ራሴን ለማስደሰትና የደስታንም ትርጒም መርምሬ ለማወቅ ወሰንኩ፤ ነገር ግን ይህም ከንቱ ሆኖ አገኘሁት። ሳቅ ከሞኝነት ያልተሻለ፥ ተድላ ደስታም ዋጋ የሌለው ነገር መሆኑን አስተዋልኩ። ይህም ሁሉ ሆኖ ጥበብን ለማግኘት ባለኝ ምኞት በመመራት ልቤን በወይን ጠጅ እያስደሰትኩ የምዝናናበት ጊዜ እንዲኖረኝ ለማድረግ በሞኝነት ወሰንኩ፤ ሰዎች ሁሉ በምድር ላይ በሚኖሩበት በአጭር ዕድሜአቸው ሊያገኙት የሚገባ የተሻለ መልካም ዕድል ይህ ብቻ መሆኑን አሰብኩ። ደግሞም አንድ ትልቅ ነገር ፈጸምኩ፤ ይኸውም፥ መኖሪያ ቤቶችን ሠራሁ፤ ወይን ተከልኩ፤ የተለያዩ የፍራፍሬ ዛፎች፥ የአበባና የአትክልት ቦታዎችን አዘጋጀሁ፤ የሚያድጉ ዛፎችን ለማጠጣት የውሃ ግድቦችን ሠራሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ባርያዎችን ገዛሁ፤ ሌሎች የቤት ውልድ አገልጋዮችም ነበሩኝ፤ ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይበልጥ ብዙ የከብት፥ የፍየልና የበግ መንጋ አረባሁ። እኔ በምገዛው አገር ሁሉ ከልዩ ልዩ አውራጃዎች የከበሩ የቤተ መንግሥት መዛግብትን በመሰብሰብ ብዙ ወርቅና ብር አከማቸሁ፤ እኔን የሚያሞግሡ ወንዶችና ሴቶች አዝማሪዎችንም አዘጋጀሁ፤ ለሰው ተድላና ደስታን ሊሰጡ የሚችሉ እጅግ ብዙ ሴቶችንም ሰበሰብኩ። ከዚህም የተነሣ ከእኔ በፊት በኢየሩሳሌም ከነበሩት ሁሉ ይበልጥ የከበርኩ ታላቅ ሰው ሆንኩ፤ ጥበቤም ከእኔ ጋር ጸንታ ኖረች። ዐይኔ ያየውንና ልቤ የተመኘውን ሁሉ አገኘሁ፤ ለሰውነቴም የሚያስፈልገውን ደስታ ሁሉ አልነፈግሁትም፤ ደክሜ በሠራሁት ነገር ሁሉ ስለምደሰትበት እንግዲህ የእኔ ዕድል ፈንታ ይህ ነበር። ይህን ሁሉ ካደረግሁ በኋላ ያንን የሠራሁትን ነገር ሁሉ ምን ያኽል እንደ ደከምኩበት ስመለከት ከቊጥር የማይገባ ዋጋቢስ መሆኑን ተረዳሁ፤ እንዲያውም ምንም የማይጠቅምና ነፋስን እንደ መጨበጥ የሚያስቈጥር ሆኖ አገኘሁት። መቼም ንጉሥ መሥራት የሚችለው ከእርሱ በፊት የነበሩት ነገሥታት የሠሩትን በመከተል ነው፤ ስለዚህ እኔም ጥበብ፥ ሞኝነትና እብደት ምን እንደ ሆኑ መርምሬ ለማወቅ ማሰብ ጀመርኩ። እንዲህም አልኩ “በእርግጥ ብርሃን ከጨለማ እንደሚሻል ጥበብም ከሞኝነት መሻልዋን ተመለከትኩ። ጥበበኞች ሰዎች መነሻና መድረሻቸውን ያውቃሉ፤ ሞኞች ግን ይህን ሁሉ አያውቁም፤” ይሁን እንጂ ጥበበኛም ሆነ ሞኝ ሁለቱም የሚኖራቸው ዕድል አንድ ዐይነት መሆኑን ተረዳሁ። ስለዚህም “ለሞኝ የሚደርሰው ዕድል ለእኔም ይደርሳል፤ ታዲያ፥ ይህን ያኽል ጥበበኛ የመሆኔ ትርፉ ምንድን ነው?” ብዬ በልቤ አሰብኩ። ወዲያውኑ “ይህ ሁሉ ከንቱ ነው!” አልኩ። ጥበበኛንም ሆነ ሞኝን ሁለቱንም ለረጅም ጊዜ የሚያስታውሳቸው አይገኝም፤ በሚመጣው ዘመን ሁላችንም የተረሳን ሆነን እንቀራለን፤ ጥበበኞችም ሆንን ሞኞች፥ ሁላችንንም ሞት ይጠብቀናል።
መጽሐፈ መክብብ 2 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መክብብ 2:1-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች