ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 9
9
ኢዩ በእስራኤል ላይ እንደ ነገሠ
1ነቢዩም ኤልሳዕ ከነቢያት ልጆች አንዱን ጠርቶ እንዲህ አለው “ወገብህን ታጥቀህ ይህን የዘይት ማሰሮ በእጅህ ያዝ፤ ወደ ሬማት ዘገለዓድም ሂድ። 2በዚያም በደረስህ ጊዜ የናሜሲን ልጅ የኢዮሣፍጥን ልጅ ኢዩን ታገኘዋለህ፤ ገብተህም ከወንድሞቹ መካከል አስነሣው፤ ወደ ጓዳም አግባው። 3የዘይቱንም ማሰሮ ይዘህ በራሱ ላይ አፍስሰውና ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ፤” በለው፤’ በሩንም ከፍተህ ሽሽ፤ አትዘግይም።”
4እንዲሁም ጐልማሳው ነቢይ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሄደ። 5በገባም ጊዜ፥ እነሆ፥ የሠራዊት አለቆች ተቀምጠው ነበር፤ እርሱም “አለቃ ሆይ! ለአንተ መልእክት አለኝ፤” አለ። ኢዩም “ለማንኛችን ነው?” አለ። እርሱም “አለቃ ሆይ! ለአንተ ነው፤” አለ። 6ተነሥቶም ወደ ቤቱ ገባ፤ ዘይቱንም በራሱ ላይ አፍስሶ እንዲህ አለው “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ። 7የባሪያዎቼን የነቢያትን ደም፥ የእግዚአብሔርንም ባሪያዎች ሁሉ ደም ከኤልዛቤል እጅ እበቀል ዘንድ የጌታህን የአክዓብን ቤት ትመታለህ። 8የአክዓብም ቤት ሁሉ ይጠፋል፤ በእስራኤልም ዘንድ የታሰረውንና የተለቀቀውን ወንድ ሁሉ ከአክዓብ አጠፋለሁ። 9የአክዓብንም ቤት እንደ ናባጥ ልጅ እንደ ኢዮርብዓም ቤት፥ እንደ አኪያም ልጅ እንደ ባኦስ ቤት አደርገዋለሁ። 10ኤልዛቤልንም በኢይዝራኤል እርሻ ውሾች ይበሉአታል፤ የሚቀብራትም አታገኝም።’” በሩንም ከፍቶ ሸሸ።
11ኢዩም ወደ ጌታው አገልጋዮች ወጣ፤ እነርሱም “ደኅና ነውን? ይህ እብድ ለምን መጣብህ?” አሉት። እርሱም “ሰውዮውንና ንግግሩን ታውቃላችሁ፤” አላቸው። 12እነርሱም “ሐሰት ነው፤ ያለውን ንገረን፤” አሉት፤ እርሱም “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ፤’ ብሎ እንዲህ እንዲህ ነገረኝ፤” አላቸው። 13ሁሉም ፈጥነው ልባሳቸውን ወሰዱ፤ በሰገነቱ መሰላል እርከን ላይ ከእግሩ በታች አነጠፉት፤ ቀንደ መለከትም እየነፉ፥ “ኢዩ ነግሦአል!” አሉ።
የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራም እንደ ተገደለ
14እንዲሁም የናሜሲ ልጅ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዩ በኢዮራም ላይ ተማማለ። ኢዮራምና የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል የተነሣ ሬማት ዘገለዓድን ይጠብቁ ነበር። 15ንጉሡ ኢዮራም ግን ከሶርያ ንጉሥ ከአዛሄል ጋር በተዋጋ ጊዜ ሶርያውያን ያቈሰሉትን ቍስል ይታከም ዘንድ ወደ ኢይዝራኤል ተመልሶ ነበር። ኢዩም “ልባችሁስ ከእኔ ጋር ከሆነ በኢይዝራኤል እንዳያወራ ማንም ከከተማ ኮብልሎ አይውጣ፤” አለ። 16ኢዮራምም በዚያ ታምሞ ተኝቶ ነበርና ኢዩ በሠረገላው ላይ ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ። የይሁዳም ንጉሥ አካዝያስ ኢዮራምን ለማየት ወርዶ ነበር።
17በኢይዝራኤልም ግንብ ላይ የቆመው ሰላይ የኢዩ ጭፍራ ሲመጣ አይቶ “ጭፍራ አያለሁ፤” አለ። ኢዮራምም “የሚገናኘው ፈረሰኛ ላክ፤ እርሱም ‘ሰላም ነውን?’ ይበለው፤” አለ። 18ፈረሰኛውም ሊገናኘው ሄዶ “ንጉሡ እንዲህ ይላል ‘ሰላም ነውን?’” አለ። ኢዩም “አንተ ከሰላም ጋር ምን አለህ? ወደ ኋላዬ አልፈህ ተከተለኝ፤” አለ። ሰላዩም “መልእክተኛው ደረሰባቸው፤ ነገር ግን አልተመለሰም፤” ብሎ ነገረው። 19ሁለተኛም ፈረሰኛ ሰደደ፤ ወደ እነርሱም ደርሶ “ንጉሡ እንዲህ ይላል ‘ሰላም ነውን?’” አለ። ኢዩም “አንተ ከሰላም ጋር ምን አለህ? ወደ ኋላዬ አልፈህ ተከተለኝ፤” አለ። 20ሰላዩም “ደረሰባቸው፤ ነገር ግን አልተመለሰም፤ በችኮላ ይሄዳልና አካሄዱ እንደ ናሜሲ ልጅ እንደ ኢዩ አካሄድ ነው፤” ብሎ ነገረው።
21ኢዮራምም “ሠረገላ አዘጋጁ፤” አለ፤ ሠረገላውንም አዘጋጁለት። የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮራም የይሁዳም ንጉሥ አካዝያስ በሠረገሎቻቸው ተቀምጠው ወጡ፤ ኢዩንም ሊገናኙት ሄዱ፤ በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ እርሻ ውስጥ አገኙት። 22ኢዮራምም ኢዩን ባየ ጊዜ “ኢዩ ሆይ! ሰላም ነውን?” አለ። እርሱም “የእናትህ የኤልዛቤል ግልሙትናዋና መተትዋ ሲበዛ ምን ሰላም አለ?” ብሎ መለሰ። 23ኢዮራምም መልሶ ነዳና ሸሸ፤ አካዝያስንም “አካዝያስ ሆይ! ዓመፅ ነው፤” አለው። 24ኢዩም በእጁ ቀስቱን ለጠጠ፤ ኢዮራምንም በጫንቃው መካከል ወጋው፤ ፍላጻውም በልቡ አለፈ፤ ወደ ሠረገላውም ውስጥ ወደቀ። 25ኢዩም አለቃውን ቢድቃርን እንዲህ አለው “አንሥተህ በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ እርሻ ጣለው፤ አንተና እኔ ጎን ለጎን በፈረስ ተቀምጠን አባቱን አክዓብን በተከተልን ጊዜ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ይህን መከራ እንደ ተናገረበት አስብ፤ 26‘በእውነት የናቡቴንና የልጆቹን ደም ትናንትና አይቻለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ በዚህም እርሻ እመልስብሃለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር።’ ስለዚህ እግዚአብሔር እንደ ተናገረው ቃል ወስደህ በእርሻው ውስጥ ጣለው።”
የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ እንደ ተገደለ
27የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ ያንን ባየ ጊዜ በአትክልት ቤት መንገድ ሸሸ። ኢዩም “ይህን ደግሞ በሠረገላው ላይ ውጉት፤” እያለ ተከተለው፤ በይብለዓምም አቅራቢያ ባለችው በጉር ዐቀበት ላይ ወጉት። ወደ መጊዶም ሸሸ፤ በዚያም ሞተ። 28ባሪያዎቹም በሠረገላው ጭነው ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፤ በዳዊትም ከተማ በመቃብሩ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት።
29በአክዓብም ልጅ በኢዮራም በዐሥራ አንደኛው ዓመት አካዝያስ በይሁዳ ላይ ነገሠ።
የንግሥት ኤልዛቤል መገደል
30ኢዩም ወደ ኢይዝራኤል መጣ፤ ኤልዛቤልም በሰማች ጊዜ ዐይንዋን ተኳለች፤ ራስዋንም አስጌጠች፤ በመስኮትም ዘልቃ ትመለከት ነበር። 31ኢዩም በበሩ ሲገባ “ጌታውን የገደለ ዘምሪ ሆይ! ሰላም ነውን?” አለችው። 32ፊቱንም ወደ መስኮቱ አንሥቶ “ከእኔ ጋር ማን ነው?” አለ። ሁለት ሦስትም ጃንደረቦች ወደ እርሱ ተመለከቱ። 33እርሱም “ወደ ታች ወርውሩአት፤” አለ፤ ወረወሩአትም፤ ደምዋም በግንቡና በፈረሶቹ ላይ ተረጨ፤ ረገጡአትም። 34በገባም ጊዜ በላ ጠጣም፤ ከዚያም በኋላ “ይህችን የተረገመች እዩ፤ የንጉሥ ልጅ ናትና ቅበሩአት፤” አለ። 35ሊቀብሩአትም በሄዱ ጊዜ ከአናትዋና ከእግርዋ ከመዳፍም በቀር ምንም አላገኙም። 36ተመልሰውም ነገሩት፤ እርሱም “በባሪያው በቴስብያዊ ኤልያስ ‘በኢይዝራኤል እርሻ የኤልዛቤልን ሥጋ ውሾች ይበላሉ፤ 37የኤልዛቤልም ሬሳ በኢይዝራኤል እርሻ መሬት ላይ እንደ ፍግ ይሆናልና ማንም “ይህች ኤልዛቤል ናት፤” ይል ዘንድ አይችልም፤’ ብሎ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው፤” አለ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 9: አማ54
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ