የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 8

8
የሱነማዊቱ ሴት ርስት መመለስ
1ኤልሳዕም ልጅዋን ያስነሥላትን ሴት “አንቺ ከቤተ ሰብሽ ጋር ተነሥተሽ ሂጂ፤ በምታገኚውም ስፍራ ተቀመጪ፤ እግዚአብሔር ራብ ጠርቶአል፤ ሰባት ዓመትም በምድር ላይ ይመጣል፤” ብሎ ተናገራት። 2ሴቲቱም ተነሥታ እንደ እግዚአብሔር ሰው ቃል አደረገች፤ ከቤተሰብዋም ጋር ሄዳ በፍልስጥኤም አገር ሰባት ዓመት ተቀመጠች። 3ሰባቱም ዓመት በተፈጸመ ጊዜ ሴቲቱ ከፍልስጥኤም አገር ተመለሰች፤ ስለ ቤትዋና ስለ መሬትዋ ልትጮኽ ወደ ንጉሡ ወጣች። 4ንጉሡም ከእግዚአብሔር ሰው ሎሌ ከግያዝ ጋር “ኤልሳዕ ያደረገውን ተአምራት ሁሉ ንገረኝ፤” እያለ ይጫወት ነበር። 5እርሱም የሞተውን እንደ አስነሣ ለንጉሡ ሲናገር፥ እነሆ፥ ልጅዋን ያስነሣላት ሴት ስለ ቤትዋና ስለ መሬትዋ ወደ ንጉሥ ጮኸች፤ ግያዝም “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ! ሴቲቱ ይህች ናት፤ ኤልሳዕም ያስነሣው ልጅዋ ይህ ነው፤” አለ። 6ንጉሡም ሴቲቱን ጠየቀ፤ ነገረችውም። ንጉሡም “የነበረላትን ሁሉ፥ መሬትዋንም ከተወች ጀምራ እስከ ዛሬ ድረስ ያለውን የእርሻዋን ፍሬ ሁሉ መልስላት፤” ብሎ ስለ እርስዋ ጃንደረባውን አዘዘ።
ኤልሳዕና የሶርያው ንጉሥ ቤንሀዳድ
7ኤልሳዕም ወደ ደማስቆ መጣ፤ የሶርያም ንጉሥ ቤንሀዳድ ታምሞ ነበር፤ ወሬኞችም “የእግዚአብሔር ሰው ወደዚህ መጥቶአል፤” ብለው ነገሩት። 8ንጉሡም አዛሄልን “ገጸ በረከት በእጅህ ወስደህ የእግዚአብሔርን ሰው ልትገናኝ ሂድ፤ በእርሱም አፍ ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁን?’ ብለህ እግዚአብሔርን ጠይቅ፤” አለው። 9አዛሄልም ሊገናኘው ሄደ፤ ከእርሱም ጋር ከደማስቆ መልካሙን ነገር ሁሉ የአርባ ግመል ጭነት ገጸ በረከት ወሰደ፤ መጥቶም በፊቱ ቆመና “ልጅህ የሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ ‘ከዚህ በሽታ እድናለሁን?’ ሲል ወደ አንተ ልኮኛል፤” አለ። 10ኤልሳዕም “ሂድ፤ ‘መዳንስ ትድናለህ፤’ በለው፤ ነገር ግን እንዲሞት እግዚአብሔር አሳይቶኛል፤” አለው። 11እስኪያፍርም ድረስ ትኵር ብሎ ተመለከተው፤ የእግዚአብሔርም ሰው አነባ። 12አዛሄልም “ጌታዬ ለምን ያነባል?” አለ። እርሱም “በእስራኤል ልጆች ላይ የምታደርገውን ክፋት ስለማውቅ ነው፤ ምሽጎቻቸውን በእሳት ታቃጥላለህ፤ ጕልማሶቻቸውንም በሰይፍ ትገድላለህ፤ ሕፃናቶቻቸውንም ትፈጠፍጣለህ፤ የእርጉዞቻቸውንም ሆድ ትቀድዳለህ፤” አለው። 13አዛሄልም “ይህን ታላቅ ነገር አደርግ ዘንድ እኔ ውሻ ባሪያህ ምንድር ነኝ?” አለ። ኤልሳዕም “አንተ በሶርያ ላይ ንጉሥ እንድትሆን እግዚአብሔር አሳይቶኛል፤” አለው። 14ከኤልሳዕም ርቆ ወደ ጌታው መጣ፤ እርሱም “ኤልሳዕ ምን አለህ?” አለው። እርሱም “እንድትፈወስ ነገረኝ፤” አለው። 15በነጋውም የአልጋ ልብስ ወስዶ በውሃ ነከረው በፊቱም ላይ ሸፈነው፤ ሞተም። አዛሄልም በፋንታው ነገሠ።
ኢዮራም በይሁዳ እንደ ነገሠ
(2ዜ.መ. 21፥1-20)
16በእስራኤልም ንጉሥ በአክዓብ ልጅ በኢዮራም በአምስተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም ነገሠ። 17መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሠላሳ ሁለት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ስምንት ዓመት ነገሠ። 18የአክዓብንም ልጅ አግብቶ ነበርና የአክዓብ ቤት እንዳደረገ በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ። 19ነገር ግን ለእርሱና ለልጆቹ በዘመኑ ሁሉ መብራት ይሰጠው ዘንድ ተስፋ እንደ ሰጠ፥ ስለ ባሪያው ስለ ዳዊት እግዚአብሔር ይሁዳን ያጠፋ ዘንድ አልወደደም።
20በእርሱም ዘመን ኤዶምያስ ለይሁዳ እንዳይገብር ሸፈተ፤ በላያቸውም ንጉሥ አነገሡ። 21ኢዮራምም ከሠረገሎቹ ሁሉ ጋር ወደ ጸዒር አለፈ፤ በሌሊትም ተነሥቶ እርሱንና የሠረገሎቹን አለቆች ከብበው የነበሩትን የኤዶምያስን ሰዎች መታ፤ ሕዝቡ ግን ወደ ድንኳኑ ሸሸ። 22ኤዶምያስ ግን ለይሁዳ እንዳይገብር እስከ ዛሬ ድረስ ሸፈተ። በዚያም ዘመን ደግሞ ልብና ሸፈተ። 23የተረፈውም የኢዮራም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 24ኢዮራምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ፤ በፋንታውም ልጁ አካዝያስ ነገሠ።
አካዝያስ በይሁዳ እንደ ነገሠ
(2ዜ.መ. 22፥1-6)
25በእስራኤል ንጉሥ በአክዓብ ልጅ በኢዮራም በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ነገሠ። 26መንገሥ በጀመረ ጊዜ አካዝያስ የሃያ ሁለት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አንድ ዓመት ነገሠ። እናቱም ጎቶልያ የተባለች የእስራኤል ንጉሥ የዖምሪ ልጅ ነበረች። 27በአክዓብም ቤት መንገድ ሄደ፤ እንደ አክዓብም ቤት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ፤ ለአክዓብ ቤት አማች ነበረና። 28ከአክዓብም ልጅ ከኢዮራም ጋር የሶርያን ንጉሥ አዛሄልን በሬማት ዘገልዓድ ሊጋጠም ሄደ፤ ሶርያውያንም ኢዮራምን አቈሰሉት። 29ንጉሡም ኢዮራም ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጋር በተዋጋ ጊዜ ሶርያውያን በሬማት ያቈሰሉትን ቈስል ይታከም ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ተመለሰ። የአክዓብም ልጅ ኢዮራም ታምሞ ነበርና የይሁዳ ንጉሥ የኢዮራም ልጅ አካዝያስ ሊያየው ወደ ኢይዝራኤል ወረደ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ