ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 3:22-39

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 3:22-39 አማ54

በዚያን ጊዜም የዳዊት ባሪያዎችና ኢዮአብ ከዘምቻ ታላቅ ምርኮ ይዘው መጡ። አበኔር ግን ዳዊት አሰናብቶት በደኅና ሄዶ ነበር እንጂ በኬብሮን አልነበረም። ኢዮአብና ከእርሱም ጋር የነበረ ጭፍራ ሁሉ በመጡ ጊዜ፦ የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሥ መጣ፥ አሰናበተውም በደኅናውም ሄደ ብለው ሰዎች ለኢዮአብ ነገሩት። ኢዮአብም ወደ ንጉሥ ገብቶ፦ ምን አደረግህ? እነሆ፥ አበኔር መጥቶልህ ነበር፥ በደኅና እንዲሄድ ስለ ምን አሰናበትኸው? የኔር ልጅ አበኔር ያታልልህ ዘንድ፥ መውጫህንና መግቢያህንም ያውቅ ዘንድ፥ የምታደርገውንም ነገር ሁሉ ያስተውል ዘንድ እንደ መጣ አታውቅምን? አለው። ኢዮአብም ከዳዊት በወጣ ጊዜ መልእክተኞችን ከአበኔር በኋላ ላከ፥ ከሴይርም ጕድጓድም መለሱት። ዳዊት ግን ይህን አላወቀም። አበኔርም ወደ ኬብሮን በተመለሰ ጊዜ ኢዮአብ በበር ውስጥ በቆይታ ይናገረው ዘንድ ወደ አጠገቡ ወሰደው፥ በዚያም ለወንድሙ ለአሣሄል ደም ተበቅሎ ሆዱን መታው፥ ሞተም። በኋላም ይህ ነገር እንደ ተደረገ በሰማ ጊዜ፦ ከኔር ልጅ ከአበኔር ደም በእግዚአብሔር ዘንድ ለዘላለም እኔ ንጽሕ ነኝ፥ መንግሥቴም ንጽሕ ነው፥ በኢዮአብ ራስ ላይና በአባቱ ቤት ሁሉ ላይ ይምጣበት፥ በኢዮአብም ቤት ፈሳሽ ነገር ያለበት ወይም ለምጻም ወይም አንካሳ ወይም በሰይፍ የሚወድቅ ወይም እንጀራ የሌለው ሰው አይታጣ አለ። ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳም በሰልፍ በገባዖን ወንድማቸውን አሣሄልን ገድሎ ነበርና አበኔርን ገደሉት። ዳዊትም ኢዮአብንና ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ሁሉ፦ ልብሳችሁን ቅደዱ፥ ማቅም ልበሱ፥ በአበኔርም ፊት አልቅሱ አላቸው። ንጉሡም ዳዊት ከቃሬዛው በኋላ ሄደ። አበኔርንም በኬብሮን ቀበሩት፥ ንጉሡም ድምፁን ከፍ አድርጎ በአበኔር መቃብር አጠገብ አለቀሰ፥ ሕዝቡም ሁሉ አለቀሱ። ንጉሡም ለአበኔር፦ አበኔር ሰነፍ እንደሚሞት ይሞታልን? እጅህ አልታሰረም፥ እግርህም በሰንሰለት አልተያዘም፥ ሰው በዓመፀኞች ፊት እንደሚወድቅ አንተ እንዲሁ ወደቅህ ብሎ የልቅሶ ቅኔ ተቀኘለት። ሕዝቡም ሁሉ ዋይታ አብዝተው አለቀሱ። ሕዝቡም ሁሉ ገና ሳይመሽ ዳዊትን እንጀራ ይበላ ዘንድ ሊጋብዙት መጡ፥ ዳዊት ግን፦ ፀሐይ ሳትጠልቅ እንጀራ ወይም ሌላ ነገር ብቀምስ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፥ ይህንም ይጨምርብኝ ብሎ፥ ማለ። ሕዝቡም ሁሉ ይህን ተመለከቱ፥ ደስ አሰኛቸውም፥ በሕዝቡም ሁሉ ፊት ንጉሥ ያደረገው ሁሉ ደስ አሰኛቸው። በዚያም ቀን ሕዝቡ ሁሉ እስራኤልም ሁሉ የኔር ልጅ የአበኔር ሞት ከንጉሡ ዘንድ እንዳልሆነ አወቁ። ንጉሡም ባሪያዎቹን፦ ዛሬ በእስራኤል ዘንድ መኮንንና ታላቅ ሰው እንደ ወደቀ አታውቁምን? እኔም ዛሬ ምንም ለመንገሥ የተቀባሁ ብሆን ደካማ ነኝ፥ እነዚህም ሰዎች የጽሩያም ልጆች በርትተውብኛል፥ እግዚአብሔር ክፋት በሠራ ላይ እንደ ክፋቱ ይመልስበት አላቸው።