የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 22:26-51

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 22:26-51 አማ54

ከቸር ሰው ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፥ ከቅን ሰው ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፥ ከንጹሕ ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፥ ከጠማማም ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ። አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህና፥ የትዕቢተኞችን ዓይን ግን ታዋርዳለህ። አቤቱ፥ አንተ መብራቴ ነህና፥ እግዚአብሔርም ጨለማዬን ያበራል። በአንተ ኃይል በጭፍራ ላይ እሮጣለሁና፥ በአምላኬም ቅጥሩን እዘልላለሁና። የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው፥ የእግዚአብሔር ቃል የነጠረ ነው፥ በእርሱ ለሚታመኑት ሁሉ ጋሻ ነው። ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን ነው? ከአምላካችንስ በቀር አምባ ማን ነው? ኃይልን የሚያስታጥቀኝ፥ መንገዴንም የሚያቃና፥ እግሮቼን እንደ ብሆር እግሮች የሚያረታ፥ በኮረብቶችም የሚያቆመኝ እግዚአብሔር ነው። እጆቼን ሰልፍ ያስተምራል፥ በክንዴ የናስ ቀስት እገትራለሁ። የማዳንህንም ጋሻ ሰጠኸኝ፥ ተግሣጽህም አሳደገኝ። አረማመዴን በበታቼ አሰፋህ፥ እግሮቼም አልተንሸራተቱም። ጠላቶቼን አሳድዳቸዋለሁ፥ አጠፋቸውማለሁ፥ እስካጠፋቸውም ድረስ አልመለስም። አስጨንቃቸዋለሁ መቆምም አይችሉም፥ ከእግሬም በታች ይወድቃሉ። ለሰልፍም ኃይልን ታስታጥቀኛለህ፥ በላዬ የቆሙትን በበታቼ ታስገዛቸዋለህ። የጠላቶቼን ጀርባ ሰጠኸኝ፥ የሚጠሉኝንም አጠፋሃቸው። ጮኹ፥ የሚረዳቸውም አልነበረም፥ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ አልሰማቸውምም። እንደ ምድር ትቢያ ፈጨኋቸው፥ እንደ አደባባይም ጭቃ ረገጥኋቸው፥ ደቀደቅኋቸውም። ከሕዝብ ክርክር ታድነኛለህ፥ የአሕዛብም ራስ አድርገህ ትሾመኛለህ፥ የማላውቀው ሕዝብም ይገዛልኛል። የባዕድ ልጆች ደለሉኝ፥ በጆሮ ሰምተው ተገዙልኝ። የባዕድ ልጆች እየጠፉ ይሄዳሉ፥ ከተዘጉ ስፍሮች እየተንቀጠቁ ይወጣሉ። እግዚአብሔር ሕያው ነው፥ ጠባቂዬም፥ ቡሩክ ነው፥ የመድኃኒቴ ጠባቂ አምላኬ ከፍ ከፍ ይበል፥ በቀሌን የሚመልስልኝ አምላክ፥ አሕዛብን በበታቼ የሚያስገዛ፥ ከጠላቶቼ የሚያወጣኝ እርሱ ነው፥ በእኔም ላይ ከቆሙ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፥ ከግፈኛ ሰው ታድነኛለህ። አቤቱ፥ ስለዚህ በአሕዛብ ዘንድ አመሰግንሃለሁ፥ ለስምህም እዘምራለሁ። የንጉሡን መድኃኒት ታላቅ ያደርጋል፥ ቸርነቱንም ለቀባው፥ ለዳዊትና ለዘሩ፥ ለዘላለም ይሰጣል።