የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 6

6
ሰጥሞ የነበረው መጥረቢያ በተአምር እንደ ተንሳፈፈ
1የነቢያት ልጆች ኤልሳዕን “እነሆ፥ በፊትህ የምንቀመጥበት ስፍራ ጠብቦናል። 2ወደ ዮርዳኖስም እንሂድ፤ ከእኛም እያንዳንዱ ከዚያ ምሰሶ ያምጣ፤ የምንቀመጥበትንም ስፍራ በዚያ እንሥራ፤” አሉት፤ እርሱም “ሂዱ” አለ። 3ከእነርሱም አንዱ “አንተ ደግሞ ከእኛ ከባሪያዎችህ ጋር ለመሄድ ፍቀድ፤” አለ። እርሱም “እሄዳለሁ” አለ። 4ከእነርሱም ጋር ሄደ፤ ወደ ዮርዳኖስም በደረሱ ጊዜ እንጨት ቆረጡ። 5ከእነርሱም አንዱ ምሰሶውን ሲቆርጥ የምሳሩ ብረት ወደ ውሃው ውስጥ ወደቀ፤ እርሱም “ጌታዬ ሆይ! ወየው! ወየው! የተዋስሁት ነበረ፤” ብሎ ጮኸ። 6የእግዚአብሔርም ሰው “የወደቀው ወዴት ነው?” አለ ስፍራውንም አሳየው፤ እንጨትም ቆርጦ በዚያ ጣለው፤ ብረቱም ተንሳፈፈ። 7እርሱም “ውሰደው፤ አለ፤ እጁንም ዘርግቶ ወሰደው።
የሶርያ ጦር ድል መሆን
8የሶርያም ንጉሥ ከእስራኤል ጋር ይዋጋ ነበር፤ ከባሪያዎቹም ጋር ተማክሮ “በዚህ ተደብቀን እንሰፍራለን፤” አለ። 9የእግዚአብሔርም ሰው “ሶርያውያን በዚያ ተደብቀዋልና በዚያ ስፍራ እንዳታልፍ ተጠንቀቅ፤” ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ላከ። 10የእስራኤልም ንጉሥ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ነገረው ስፍራ ሰደደ፤ አንድ ጊዜም ሳይሆን፥ ሁለት ጊዜም ሳይሆን በዚያ ራሱን አዳነ። 11የሶርያም ንጉሥ ልብ ስለዚህ እጅግ ታወከ፤ ባሪያዎቹንም ጠርቶ “ከእኛ ዘንድ ከእስራኤል ንጉሥ ጋር የተወዳጀ እንዳለ አትነግሩኝምን?” አላቸው። 12ከባሪያዎቹም አንዱ “ጌታዬ ሆይ! እንዲህ እኮ አይደለም፤ ነገር ግን በእልፍኝህ ውስጥ ሆነህ የምትናገረውን በእስራኤል ዘንድ ያለ ነቢይ ኤልሳዕ ለእስራኤል ንጉሥ ይነግረዋል፤” አለ። 13እርሱም “ልኬ አስይዘው ዘንድ ሄዳችሁ ወዴት እንደሆነ እዩ፤” አለ። እነርሱም “እነሆ፥ በዶታይን አለ፤” ብለው ነገሩት።
14ወደዚያም ፈረሶችንና ሠረገሎችን እጅግም ጭፍራ ሰደደ፤ በሌሊትም መጥተው ከተማይቱን ከበቡ። 15የእግዚአብሔር ሰው ሎሌ ማለዳ ተነሥቶ በወጣ ጊዜ፥ እነሆ፥ በከተማይቱ ዙሪያ ጭፍራና ፈረሶች ሠረገሎችም ነበሩ። ሎሌውም “ጌታዬ ሆይ! ወዮ! ምን እናደርጋለን?” አለው። 16እርሱም “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ፤” አለው። 17ኤልሳዕም “አቤቱ፥ ያይ ዘንድ ዐይኖቹን እባክህ ግለጥ፤” ብሎ ጸለየ። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ዐይኖች ገለጠ፤ አየም፤ እነሆም፥ በኤልሳዕ ዙሪያ ያሉት የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች ተራራውን ሞልተውት ነበር። 18ወደ እርሱም በወረዱ ጊዜ ኤልሳዕ “ይህን ሕዝብ ዕውር ታደርገው ዘንድ እለምንሃለሁ፤” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ኤልሳዕም እንደ ተናገረው ቃል ዕውር አደረጋቸው። 19ኤልሳዕም “መንገዱ በዚህ አይደለም፤ ከተማይቱም ይህች አይደለችም፤ የምትሹትን ሰው አሳያችሁ ዘንድ ተከተሉኝ፤” አላቸው፤ ወደ ሰማርያም መራቸው።
20ወደ ሰማርያም በገቡ ጊዜ ኤልሳዕ “አቤቱ! ያዩ ዘንድ የእነዚህን ሰዎች ዐይኖች ግለጥ፤” አለ፤ እግዚአብሔርም ዐይኖቻቸውን ገለጠ፤ እነርሱም አዩ። እነሆም፥ በሰማርያ መካከል ነበሩ። 21የእስራኤልም ንጉሥ ባያቸው ጊዜ አልሳዕን “አባቴ ሆይ! ልግደላቸውን? ልግደላቸውን?” አለው። 22እርሱም “አትግደላቸው፤ በሰይፍህና በቀስትህ የማረክኸውን ትገድል ዘንድ ይገባሃልን? እንጀራና ውሃ በፊታቸው አኑርላቸው፤ በልተውና ጠጥተውም ወደ ጌታቸው ይሂዱ፤” አለው። 23ብዙም መብል አዘጋጀላቸው፤ በበሉና በጠጡ ጊዜም አሰናበታቸው፤ እነርሱም ወደ ጌታቸው ሄዱ። ከዚያም በኋላ የሶርያ አደጋ ጣዮች ወደ እስራኤል አገር አልመጡም።
ቤንሀዳድ ሰማርያን እንደ ከበበ
24ከዚያም በኋላ የሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ ሠራዊቱን ሁሉ ሰበሰበ፤ ወጥቶም ሰማርያን ከበባት። 25በሰማርያም ታላቅ ራብ ሆኖ ነበር፤ እነሆም፥ የአህያ ራስ በአምሳ ብር፥ የርግብም ኩስ የጎሞር ስምንተኛ የሚሆን በአምስት ብር እስኪሸጥ ድረስ ከበቡአት። 26የእስራኤልም ንጉሥ በቅጥር ላይ በተመላለሰ ጊዜ አንዲት ሴት “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! እርዳኝ፤” ብላ ወደ እርሱ ጮኸች። 27እርሱም “እግዚአብሔር ያልረዳሽን እኔ እንዴት እረዳሻለሁ? ከአውድማው ወይስ ከመጥመቂያው ነውን?” አለ። 28ንጉሡም “ምን ሆነሻል?” አላት፤ እርስዋም “ይህች ሴት ‘ዛሬ እንድንበላው ልጅሽን አምጪ፤ ነገም ልጄን እንበላለን፤’ አለችኝ። 29ልጄንም ቀቅለን በላነው፤ በማግሥቱም ‘እንድንበላው ልጅሽን አምጪ፤’ አልኋት፤ ልጅዋንም ሸሸገችው፤” ብላ መለሰችለት። 30ንጉሡም የሴቲቱን ቃል ሰምቶ ልብሱን ቀደደ፤ በቅጥርም ይመላለስ ነበር፤ ሕዝቡም በስተ ውስጥ በሥጋው ላይ ለብሶት የነበረውን ማቅ አዩ። 31ንጉሡም “የሣፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ራስ ዛሬ በላዩ ያደረ እንደ ሆነ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ! ይህንም ይጨምርብኝ!” አለ።
32ኤልሳዕ ግን በቤቱ ተቀምጦ ነበር፤ ሽማግሌዎችም ከእርሱ ጋር ተቀምጠው ነበር፤ ንጉሡ ሰው ላከ፤ መልእክተኛውም ገና ሳይደርስ ለሽማግሌዎች “ይህ የነፍሰ ገዳይ ልጅ ራሴን ይቈርጥ ዘንድ እንደ ላከ እዩ፤ መልእከተኛውም በመጣ ጊዜ ደጁን ዘግታችሁ ከልክሉት፤ የጌታው የእግሩ ኮቴ በኋላው ነው፤” አላቸው። 33ሲናገራቸውም መልእክተኛው ወደ እርሱ ደረሰ፤ እርሱም “እነሆ፥ ይህ ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ እግዚአብሔርን ገና እጠብቅ ዘንድ ምንድር ነኝ?” አለ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ