነትን አሰናዳሁ፥ ልዩ ልዩ ፍሬ ያለባቸውንም ዛፎች ተከልሁባቸው፥ በዱር የተተከሉትን ዛፎች አጠጣበት ዘንድ የውኃ ማጠራቀሚያ ሠራሁ። ወንዶችንና ሴቶችን ባርያዎች ገዛሁ፥ የቤት ውልድ ባርያዎችም ነበሩኝ፥ ከእኔ አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ብዙ ከብቶችና መንጋዎች ነበሩኝ። ብርንና ወርቅን የከበረውንም የነገሥታትና የአውራጆችን መዝገብ ሰበሰብሁ፥ ወንዶችና ሴቶች አዝማሪዎችን፥ ለሰዎች ልጆች ተድላ የሚሰጡ እጅግ የበዙ ሴቶችንም አከማቸሁ። ታላቅም ሆንሁ፥ ከእኔም አስቀድመው በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ከበርሁ፥ ደግምም ጥበቤ ከእኔ ጋር ጸናች። ዐይኖቼ የፈለጉትን እንዳያዩ አልከለከልኋቸውም፥ ልቤም በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና ልቤን ከደስታ ሁሉ አላራቅሁትም፥ ከድካሜም ሁሉ ይህ እድል ፈንታዬ ሆነ። እጄ የሠራቻትን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፥ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበረ፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም። እኔም ጥበብን ዕብደትንና አለማወቅን ለመመርመር ወሰንኩ፥ በፊት የተደረገውን መድገም ካልሆነ በቀር፥ ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ያደርጋል? እኔ ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ እንዲሁ ጥበብ ከአለማወቅ እንደሚበልጥ አየሁ። የጠቢብ ዐይኖች በራሱ ላይ ናቸው፥ አላዋቂ ግን በጨለማ ይሄዳል፥ ሆኖም የሁለቱም መጨረሻቸው አንድ እንደሆነ አስተዋልሁ። እኔም በልቤ፦ በአላዋቂ ላይ የሚደርሰው በእኔም ላይ ይደርሳል፤ ለምን እጅግ ጠቢብ ሆንሁ? አልሁ። የዚያን ጊዜም በልቤ፦ ይህ ደግሞ ከንቱ ነው አልሁ። በሚመጣው ዘመን ነገር ሁሉ የተረሳ ይሆናልና ለዘለዓለም የሚሆን የጠቢብና የአላዋቂ መታሰቢያ አይገኝም። አዬ ጉድ! ጠቢብ ከአላዋቂ ጋር እንዴት ይሞታል!
መጽሐፈ መክብብ 2 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መክብብ 2:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች