የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 20

20
1እንዲህም ሆነ፥ አንድ ብንያማዊ የቢክሪ ልጅ ስሙ ሳቤዔ የሚባል ምናምንቴ ሰው ነበረ፥ እርሱም፦ ከዳዊት ዘንድ እድል ፈንታ የለንም፥ ከእሴይም ልጅ ዘንድ ርስት የለንም፥ እስራኤል ሆይ፥ እያንዳንድህ ወደ ድንኳንህ ተመለስ ብሎ ቀንደ መለከት ነፋ። 2የእስራኤልም ሰዎች ሁሉ ከዳዊት ተለይተው የቢክሪን ልጅ ሳቤዔን ተከተሉ፥ የይሁዳ ሰዎች ግን ከዮርዳኖስ ጀምረው ኢየሩሳሌም እስኪደርሱ ንጉሣቸውን ተከተሉ።
3ዳዊትም ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ቤቱ መጣ፥ ንጉሡም ቤቱን ሊጠብቁ የተዋቸውን አሥሩን ቁባቶች ወስዶ ለጠባቂ ሰጣቸው፥ ቀለብም ሰጣቸው፥ ነገር ግን ወደ እነርሱ አልገባም፥ በቤት ተዘግተው እስኪሞቱም ድረስ ባልቴቶች ሆነው ተቀመጡ።
4ንጉሡም አሜሳይን፦ የይሁዳን ሰዎች ሁሉ በሦስት ቀን ውስጥ ጥራልኝ፥ አንተም አብረህ በዚህ ሁን አለው። 5አሜሳይም የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ይጠራ ዘንድ ሄደ፥ ነገር ግን እርሱ የተቀጠረውን ቀን አሳልፎ ዘገየ። 6ዳዊትም አቢሳን፦ አሁን ከአቤሴሎም ይልቅ የሚጎዳን የቢክሪ ልጅ ሳቤዔ ነው፥ እርሱ የተመሸጉትን ከተሞች አግኝቶ ከዓይናችን እንዳያመልጥ፥ አንተ የጌታህን ባሪያዎች ወስደህ አሳድደው አለው። 7አቢሳንም ተከትለው የኢዮአብ ሰዎች ከሊታውያንም ፈሊታው ያንም ኃያላንም ሁሉ ሄዱ፥ የቢክሪንም ልጅ ሳቤዔን ለማሳደድ ከኢየሩሳሌም ወጡ። 8በገባዖንም ወዳለው ወደ ታላቁ ድንጋይ በደረሱ ጊዜ አሜሳይ ሊገናኛቸው መጣ፥ ኢዮአብም የሰልፍ ልብስ ለብሶ ነበር፥ በላዩም መታጠቂያ ነበረ፥ በወገቡም ላይ ሰገባ ያለው ሰይፍ ታጥቆ ነበር፥ እርሱም ሲራመድ ሰይፉ ወደቀ። 9ኢዮአብም አሜሳይን፦ ወንድሜ ሆይ፥ ደኅና ነህን? አለው ኢዮአብም አሜሳይን የሚስም መስሎ በቀን እጁ ጢሙን ያዘው። 10አሜሳይ ግን በኢዮአብ እጅ ከነበረው ሰይፍ አልተጠነቀቀም ነበር፥ ኢዮአብም ሆዱን ወጋው፥ አንጀቱንም በምድር ላይ ዘረገፈው፥ ሁለተኛም አልወጋውም፥ ሞተም።
11ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳ የቢክሪን ልጅ ሳቤዔን አሳደዱ። ከኢዮአብም ብላቴኖች አንዱ በአሜሳይ ሬሳ አጠገብ ቆሞ፦ ለኢዮአብ ወዳጅ የሚሆን ለዳዊትም የሆነ ሁሉ ኢዮአብን ይከተል ይል ነበር። 12አሜሳይም በመንገድ መካከል ወድቆ በደሙ ላይ ይንከባለል ነበር፥ ያም ሰው ወደ እርሱ የሚመጣ ሁሉ ሲቆም አይቶአልና ሕዝቡ ሁሉ እንደ ቆመ ባየ ጊዜ አሜሳይን ከመንገድ ላይ ወደ እርሻ ውስጥ ፈቀቅ አደረገው፥ በልብስም ከደነው። 13ከመንገድ ራቅ ባለ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ የቢክሪን ልጅ ሳቤዔን ለማሳደድ ኢዮአብን ተከትሎ ያልፍ ነበር።
14እርሱ ግን ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ወደ አቤል፥ ወደ ቤትመዓካ፥ ወደ ቤሪም ሁሉ አለፈ፥ ሰዎችም ደግሞ ተሰብስበው ተከተሉት። 15በቤትመዓካ ባለ በአቤልም መጥተው ከበቡት፥ በከተማይቱም ላይ እስከ ቅጥርዋ ድረስ የአፈርን ድልድል ደለደሉ፥ ቅጥሩንም ያፈርሱ ዘንድ ከኢዮአብ ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ ይደባደቡ ነበር። 16ከከተማይቱም አንዲት ብልሃተኛ ሴት፦ ስሙ፥ ስሙ፥ ኢዮአብንም፦ እነግርህ ዘንድ ወደዚህ ቅረብ በሉት ስትል ጮኸች። 17ወደ እርስዋም ቀረበ፥ ሴቲቱም፦ ኢዮአብ አንተ ነህን? አለች። እርሱም፦ እኔ ነኝ ብሎ መለሰላት። እርስዋም፦ የባሪያህን ቃል ስማ አለችው። እርሱም፦ እሰማለሁ አላት። 18እርስዋም፦ ቀድሞ፦ የሚጠይቅ በአቤል ዘንድ ይጠይቅ ይባል ነበር፥ እንዲሁም ነገሩ ይፈጸም ነበር። 19በእስራኤል ዘንድ ሰላምንና እውነትን ከሚወድዱ እኔ ነኝ፥ አንተ በእስራኤል ያለችውን ከተማና እናት ለማፍረስ ትሻለህ፥ ስለ ምንስ የእግዚአብሔርን ርስት ትውጣለህ? ብላ ተናገረች። 20ኢዮአብም መልሶ፦ ይህ መዋጥና ማጥፋት ከእኔ ይራቅ፥ 21ነገሩ እንዲህ አይደለም፥ ከተራራማው ከኤፍሬም አገር የሚሆን የቢክሪ ልጅ ሳቤዔ የሚባል አንድ ሰው ግን በንጉሡ በዳዊት ላይ እጁን አነሣ፥ እርሱን ብቻውን ስጡኝ፥ እኔም ከከተማይቱ እርቃለሁ አላት። ሴቲቱም ኢዮአብን፦ እነሆ፥ ራሱ ከቅጥር ላይ ይጣልልሃል አለችው። 22ሴቲቱም በልሃትዋ ወደ ሕዝቡ ሁሉ ሄደች፥ እነርሱም የቢክሪን ልጅ የሳቤዔን ራስ ቆርጠው ወደ ኢዮአብ ጣሉት። እርሱም ቀንደ መለከቱን ነፋ፥ ሰውም ሁሉ ከከተማይቱ ርቆ እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሄደ። ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
23ኢዮአብም በእስራኤል ሠራዊት ሁሉ ላይ አለቃ ነበር፥ የዩዳሄም ልጅ በናያስ በከሊታውያንና በፈሊታውያን ላይ ነበረ፥ 24አዶኒራምም ግብር አስገባሪ ነበረ፥ የአሒሉድም ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሐፊ ነበረ፥ 25ሱሳም ጸሐፊ ነበረ፥ ሳዶቅና አብያታርም ካህናት ነበሩ፥ 26የኢያዕር ሰውም ዒራስ ለዳዊት አማካሪ ነበረ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ