ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 6:15-23

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 6:15-23 አማ54

የእግዚአብሔር ሰው ሎሌ ማለዳ ተነሥቶ በወጣ ጊዜ፥ እነሆ፥ በከተማይቱ ዙሪያ ጭፍራና ፈረሶች ሠረገሎችም ነበሩ። ሎሌውም “ጌታዬ ሆይ! ወዮ! ምን እናደርጋለን?” አለው። እርሱም “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ፤” አለው። ኤልሳዕም “አቤቱ፥ ያይ ዘንድ ዐይኖቹን እባክህ ግለጥ፤” ብሎ ጸለየ። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ዐይኖች ገለጠ፤ አየም፤ እነሆም፥ በኤልሳዕ ዙሪያ ያሉት የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች ተራራውን ሞልተውት ነበር። ወደ እርሱም በወረዱ ጊዜ ኤልሳዕ “ይህን ሕዝብ ዕውር ታደርገው ዘንድ እለምንሃለሁ፤” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ኤልሳዕም እንደ ተናገረው ቃል ዕውር አደረጋቸው። ኤልሳዕም “መንገዱ በዚህ አይደለም፤ ከተማይቱም ይህች አይደለችም፤ የምትሹትን ሰው አሳያችሁ ዘንድ ተከተሉኝ፤” አላቸው፤ ወደ ሰማርያም መራቸው። ወደ ሰማርያም በገቡ ጊዜ ኤልሳዕ “አቤቱ! ያዩ ዘንድ የእነዚህን ሰዎች ዐይኖች ግለጥ፤” አለ፤ እግዚአብሔርም ዐይኖቻቸውን ገለጠ፤ እነርሱም አዩ። እነሆም፥ በሰማርያ መካከል ነበሩ። የእስራኤልም ንጉሥ ባያቸው ጊዜ አልሳዕን “አባቴ ሆይ! ልግደላቸውን? ልግደላቸውን?” አለው። እርሱም “አትግደላቸው፤ በሰይፍህና በቀስትህ የማረክኸውን ትገድል ዘንድ ይገባሃልን? እንጀራና ውሃ በፊታቸው አኑርላቸው፤ በልተውና ጠጥተውም ወደ ጌታቸው ይሂዱ፤” አለው። ብዙም መብል አዘጋጀላቸው፤ በበሉና በጠጡ ጊዜም አሰናበታቸው፤ እነርሱም ወደ ጌታቸው ሄዱ። ከዚያም በኋላ የሶርያ አደጋ ጣዮች ወደ እስራኤል አገር አልመጡም።