ኦሪት ዘዳግም 15:1-18

ኦሪት ዘዳግም 15:1-18 አማ54

በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ የዕዳ ምሕረት ታደርጋለህ። ለምሕረቱም የሚገባ ወግ ይህ ነው፤ አበዳሪ ሁሉ ለባልጀራውም ያበደረውን ይተዋል፤ የእግዚአብሔር ይቅርታ ታውጆአልና ያበደረውን ከባልንጀራው ወይም ከወንድሙ አይሻ። ከእንግዳ ላይ ያበደርኸውን መፈለግ ትችላለህ፤ በወንድምህ ላይ ያለውን ሁሉ ግን እጅህ ይተወዋል። አምላክህም እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ ርስት አድርጎ በሰጠህ ምድር ላይ እግዚአብሔር በእውነት ይባርክሃልና አንተም የአምላክህን የእግዚአብሔርን ቃል ፈጽመህ ብትሰማ፥ ታደርጋትም ዘንድ ዛሬ የማዝዝህን ይህችን ትእዛዝ ሁሉ ብትጠብቅ፥ በመካከልህ ድሃ አይኖርም። አምላክህም እግዚአብሔር ተስፋ እንደ ሰጠህ ይባርክሃል፤ ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ፥ አንተ ግን አትበደርም፤ ብዙ አሕዛብንም ትገዛለህ፥ አንተን ግን አይገዙህም። አምላክህ እግዚአብሔር በሰጠህ በአገርህ ደጅ ውስጥ ከሚኖሩ ከወንድሞችህ አንዱ ቢደኸይ፥ ልብህን አታጽና፥ በድሀው ወንድምህ ላይ እጅህን አትጨብጥ። ነገር ግን እጅህን ለእርሱ ክፈት፥ የለመነህንም አስፈላጊውን ነገር አበድረው። ሰባተኛው ዓመት የዕዳ ምሕረት ዓመት ቀርቦአል ብለህ ክፉ አሳብ በልብህ እንዳታስብ፥ ለድሀውም ወንድምህ አንዳች የማትሰጥ እንዳትሆን፥ ዓይንህም በእርሱ ላይ ክፉ እንዳይሆን፥ እርሱም ወደ እግዚአብሔር በአንተ ላይ እንዳይጮኽ፥ ኃጢአትም እንዳይሆንብህ ተጠንቀቅ። እጅህን በምትጥልበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ስለዚህ በሥራህ ሁሉ ይባርክሃልና ፈጽመህ ስጠው፥ በሰጠኸውም ጊዜ በልብህ አትጸጸት። ድሆች ከምድሪቱ ላይ አያልቁምና ስለዚህ እኔ፦ በአገርህ ውስጥ ላለው ድሀ ለተቸገረው ወንድምህ እጅህን ትከፍታለህ ብዬ አዝዝሃለሁ። አንተም ወንድምህን ዕብራዊውን ወይም ዕብራዊቱን ብትገዛ ስድስት ዓመት ያገልግሉህ፤ በሰባተኛውም ዓመት ከአንተ ዘንድ አርነት አውጣው። ከአንተም ዘንድ አርነት ባወጣኸው ጊዜ ባዶውን አትስደደው፤ ነገር ግን ከመንጋህ፥ ከአውድማህም፥ ከወይንህም መጥመቂያ ትለግስለታለህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ባረከህ መጠን ትሰጠዋለህ። አንተም በግብፅ ምድር ባሪያ እንደ ነበርህ አምላክህም እግዚአብሔር እንዳዳነህ አስብ፤ ስለዚህ እኔ ዛሬ ይህን ነገር አዝዝሃለሁ። እርሱ ግን አንተንና ቤትህን ስለወደደ፥ ከአንተም ጋር መልካም ስለ ሆነለት፦ ልወጣ አልወድድም ቢል፥ አንተ ወስፌ ወስደህ በቤትህ በር ላይ ጆሮውን ትበሳዋለህ፥ ለዘላለምም ባሪያ ይሆንሃል። በሴት ባሪያህ ደግሞ እንዲሁ ታደርጋለህ። እርሱንም አርነት ባወጣኸው ጊዜ የምንደኝነቱን ሥራ ሁለት እጥፍ አድርጎ ስድስት ዓመት አገልግሎሃልና አይክበድህ፤ አምልካህም እግዚአብሔር በምትሠራው ሁሉ ይባርክሃል።