ዘዳግም 15:1-18

ዘዳግም 15:1-18 NASV

በየሰባቱ ዓመት መጨረሻ የዕዳ ምሕረት አድርግ። አፈጻጸሙም እንደሚከተለው ነው፤ እያንዳንዱ አበዳሪ ለእስራኤላዊ ባልንጀራው ያበደረውን ይተውለት፤ እግዚአብሔር የዕዳ ምሕረት ዐውጇልና፣ አበዳሪው፣ እስራኤላዊ ባልንጀራውን ወይም ወንድሙን ዕዳውን እንዲከፍለው አይጠይቀው። ለባዕድ ያበደርኸውን መጠየቅ ትችላለህ፤ ወንድምህ ከአንተ የተበደረውን ማንኛውንም ዕዳ ግን ተወው። ይሁን እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር ትወርሳት ዘንድ ርስት አድርጎ በሚሰጥህ ምድር ውስጥ አብዝቶ ስለሚባርክህ፣ በመካከልህ ድኻ አይኖርም፤ ይህ የሚሆነውም ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ፈጽመህ ስትታዘዝና ዛሬ የምሰጥህን እነዚህን ትእዛዞች ሁሉ በጥንቃቄ ስትከተል ብቻ ነው። አምላክህ እግዚአብሔር በሰጠህ ተስፋ መሠረት ስለሚባርክህ፣ አንተ ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ እንጂ ከማንም አትበደርም፤ ብዙ አሕዛብን ትገዛለህ እንጂ ማንም አንተን አይገዛህም። አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር ላይ ካሉት ከተሞች በአንዲቱ ውስጥ ድኻ ቢኖር፣ በድኻ ወንድምህ ላይ ልብህን አታጨክንበት፤ ወይም እጅህን ወደ ኋላ አትሰብስብበት። ይልቁንስ እጅህን ፍታለት፤ የሚያስፈልገውንም ሁሉ ቅር ሳይልህ አበድረው። “ዕዳ የሚሠረዝበት ሰባተኛው ዓመት ተቃርቧል” የሚል ምናምንቴ ሐሳብ ዐድሮብህ፣ በድኻ ወንድምህ ላይ እንዳትጨክንና ምንም ሳትሰጠው እንዳትቀር፣ እርሱም በአንተ ላይ ወደ እግዚአብሔር ጮኾ በደለኛ እንዳትሆን ተጠንቀቅ! በልግስና ስጠው፤ ስትሰጠውም ልብህ አይጸጸት፤ ከዚህም የተነሣ አምላክህ እግዚአብሔር በሥራህ ሁሉና እጅህ ባረፈበት በማናቸውም ነገር ይባርክሃል። በምድሪቱ ላይ ድኾች ምን ጊዜም አይጠፉም፤ ስለዚህ በዚያ ለሚኖሩ ወንድሞችህ፣ ለችግረኞችና ለድኾች እጅህን እንድትዘረጋ አዝዝሃለሁ። ወገንህ የሆነ ዕብራዊ ወንድን ወይም ሴትን ገዝተህ ስድስት ዓመት ካገለገለህ፣ በሰባተኛው ዓመት በነጻ ይሂድ። በምታሰናብተውም ጊዜ ባዶ እጁን አትስደደው። ከመንጋህ፣ ከዐውድማህና ከወይን መጭመቂያህ በልግስና ስጠው፤ አምላክህ እግዚአብሔር በባረከህ መጠን ስጠው። አንተም ራስህ በግብጽ ባሪያ እንደ ነበርህና አምላክህ እግዚአብሔር እንደ ተቤዠህ አስታውስ፤ ይህን ትእዛዝ ዛሬ የምሰጥህም በዚሁ ምክንያት ነው። ነገር ግን አገልጋይህ፣ አንተንና ቤተ ሰብህን ከመውደዱና ከአንተም ጋራ ደስተኛ ሆኖ ከመኖሩ የተነሣ፣ “ከአንተ መለየት አልፈልግም” ቢልህ፣ ጆሮውን ከቤትህ መዝጊያ ላይ በማስደገፍ በወስፌ ትበሳዋለህ፤ ከዚያም ዕድሜ ዘመኑን አገልጋይህ ይሆናል። በሴት አገልጋይህም ላይ እንደዚሁ አድርግ። አገልጋይህን ዐርነት ማውጣቱ ከባድ መስሎ አይታይህ፤ የስድስት ዓመት አገልግሎቱ፣ አንድ የቅጥር ሠራተኛ የሚሰጠው አገልግሎት ዕጥፍ ነውና። አምላክህ እግዚአብሔር በምታደርገው ነገር ሁሉ ይባርክሃል።