የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ሳሙኤል 22:26-51

2 ሳሙኤል 22:26-51 NASV

“ለታማኝ ሰው አንተም ታማኝ መሆንህን፣ ለቅን ሰው አንተም ቅን መሆንህን ታሳያለህ። ለንጹሕ ሰው አንተም ንጹሕ መሆንህን፣ ለጠማማ ሰው ግን አንተም ጠማማ መሆንህን ታሳያለህ። አንተ የተጠቃውን ሕዝብ ታድናለህ፤ ዐይንህ ግን ያዋርዳቸው ዘንድ፣ ትዕቢተኞችን ይመለከታል። እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ መብራቴ ነህ፤ እግዚአብሔርም ጨለማዬን ያበራል። በአንተ ርዳታ በጠላት ሰራዊት ላይ ወደ ፊት ገፍቼ እሄዳለሁ፤ በአምላኬም ኀይል ቅጥሩን እዘላለሁ። “የአምላክ መንገዱ ፍጹም ነው፤ የእግዚአብሔርም ቃል የነጠረ ነው፤ ለሚታመኑበትም ሁሉ ጋሻ ነው፤ ከእግዚአብሔር በቀር አምላክ ማን አለና፤ ከአምላካችንስ በቀር ዐለት ማን ነው? ኀይልን የሚያስታጥቀኝ፣ መንገዴንም የሚያቀና እርሱ አምላኬ ነው። እግሮቼን እንደ ብሆር እግሮች ያበረታል፤ በከፍታዎችም ላይ አጽንቶ ያቆመኛል። እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናል፤ ክንዶቼም የናስ ቀስት ይገትራሉ። የማዳንህን ጋሻ ሰጥተኸኛል፤ ድጋፍህ ታላቅ አድርጎኛል። ርምጃዬን አሰፋህ፤ እግሮቼም አልተሰነካከሉም። “ጠላቶቼን አሳደድሁ፤ አጠፋኋቸውም፤ እስኪደመሰሱም ድረስ ወደ ኋላ አልተመለስሁም። ፈጽሜ አጠፋኋቸው፤ ተመልሰውም መቆም አልቻሉም፤ ከእግሬም ሥር ወድቀዋል። ለጦርነት ኀይልን አስታጠቅኸኝ፣ ተቃዋሚዎቼንም ከእግሬ ሥር አንበረከክሃቸው። ጠላቶቼ ፊታቸውን አዙረው እንዲሸሹ አደረግሃቸው። ባላንጣዎቼንም ደመሰስኋቸው። ለርዳታ ጮኹ፤ ያዳናቸው ግን አልነበረም፤ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እርሱ ግን አልመለሰላቸውም። በምድር ላይ እንዳለ ትቢያ አድቅቄ ፈጨኋቸው፤ በመንገድም ላይ እንዳለ ጭቃ ወቀጥኋቸው፤ ረገጥኋቸውም። “በሕዝቤ ከተቃጣብኝ አደጋ አዳንኸኝ፤ የመንግሥታትም ራስ አደረግኸኝ። የማላውቀው ሕዝብ ተገዛልኝ፤ ባዕዳን ሊለማመጡኝ መጡ፤ እንደ ሰሙኝም ወዲያውኑ ይታዘዙኛል። ባዕዳን ፈሩ፤ ከምሽጋቸውም እየተንቀጠቀጡ ወጡ። “እግዚአብሔር ሕያው ነው፤ ዐለቴ የተባረከ ይሁን፤ የድነቴ ዐለት አምላኬ ከፍ ከፍ ይበል። የሚበቀልልኝ አምላክ፣ መንግሥታትንም ከሥሬ የሚያስገዛልኝ እርሱ ነው፤ እርሱ ከጠላቶቼ እጅ ነጻ ያወጣኛል። አንተ ከጠላቶቼ በላይ ከፍ ከፍ አደረግኸኝ፤ ከጨካኝ ሰዎችም እጅ ታደግኸኝ። ስለዚህ እግዚአብሔር ሆይ፤ በመንግሥታት መካከል አመሰግንሃለሁ፤ ለስምህም ምስጋና እዘምራለሁ። “ለንጉሡ ታላቅ ድል ይሰጠዋል፤ ለቀባው ለዳዊትና ለዘሩ፣ ለዘላለም የማይለወጥ ፍቅሩን ያሳየዋል።”