ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19
19
1ኢዮአብም ንጉሡ ስለ አቤሴሎም እንዳለቀሰና ዋይ ዋይ እንዳለ ሰማ። 2በዚያም ቀን፦ ንጉሡ ስለ ልጁ አዘነ ሲባል ሕዝቡ ሰምቶአልና የዚያ ቀን ድል በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ ወደ ኅዘን ተለወጠ። 3ሕዝቡም ከሰልፍ የሸሸ ሕዝብ አፍሮ ወደ ኋላው እንዲል በዚያ ቀን ወደ ከተማ ተሰርቆ ገባ። 4ንጉሡም ፊቱን ሸፈነ፥ ንጉሡም በታላቅ ድምፅ፦ ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ እያለ ይጮኽ ነበር። 5ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ወደ ቤት ገብቶ እንዲህ አለ፦ ዛሬ ነፍስህንና የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ነፍስ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ነፍስ ያዳኑትን የባሪያዎችህን ሁሉ ፊት ዛሬ አሳፍረሃል፥ 6አንተ የሚጠሉህን ትወድዳለህ፦ የሚወድዱህንም ትጠላለህ። መሳፍንትህና ባሪያዎችህን እንዳታስብ ዛሬ ገልጠሃል፥ ዛሬ ሁላችን ሞተን ቢሆን ኖር አቤሴሎምም ድኖ ቢሆን ኖሮ ደስ ያሰኘህ እንደ ነበረ ዛሬ አያለሁ። 7አሁን እንግዲህ ተነሥተህ ውጣ፥ ለባሪያዎችህም የሚያጽናናቸውን ነገር ተናገራቸው፥ ያልወጣህ እንደ ሆነ ግን አንድ ሰው ከአንተ ጋር በዚህች ሌሊት እንዳይቀር በእግዚአብሔር እምላለሁ፥ ይህም ከብላቴናነትህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ካገኘህ ክፉ ነገር ሁሉ ይልቅ ታላቅ መከራ ይሆንብሃል። 8ንጉሡም ተነሥቶ በበሩ ተቀመጠ፥ ሕዝቡም ሁሉ ንጉሡ በበሩ እንደተቀመጠ ሰማ፥ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ንጉሡ ፊት መጣ።
9እስራኤልም እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሸሽቶ ነበር። ሕዝቡም ሁሉ በእስራኤል ነገድ ሁሉ ውስጥ፦ ንጉሡ ከጠላቶቻችን እጅ ታድጎናል፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ አድኖናል፥ አሁንም ስለ አቤሴሎም ከአገር ሸሽቶአል። 10በላያችን እንዲሆን የቀባነው አቤሴሎም በሰልፍ ሞቶአል፥ አሁንም እንግዲህ ንጉሡን ለመመለስ ስለ ምን ዝም ትላላችሁ? እያለ እርስ በርሱ ይከራከር ነበር።
11ንጉሡም ዳዊት ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር ልኮ እንዲህ አላቸው፦ ለይሁዳ ሽማግሌዎች እንዲህ ብላችሁ ተናገሩአቸው፦ የእስራኤል ሁሉ ነገር ወደ ንጉሡ ደርሶአልና ንጉሡን ወደ ቤቱ ከመመለስ ስለ ምን ዘገያችሁ? 12እናንተ ወንድሞቼ፥ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቁራጭ ናችሁ፥ እናንተ ንጉሡን ከመመለስ ስለ ምን ዘገያችሁ? 13ለአሜሳይም፦ አንተ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቁራጭ አይደለህምን? በዘመንህም ሁሉ በኢዮአብ ፋንታ በፊቴ የሠራዊት አለቃ ሳትሆን ብትቀር እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ ይህንም ይጨምርብኝ በሉት። 14የይሁዳንም ሰዎች ሁሉ ልብ እንደ አንድ ሰው ልብ አድርጎ አዘነበለ፥ ወደ ንጉሡም ልከው፦ አንተ ከባሪያዎችህ ሁሉ ጋር ተመለስ አሉት።
15ንጉሡም ተመልሶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ መጣ። የይሁዳ ሰዎች ንጉሡን ሊቀበሉ ንጉሡንም ዮርዳኖስን ሊያሻግሩ ወደ ጌልገላ መጡ። 16ከብራቂምም አገር የነበረው ብንያማዊው የጌራ ልጅ ሳሚ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ዳዊትን ሊቀበል ፈጥኖ ወረደ። 17ከእርሱም ጋር ብንያማውያን የሆኑ ሺህ ሰዎች ነበሩ፥ የሳኦልም ቤት ባሪያ ሲባ ከእርሱም ጋር አሥራ አምስቱ ልጆችና ሀያው ባሪያዎች ነበሩ፥ በንጉሡም ፊት ፈጥነው ዮርዳኖስን ተሻገሩ። 18ታንኳውም የንጉሥን ቤተ ሰብ ያሻግር ዘንድ ንጉሡም ደስ ያሰኘውን ያደርግ ዘንድ ይሸጋገር ነበር። ንጉሡም ዮርዳኖስን ከተሻገረ በኋላ የጌራ ልጅ ሳሚ በፊቱ ተደፋ። 19ንጉሡንም፦ ጌታዬ ሆይ፥ ኃጢአቴን አትቍጠርብኝ፥ ጌታዬ ንጉሡ፥ ከኢየሩሳሌም በወጣህ ቀነ ባሪያህ የበደልሁህን አታስብብኝ፥ ንጉሡም በልቡ አያኑረው። 20ባሪያህ በደለኛ እንደ ሆንሁ አውቄአለሁና እነሆ፥ ከዮሴፍ ቤት ሁሉ አስቀድሜ ዛሬ መጣሁ፥ ጌታዬንም ንጉሡን ልቀበል ወረድሁ አለው። 21የጽሩያ ልጅ አቢሳ ግን፦ ሳሚ እግዚአብሔር የቀባውን ሰድቦአልና ሞት የተገባው አይደለምን? አለ። 22ዳዊትም፦ እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ዛሬ ስለ ምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ? ዛሬስ በእስራኤል ዘንድ ሰው ሊሞት ይገባልን? ዛሬስ በእስራኤል ላይ እንደ ነገሥሁ አላወቅሁምን? አለ። 23ንጉሡም ሳሚን፦ አትሞትም አለው። ንጉሡም ማለለት።
24የሳኦልም ልጅ ሜምፊቦስቴ ንጉሡን ሊቀበል ወረደ፥ ንጉሡም ከሄደ ጀምሮ በደኅና እስከ ተመለሰበት ቀን ድረስ እግሩን አልጠገነም፥ ጢሙንም አልቆረጠም፥ ልብሱንም አላጠበም ነበር። 25ንጉሡም ሊቀበለው ከኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፦ ሜምፊቦስቴ ሆይ፥ ከእኔ ጋር ስለ ምን አልወጣህም? አለው። 26እርሱም መልሶ አለ፦ ጌታዬ፥ ንጉሥ ሆይ፥ ባሪያዬ አታለለኝ፥ እኔ ባሪያህ አንካሳ ነኝና፦ ከንጉሥ ጋር እሄድ ዘንድ የምቀመጥበትን አህያ ልጫን አልሁት። 27እርሱም እኔን ባሪያህን ለጌታዬ ለንጉሡ አማ፥ አንተ ጌታዬ ንጉሥ ግን እንደ እግዚአብሔር መልአክ ነህ፥ ደስም ያሰኘህን አድርግ። 28የአባቴ ቤት ሁሉ በጌታዬ በንጉሡ ዘንድ ሞት የሚገባቸው ነበሩ፥ አንተ ግን እኔን ባሪያህን በገበታህ በሚበሉ መካከል አስቀመጥኸኝ፥ ለንጉሥ ደግሞ ለመናገር ምን መብት አለኝ? 29ንጉሡም፦ ነገርህን ለምን ታበዛለህ? አንተና ሲባ እርሻውን ትካፈሉ ዘንድ ብያለሁ አለው። 30ሜምፊቦስቴም ንጉሡን፦ ጌታዬ ንጉሡ በደኅና ወደ ቤቱ ከተመለሰ እርሱ ሁሉን ይውሰደው አለው።
31ገለዓዳዊውም ቤርዜሊ ከሮግሊም ወረደ፥ ሊሸኘውም ከንጉሡ ጋር ዮርዳኖስን ተሻገረ። 32ቤርዜሊም እጅግ ያረጀ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነበረ፥ እጅግም ትልቅ ሰው ነበረና ንጉሡ በመሃናይም ሳለ ይቀልበው ነበር። 33ንጉሡም ቤርዜሊን፦ በኢየሩሳሌም እቀልብህ ዘንድ ከእኔ ጋር እለፍ አለው። 34ቤርዜሊም ንጉሡን አለው፦ ከንጉሡ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም እወጣ ዘንድ ከሕይወቴ ዘመን ምን ያህል ቀረኝ? 35ዛሬ የሰማንያ ዓመት ሽማግሌ ነኝ፥ መልካሙንና ክፉውን መለየት እችላለሁን? እኔ ባሪያህ የምበላውንና የምጠጣውን ጣዕሙን መለየት እችላለሁን? የወንዱንና የሴቲቱን ዘፈን ድምፅ መስማት እችላለሁን? እኔ ባሪያህ በጌታዬ በንጉሡ ላይ ለምን እከብድብሃለሁ? 36እኔ ባሪያህ ዮርዳኖስን ተሻግሬ ከንጉሡ ጋር ጥቂት ልሄድ ነበር፥ ንጉሡ እንዲህ ያለ ወረታ ለምን ይመልስልኛል? 37እኔ ባሪያህ ተመልሼ በከተማዬ በአባቴና በእናቴ መቃብር አጠገብ፥ እባክህ፥ ልሙት። ነገር ግን ባሪያህን ከመዓምን እይ፥ እርሱ ከጌታዬ ከንጉሡ ጋር ይለፍ፥ ደስ የሚያሰኝህንም ለእርሱ አድርግ። 38ንጉሡም፦ ከመዓም ከእኔ ጋር ይለፍ፥ ደስ የሚያሰኝህንም አደርግለታለሁ፥ አንተም ከእኔ የምትሻውን ሁሉ አደርግልሃለሁ አለው። 39ሕዝቡም ሁሉ ዮርዳኖስን ተሻገረ፥ ንጉሡም ተሻገረ፥ ንጉሡም ቤርዜሊን ሳመው፥ መረቀውም፥ ወደ ስፍራውም ተመለሰ።
40ንጉሡም ወደ ጌልገላ ተሻገረ፥ ከመዓምም ከእርሱ ጋር ሄደ፥ የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ ደግሞም የእስራኤል ሕዝብ እኩሌታ ንጉሡን አሻገረው። 41እነሆም፥ የእስራኤል ሰዎች ሁሉ ወደ ንጉሥ መጡ፥ ንጉሡንም፦ ወንድሞቻችን የይሁዳ ሰዎች ለምን ሰረቁህ? ንጉሡንም ቤተ ሰቡንም ከእርሱም ጋር የዳዊትን ሰዎች ሁሉ ዮርዳኖስን አሻገሩ? አሉት። 42የይሁዳም ሰዎች ሁሉ ለእስራኤል ሰዎች መልሰው፦ ንጉሡ ለእኛ ቅርባችን ነው፥ ስለ ምን በዚህ ነገር ትቆጣላችሁ? በውኑ ከንጉሡ አንዳች በልተናልን? ወይስ እርሱ በረከት ሰጥቶናልን? አሉ። 43የእስራኤልም ሰዎች ለይሁዳ ሰዎች መልሰው፦ በንጉሡ ዘንድ ለእኛ አሥር ክፍል አለን፥ በዳዊትም ዘንድ ደግሞ ከእናንተ ይልቅ መብት አለን፥ ስለ ምን ናቃችሁን? ስለ ምንስ ንጉሣችንን ለመመለስ ቀድሞ ምክር አልጠየቃችሁንም? አሉ። የይሁዳም ሰዎች ቃል ከእስራኤል ሰዎች ቃል ይልቅ ጠነከረ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ