ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 21
21
1በዳዊትም ዘመን ሦስት ዓመት ያህል ቀጥሎ ቀጥሎ ራብ ሆነ፥ ዳዊትም የእግዚአብሔርን ፊት ጠየቀ። እግዚአብሔርም፦ የገባዖንን ሰዎች ስለ ገደለ በሳኦልና በቤቱ ላይ ደም አለበት አለ። 2ንጉሡም የገባዖንን ሰዎች ጠራ፥ የገባዖን ሰዎችም ከአሞራውያን የተረፉ ነበሩ እንጂ ከእስራኤል ልጆች ወገን አልነበሩም፥ የእስራኤልም ልጆች ምለውላቸው ነበር፥ ሳኦል ግን ለእስራኤል ልጆችና ለይሁዳ ስለ ቀና ሊገድላቸው ወድዶ ነበር። 3ዳዊትም የገባዖንን ሰዎች፦ የእግዚአብሔርን ርስት ትባርኩ ዘንድ ምን ላድርግላችሁ? ማስተሰረያውስ ምንድር ነው? አላቸው። 4የገባዖን ሰዎችም፦ በእኛና በሳኦል ወይም በእኛና በቤቱ መካከል ያለው የብርና የወርቅ ነገር አይደለም፥ ከእስራኤልም ወገን እኛ የምንገድለው የለም አሉት። እርሱም፦ የምትናገሩትን አደርግላችኋለሁ አለ። 5ንጉሡንም፦ እኛን ካጠፋ፥ ከእስራኤል ዳርቻ ሁሉ እንዳንቀመጥ መፍረሳችንን 6ካሰበው ሰው ልጆች ሰባት ሰዎች አሳልፈህ ስጠንና ከእግዚአብሔር በተመረጠው በሳኦል አገር በጊብዓ ለእግዚአብሔር እንሰቅላቸዋለን አሉት። ንጉሡም፦ እሰጣችኋለሁ አለ።
7ንጉሡም በሳኦል ልጅ በዮናታንና በዳዊት መካከል ስለ ነበረው ስለ እግዚአብሔር መሐላ የሳኦልን ልጅ የዮናታንን ልጅ ሜምፊቦስቴን አዳነ። 8ንጉሡም ለሳኦል የወለደቻቸውን የኢዮሄል ልጅ የሪጽፋን ሁለቱን ልጆች ሄርሞንንና ሜምፊቦስቴን ለመሓላታዊውም ለቤርዜሊ ልጅ ለኤስድሪኤል የወለደቻቸውን የሳኦልን ልጅ የሜሮብን አምስቱን ልጆች ወሰደ፥ 9ለገባዖንም ሰዎች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው፥ በእግዚአብሔርም ፊት በተራራው ላይ ሰቀሉአቸው፥ ሰባቱም በአንድነት ወደቁ፥ እህል በሚታጨድበት ወራት በገብሱ መከር መጀመሪያ ተገደሉ።
10የኢዮሄልም ልጅ ሪጽፋ ማቅ ወስዳ ከመከር ወራት ጀምሮ ዝናብ ከሰማይ እስኪዘንብ ድረስ በድንጋይ ላይ ዘረጋችው በቀንም ወፎች በሌሊትም አራዊት ያርፉባቸው ዘንድ አልተወችም። 11የሳኦልም ቁባት የኢዮሄል ልጅ ሪጽፋ ያደረገችውን ለዳዊት ነገሩት። 12ዳዊትም ሄደ፥ ሳኦልንም በጊልቦዓ በገደሉ ጊዜ ፍልስጥኤማውያን ከሰቀሉአቸው ስፍራ ከቤትሳን አደባባይ ከሰረቁት ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ወሰደ፥ 13ከዚያም የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት ይዞ መጣ፥ የተሰቀሉትንም ሰዎች አጥንት ሰበሰቡ። 14የሳኦልንና የልጁን የዮናታንን አጥንት በብንያም አገር በጼላ በአባቱ በቂስ መቃብር ቀበሩት፥ ንጉሡም ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ። ከዚያም በኋላ እግዚአብሔር ስለ አገሩ የተለመነውን ሰማ።
15በፍልስጥኤማውያንና በእስራኤልም መካከል ደግሞ ሰልፍ ነበረ፥ ዳዊትም ከእርሱም ጋር ባሪያዎቹ ወረዱ፥ ከፍልስጥኤማውያንም ጋር ተዋጉ፥ ዳዊትም ደከመ። 16ከራፋይም ወገን የነበረው ይሽቢብኖብ ዳዊትን ይገድል ዘንድ አሰበ፥ የጦሩም ሚዛን ክብደት ሦስት መቶ ሰቅል ናስ ነበረ፥ አዲስም የጦር መሣሪያ ታጥቆ ነበር። 17የጽሩያም ልጅ አቢሳ አዳነው፥ ፍልስጥኤማዊውንም መትቶ ገደለው። ያንጊዜም የዳዊት ሰዎች፦ አንተ የእስራኤልን መብራት እንዳታጠፋ ከእንግዲህ ወዲህ ከእኛ ጋር ለሰልፍ አትወጣም ብለው ማሉለት።
18ከዚህም በኋላ እንደ ገና በጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ሆነ፥ ኩሳታዊውም ሴቦካይ ከራፋይም ወገን የነበረውን ሳፍን ገደለ። 19ደግሞም በጎብ ላይ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ሰልፍ ነበረ፥ የቤተልሔማዊውም የየዓሬኦርጊም ልጅ ኤልያናን የጦሩ የቦ እንደ ሸማኔ መጠቅለያ የነበረውን የጌት ሰው ጎልያድን ገደለ። 20ደግሞም በጌት ላይ ሰልፍ ሆነ፥ በዚያም በእጅና በእግሩ ስድስት ስድስት ሁላሁሉ ሀያ አራት ጣቶች የነበሩት አንድ ረጅም ሰው ነበረ፥ እርሱ ደግሞ ከራፋይም የተወለደ ነበረ። 21እስራኤልንም በተገዳደረ ጊዜ የዳዊት ወንድም የሣማ ልጅ ዮናታን ገደለው። 22እነዚህም አራቱ በጌት ውስጥ ከራፋይም የተወለዱ ነበሩ፥ በዳዊትም እጅ በባሪያዎቹም እጅ ወደቀ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 21: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ