የዳዊትና የኢዮአብ ሰዎች በዚያ ጊዜ ብዙ ምርኮ ይዘው ከዘመቻ ተመለሱ። አበኔር ግን ዳዊት በሰላም አሰናብቶት ስለ ሄደ፣ በኬብሮን አልነበረም። ኢዮአብና ዐብሮት የነበረው ሰራዊት ሁሉ እዚያ እንደ ደረሱ፣ የኔር ልጅ አበኔር ወደ ንጉሡ መምጣቱን፣ ንጉሡ እንዳሰናበተውና እርሱም በሰላም እንደ ሄደ፣ ኢዮአብ ሰማ። ስለዚህ ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ገብቶ እንዲህ አለ፤ “ምን ማድረግህ ነው? እነሆ አበኔር መጥቶልህ እንዴት በሰላም እንዲሄድ አሰናበትኸው? የኔርን ልጅ አበኔርን ታውቀዋለህ፤ የመጣው ሊያታልልህ፣ መውጣት መግባትህን ለማወቅና የምታደርገውን ሁሉ ሊሰልል ነው።” ከዚያም ኢዮአብ ከዳዊት ዘንድ ወጣ፤ አበኔርን እንዲያመጡትም መልክተኞች ላከ፤ መልክተኞቹም ከሴይር የውሃ ጕድጓድ አጠገብ መለሱት። ዳዊት ግን ይህን አላወቀም ነበር። አበኔር ወደ ኬብሮን በተመለሰ ጊዜ፣ ኢዮአብ በቈይታ የሚያነጋግረው በመምሰል ዞር አድርጎ ወደ ቅጽሩ በር ይዞት ሄደ፤ እዚያም የወንድሙን የአሣሄልን ደም ለመበቀል ሲል፣ ሆዱ ላይ ወግቶ ገደለው። ዳዊት ይህን ነገር ቈይቶ በሰማ ጊዜ እንዲህ አለ፤ “እኔም ሆንሁ መንግሥቴ ከኔር ልጅ ከአበኔር ደም በእግዚአብሔር ፊት ለዘላለም ንጹሕ ነን፤ ደሙ በኢዮአብ ራስና በአባቱ ቤት ሁሉ ላይ ይሁን፤ ፈሳሽ ነገር የሚወጣው ወይም አሠቃቂ የቈዳ በሽታ ያለበት፣ በምርኵዝ የሚሄድ ዐንካሳ፣ ወይም በሰይፍ ተመትቶ የሚወድቅ ወይም የሚበላው ያጣ ራብተኛ ከኢዮአብ ቤት አይታጣ።” አበኔር ገባዖን ላይ በተደረገው ጦርነት የኢዮአብንና የአቢሳን ወንድም አሣሄልን ገድሎት ስለ ነበር፣ እነርሱም አበኔርን ገደሉት። ከዚያም ዳዊት ለኢዮአብና ዐብሮት ለነበረው ሕዝብ ሁሉ፣ “ልብሳችሁን ቀድዳችሁ፣ ማቅ ለብሳችሁ በአበኔር ፊት አልቅሱ” አላቸው፤ ራሱ ንጉሥ ዳዊትም አስከሬኑን አጀበ። ከዚያም አበኔርን በኬብሮን ቀበሩት፤ ንጉሡም በአበኔር መቃብር ላይ ጮኾ አለቀሰ፤ ሕዝቡም ሁሉ እንደዚሁ አለቀሱ። ንጉሡም ለአበኔር ይህን የሐዘን እንጕርጕሮ ተቀኘ፤ “አበኔር እንደ ሞኝ ሰው ይሙት? እጆችህ አልታሰሩም፤ እግሮችህ በእግር ብረት አልገቡም፤ ሰው በክፉ ሰዎች ፊት እንደሚወድቅ አንተም እንደዚሁ ወደቅህ።” ሕዝቡም ሁሉ እንደ ገና አለቀሱለት። ከዚያም ሕዝቡ ሁሉ እህል በሚቀምስበት ሰዓት ወደ ዳዊት መጥተው ምግብ እንዲበላ አጥብቀው ለመኑት። ዳዊት ግን፣ “ፀሓይ ከመጥለቋ በፊት እንጀራ ወይም ሌላ ነገር ብቀምስ፣ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ ከዚህም የባሰ ያምጣብኝ” ብሎ ማለ። ሕዝቡም ሁሉ ይህንኑ ተመለከቱ፤ ደስም አላቸው፤ በርግጥ ንጉሡ ያደረገው ሁሉ ሕዝቡን ደስ አሠኛቸው። እንዲሁም በዚያ ዕለት ሕዝቡ ሁሉና እስራኤል በሙሉ ንጉሡ በኔር ልጅ በአበኔር ሞት እጁ እንዳልገባበት ዐወቁ። ከዚያም ንጉሡ ለራሱ ሰዎች እንዲህ አለ፤ “በዛሬዪቱ ዕለት በእስራኤል መስፍንና ታላቅ ሰው መውደቁን አላወቃችሁምን? ምንም እንኳ ዛሬ የተቀባሁ ንጉሥ ብሆንም፣ እኔ ደካማ ሰው ነኝ፤ እነዚህ የጽሩያ ልጆች እጅግ በርትተውብኛል። እግዚአብሔር ለክፉ አድራጊ የእጁን ይስጠው።”
2 ሳሙኤል 3 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ሳሙኤል 3
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ሳሙኤል 3:22-39
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች