ኦሪት ዘዳግም 15:1-18

ኦሪት ዘዳግም 15:1-18 አማ05

“ገንዘብ ያበደርካቸውን ሰዎች ሁሉ በየሰባተኛው ዓመት መጨረሻ ላይ ዕዳቸውን በመሰረዝ ትተውላቸዋለህ፤ አፈጻጸሙም እንደሚከተለው ነው፤ ለእስራኤላዊ ወገኑ ገንዘብ ያበደረ ሁሉ ያበደረውን ብድር ይሰርዝለት፤ እግዚአብሔር የዕዳ መሰረዣ ዓመት ነው ብሎ ያወጀበት ዓመት ስለ ሆነ ከእስራኤላዊ ወገኑ ያበደረውን ገንዘብ ለመቀበል አይፈልግ። ለውጪ አገር ሰው ያበደርከው ብድር እንዲመለስልህ መጠየቅ ትችላለህ፤ ለማንኛውም እስራኤላዊ ወገንህ ያበደርከው ገንዘብ ግን እንዲመለስልህ መጠየቅ የለብህም። “እኔ ዛሬ በማዝህ ትእዛዞች ሁሉ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ታዛዥ ሆነህ ብትገኝ፥ እግዚአብሔር አብዝቶ ስለሚባርክህ እርሱ በርስትነት በሚሰጥህ ምድር በመካከልህ ድኻ አይኖርም፤ እግዚአብሔር በሰጠው የተስፋ ቃል መሠረት ይባርክሃል፤ አንተ ለብዙ ሕዝቦች ገንዘብ ታበድራለህ፤ ነገር ግን ከእነርሱ ከማንኛውም ሰው አትበደርም፤ አንተ በብዙ ሕዝቦች ላይ የበላይነት ይኖርሃል፤ በአንተ ላይ ግን ማንም የበላይ አይሆንም። “አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህ ምድር በምትኖርባቸው ከተሞች ሁሉ አንድ እስራኤላዊ ችግረኛ ሆኖ ቢገኝ የገዛ ወገንህ ስለ ሆነ አትጨክንበት፤ ገንዘብህንም አትንፈገው። ይልቅስ እጅህን ዘርግተህ የሚያስፈልገውን ሁሉ አበድረው። የዕዳ መሰረዣ ሰባተኛ ዓመት ደርሶአል በማለት ችግረኛ ወገንህን ብድር አትከልክለው፤ እንዲህ ያለ ክፉ ሐሳብም ወደ ልብህ አይግባ፤ ብድር መስጠትን ብትከለክል ችግረኛው ወገንህ ወደ እግዚአብሔር ይጮኻል፤ ስለዚህ በአንተ ላይ እንደ በደል ይቈጠርብሃል። ይልቅስ ያለ ቅርታ በለጋሥነት ስጥ፤ ይህን ብታደርግ አምላክህ እግዚአብሔር በምትሠራው ሥራና በምታደርገው ድርጊት ሁሉ ይባርክሃል። መቼም ቢሆን በምድር ላይ ችግረኛና ድኻ መኖሩ ስለማይቀር በአገርህ ለሚገኙ ድኾችና ችግረኞች ጐረቤቶችህ እጅህን እንድትዘረጋ አዝሃለሁ። “ወንድም ሆነ ሴት ከእስራኤላውያን ወገን አንድ ሰው ራሱን ባሪያ አድርጎ ለአንተ ቢሸጥልህ፥ ከስድስት ዓመት አገልግሎት በኋላ በሰባተኛው ዓመት ነጻ ታወጣዋለህ፤ ነጻ በምታወጣው ጊዜ ባዶ እጁን አትስደደው፤ እግዚአብሔር አምላክህ ከሰጠህ በረከት፥ ማለት፥ ከበጎች፥ ከእህልና ከወይን በልግሥና ስጠው። አንተም በግብጽ ምድር ባሪያ እንደ ነበርክና እግዚአብሔር አምላክህ ነጻ ያወጣህ መሆኑን አስታውስ፤ እኔም ዛሬ ይህን ትእዛዝ የማዝህ በዚህ ምክንያት ነው። “ነገር ግን ባሪያህ አንተንና ቤተሰብህን በመውደዱና ከአንተም ጋር ስምምነት ስላለው ለመሄድ አይፈልግም ይሆናል፤ ይህም ከሆነ ወደ ቤትህ ደጃፍ ወስደህ ጆሮውን በወስፌ ብሳው፤ ከዚያም በኋላ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ የአንተ ባሪያ ይሆናል፤ ለሴት ባሪያህም ቢሆን ይህንኑ አድርግ። እርሱንም ነጻ ባወጣኸው ጊዜ አንድ ተቀጣሪ ለስድስት ዓመት ከሚሰጥህ እጥፍ አገልግሎት ስለ ሰጠህ ቅር አይበልህ። እንግዲህ ይህን አድርግ፤ እግዚአብሔርም በምትሠራው ሁሉ ይባርክሃል።