በማግስቱም ማለዳ የኤልሳዕ አገልጋይ ከመኝታው ተነሥቶ፥ ከቤት ሲወጣ በፈረሶችና በሠረገሎች የታጀቡ የሶርያ ወታደሮች ከተማይቱን መክበባቸውን አየ፤ ወደ ኤልሳዕም ተመልሶ ድምፁን ከፍ በማድረግ “ጌታዬ ወዮ! ምን ማድረግ ይሻለናል?” ሲል ጠየቀው። ኤልሳዕም “አይዞህ አትፍራ፤ ከእነርሱ ጋር ከተሰለፈው ይልቅ ከእኛ ጋር የተሰለፈው ሠራዊት ይበልጣል” አለው። ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ “እግዚአብሔር ሆይ! ማየት እንዲችል ዐይኖቹን ክፈትለት!” ሲል ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የኤልሳዕ አገልጋይ ዐይኖቹ እንዲከፈቱለት ስላደረገ፥ በኰረብታው ጐን ብዙ የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተሰልፈው የሚጠብቁት መሆናቸውን ተመለከተ። ሶርያውያንም ወደ እርሱ በወረዱ ጊዜ ኤልሳዕ “እግዚአብሔር ሆይ! እነዚህ ሰዎች እንዲታወሩ አድርግ!” ብሎ ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የኤልሳዕን ጸሎት በመስማት፥ ዐይኖቻቸው እንዲታወሩ አደረገ። ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ ወደ እነርሱ ቀረብ ብሎ “መንገድ ተሳስታችኋል፤ የምትፈልጓት ከተማ ይህች አይደለችም፤ ይልቅስ ወደምትፈልጉት ሰው እኔ ልመራችሁ ስለምችል ተከተሉኝ” ብሎ ወደ ሰማርያ መራቸው። ወደ ከተማይቱም እንደ ገቡ ኤልሳዕ “እግዚአብሔር ሆይ! ማየት እንዲችሉ ዐይኖቻቸውን ግለጥላቸው!” ሲል ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ዐይኖቻቸውን በከፈተላቸው ጊዜ በሰማርያ ውስጥ መሆናቸውን ተረዱ። የእስራኤልም ንጉሥ ሶርያውያንን ባያቸው ጊዜ “ጌታዬ ሆይ! ልግደላቸውን? ልግደላቸውን?” ሲል ኤልሳዕን ጠየቀው። ኤልሳዕም “አይሆንም! እንኳን እነዚህን፥ በሰይፍህና በቀስትህ የማረክኻቸውን ወታደሮች መግደል አይገባህም፤ ይልቅስ የሚበሉትና የሚጠጡትን ምግብ አቅርብላቸውና ወደ ንጉሣቸው ተመልሰው እንዲሄዱ አድርግ” አለው። ስለዚህም የእስራኤል ንጉሥ ለእነርሱ ታላቅ ግብዣ አደረገላቸው፤ ከበሉና ከጠጡም በኋላ ወደ ሶርያ ንጉሥ መልሶ ላካቸው፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ሶርያውያን በእስራኤል ምድር ላይ ወረራ ማድረጋቸውን አቆሙ።
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 6 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 6:15-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች