የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 7

7
1ኤልሳዕም “የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል፥ ሁለትም መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ይሸመታል’” አለ። 2ንጉሡም በእጁ ተደግፎ የነበረ አለቃ ለእግዚአብሔር ሰው መልሶ “እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ መስኮቶች ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን?” አለው። እርሱም “እነሆ፥ በዐይኖችህ ታየዋለህ፤ ከዚያም አትቀምስም፤” አለ።
የሶርያ ጦር መሸሽ
3በበሩም መግቢያ አራት ለምጻም ሰዎች ነበሩ፤ እርስ በርሳቸውም “እስክንሞት ድረስ በዚህ ለምን እንቀመጣለን? 4ወደ ከተማ እንገባ ዘንድ ብንወድድ ራብ በከተማ አለ፤ በዚያም እንሞታለን፤ በዚህም ብንቀመጥ እንሞታለን። እንግዲህ ኑ፤ ወደ ሶርያውያን ሰፈር እንሽሽ፤ በሕይወት ቢያኖሩን እንኖራለን፤ ቢገድሉንም እንሞታለን፤” ተባባሉ። 5ጨለምለም ባለ ጊዜ ወደ ሶርያውያን ሰፈር ይሄዱ ዘንድ ተነሡ፤ ወደ ሶርያውያንም ሰፈር መጀመሪያ ዳርቻ በመጡ ጊዜ፥ እነሆ፥ ማንም አልነበረም። 6እግዚአብሔር ለሶርያውያን የሠረገላና የፈረስ የብዙም ጭፍራ ድምፅ አሰምቶ ነበር፤ እርስ በርሳቸውም “እነሆ፥ የእስራኤል ንጉሥ የኬጢያውያንና የግብጻውያንን ነገሥታት ቀጥሮ አምጥቶብናል፤” ይባባሉ ነበር። 7ስለዚህም ተነሥተው በጨለማ ሸሹ፤ ድንኳኖቻቸውንና ፈረሶቻቸውን አህዮቻቸውንና ሰፈሩን እንዳለ ትተው ነፍሳቸውን ያድኑ ዘንድ ሸሹ። 8እነዚህም ለምጻሞች ወደ ሰፈሩ መጀመሪያ ዳርቻ በመጡ ጊዜ ወደ አንድ ድንኳን ገብተው በሉ፤ ጠጡም፤ ከዚያም ወርቅና ብር ልብስም ወሰዱ፤ ሄደውም ሸሸጉት፤ ተመልሰውም ወደ ሌላ ድንኳን ገቡ፤ ከዚያም ደግሞ ወስደው ሸሸጉ።
9ከዚያም ወዲያ እርስ በርሳቸው “መልካም አላደረግንም፤ ዛሬ የመልካም ምስራች ቀን ነው፤ እኛም ዝም ብለናል፤ እስኪነጋም ድረስ ብንቆይ በደለኞች እንሆናለን፤ ኑ፤ እንሂድ፤ ለንጉሥ ቤተሰብ እንናገር፤” ተባባሉ። 10መጥተውም “ወደ ሶርያውያን ሰፈር መጣን፤ እነሆም፥ ፈረሶችና አህዮች ታስረው፥ ድንኳኖችም ተተክለው ነበር እንጂ ሰው አልነበረም፤ የሰውም ድምፅ አልነበረም፤” ብለው ወደ ከተማይቱ ደጅ ጠባቂ ጮኹ። 11የደጁም ጠባቂዎች ተጣሩ፤ በንጉሡም ቤት ውስጥ አወሩ። 12ንጉሡም በሌሊት ተነሥቶ ባሪያዎቹን “ሶርያውያን ያደረጉብንን እነግራችኋለሁ፤ እንደ ተራብን ያውቃሉ፤ ስለዚህ ‘ከከተማይቱ በወጡ ጊዜ በሕይወታቸው እንይዛቸዋለን፤ ወደ ከተማም እንገባለን፤’ ብለው በሜዳ ይሸሸጉ ዘንድ ከሰፈሩ ወጥተዋል፤” አላቸው። 13ከባሪያዎቹም አንዱ መልሶ “በከተማ ከቀሩት ፈረሶች አምስት ይውሰዱ፤ እነሆ፥ እንደ ቀሩት እንደ እስራኤል ወገን ሁሉ ናቸው፤ እነሆ፥ እንዳለቁ እንደ እስራኤል ወገን ሁሉ ናቸው፤ እንስደድም፤ እንይም፤” አለ። 14ሁለትም ሠረገሎች ከፈረሶች ጋር ወሰዱ፤ ንጉሡም “ሄዳችሁ እዩ፤” ብሎ ከሶርያውያን ሠራዊት በኋላ ላከ። 15በኋላቸው እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ሄዱ፤ እነሆም፥ ሶርያውያን ሲሸሹ የጣሉት ልብስና ዕቃ መንገዱን ሁሉ ሞልቶ ነበር። መልእክተኞችም ተመልሰው ለንጉሡ ነገሩት።
16ሕዝቡም ወጥቶ የሶርያውያንን ሰፈር በዘበዘ፤ እንደ እግዚአብሔርም ቃል እንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል፥ ሁለትም መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል ተሸመተ። 17ንጉሡም ያን እጁን ይደግፈው የነበረውን አለቃ በሩን ይጠብቅ ዘንድ አቆመው። ሕዝቡም በበሩ ረገጠው፤ ንጉሡም ወደ እርሱ በወረደ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ተናገረው ሞተ። 18የእግዚአብሔርም ሰው ለንጉሡ “ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር ሁለት መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል፥ አንድም መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል ይሸመታል፤” ብሎ እንደ ተናገረው ነገር እንዲሁ ሆነ። 19ያም አለቃ ለእግዚአብሔር ሰው መልሶ “እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ መስኮቶች ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን?” ብሎ ነበር፤ እርሱም “እነሆ፥ በዐይኖችህ ታየዋለህ፤ ከዚያም አትቀምስም፤” ብሎት ነበር። 20እንዲሁም ደረሰበት፤ ሕዝቡም በበሩ ረገጠውና ሞተ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ