ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 6
6
ሰጥሞ የነበረው መጥረቢያ በተአምር መውጣቱ
1በኤልሳዕ ኀላፊነት ሥር የነበሩት የነቢያት ጉባኤ አባላት፥ “የምንኖርበት ስፍራ ጠባብ ነው፤ 2ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ሄደን ዛፍ በመቊረጥ የምንኖርበት ቤት በዚያ እንድንሠራ ፍቀድልን!” አሉት።
ኤልሳዕም “እሺ መልካም ነው!” አላቸው።
3ከነቢያቱም አንዱ ኤልሳዕን አብሮአቸው እንዲሄድ ጠየቀው፤ ኤልሳዕም በጥያቄው ተስማማ፤ 4አብረውም ሄዱ፤ ወደ ዮርዳኖስም በደረሱ ጊዜ ዛፍ የመቊረጥ ተግባራቸውን ጀመሩ፤ 5ከእነርሱም አንዱ ዛፍ በመቊረጥ ላይ ሳለ በድንገት መጥረቢያው ከዛቢያው ላይ ወድቆ ውሃ ውስጥ ገባ፤ እርሱም ድምፁን ከፍ አድርጎ በመጮኽ “ጌታዬ ሆይ! እንግዲህ ምን አደርጋለሁ? መጥረቢያው የተውሶ ነው!” ሲል ለኤልሳዕ ነገረው።
6ኤልሳዕም “በየት በኩል ነው የወደቀው?” ሲል ጠየቀው።
ሰውየውም መጥረቢያው የወደቀበትን ስፍራ ባሳየው ጊዜ እርሱ አንድ እንጨት ቈርጦ ወደ ውሃው ውስጥ በመጣል መጥረቢያው እንዲንሳፈፍ አደረገው፤ 7ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ “አውጥተህ ውሰድ” አለው፤ ሰውየውም ጐንበስ ብሎ አነሣው።
የሶርያ የጦር ሠራዊት ድል መሆን
8እነሆ፥ የሶርያ ንጉሥ ከእስራኤል ጋር በጦርነት ላይ ነበር፤ እርሱም ከጦር አዛዥውቹ ጋር ተማክሮ የሚሰፍሩበትን ቦታ መረጠ፤ 9ኤልሳዕ ግን “ሶርያውያን ደፈጣ አድርገው ስለሚጠብቁህ ወደዚያ ስፍራ አትቅረብ” ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ላከ። 10ስለዚህም የእስራኤል ንጉሥ በዚያ የሚኖሩትን ወታደሮቹን ስላስጠነቀቃቸው ነቅተው ይጠባበቁ ነበር፤ ይህም ድርጊት ብዙ ጊዜ በተደጋጋሚ ተፈጸመ።
11“ከእኛ መካከል ከእስራኤል ንጉሥ ጋር ግኑኝነት ያለው ማን እንደ ሆነ አትነግሩኝምን?” ሲል ጠየቃቸው።
12ከእነርሱም አንዱ “ንጉሥ ሆይ፥ ከእኛ መካከል ይህን የሚያደርግ ማንም የለም፤ በመኝታ ክፍልህ እንኳ ሆነህ የምትናገረውን ሁሉ ሳይቀር ለእስራኤል ንጉሥ ምሥጢሩን የሚገልጥለት ኤልሳዕ የተባለው ነቢይ ነው” ሲል መለሰለት።
13የሶርያም ንጉሥ “እርሱ የሚገኝበትን ስፍራ ፈልጉ፤ እኔም ልኬ እማርከዋለሁ” አላቸው።
በዚህም ጊዜ ኤልሳዕ በዶታን የሚኖር መሆኑ ተነገረው፤ 14ንጉሡ በፈረሶችና በሠረገሎች የተጠናከረ ሠራዊት ወደዚያ ላከ፤ እነርሱም በሌሊት ደርሰው ከተማይቱን ከበቡ። 15በማግስቱም ማለዳ የኤልሳዕ አገልጋይ ከመኝታው ተነሥቶ፥ ከቤት ሲወጣ በፈረሶችና በሠረገሎች የታጀቡ የሶርያ ወታደሮች ከተማይቱን መክበባቸውን አየ፤ ወደ ኤልሳዕም ተመልሶ ድምፁን ከፍ በማድረግ “ጌታዬ ወዮ! ምን ማድረግ ይሻለናል?” ሲል ጠየቀው።
16ኤልሳዕም “አይዞህ አትፍራ፤ ከእነርሱ ጋር ከተሰለፈው ይልቅ ከእኛ ጋር የተሰለፈው ሠራዊት ይበልጣል” አለው። 17ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ “እግዚአብሔር ሆይ! ማየት እንዲችል ዐይኖቹን ክፈትለት!” ሲል ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የኤልሳዕ አገልጋይ ዐይኖቹ እንዲከፈቱለት ስላደረገ፥ በኰረብታው ጐን ብዙ የእሳት ፈረሶችና ሠረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተሰልፈው የሚጠብቁት መሆናቸውን ተመለከተ።
18ሶርያውያንም ወደ እርሱ በወረዱ ጊዜ ኤልሳዕ “እግዚአብሔር ሆይ! እነዚህ ሰዎች እንዲታወሩ አድርግ!” ብሎ ጸለየ፤ እግዚአብሔርም የኤልሳዕን ጸሎት በመስማት፥ ዐይኖቻቸው እንዲታወሩ አደረገ። 19ከዚህም በኋላ ኤልሳዕ ወደ እነርሱ ቀረብ ብሎ “መንገድ ተሳስታችኋል፤ የምትፈልጓት ከተማ ይህች አይደለችም፤ ይልቅስ ወደምትፈልጉት ሰው እኔ ልመራችሁ ስለምችል ተከተሉኝ” ብሎ ወደ ሰማርያ መራቸው።
20ወደ ከተማይቱም እንደ ገቡ ኤልሳዕ “እግዚአብሔር ሆይ! ማየት እንዲችሉ ዐይኖቻቸውን ግለጥላቸው!” ሲል ጸለየ፤ እግዚአብሔርም ዐይኖቻቸውን በከፈተላቸው ጊዜ በሰማርያ ውስጥ መሆናቸውን ተረዱ።
21የእስራኤልም ንጉሥ ሶርያውያንን ባያቸው ጊዜ “ጌታዬ ሆይ! ልግደላቸውን? ልግደላቸውን?” ሲል ኤልሳዕን ጠየቀው።
22ኤልሳዕም “አይሆንም! እንኳን እነዚህን፥ በሰይፍህና በቀስትህ የማረክኻቸውን ወታደሮች መግደል አይገባህም፤ ይልቅስ የሚበሉትና የሚጠጡትን ምግብ አቅርብላቸውና ወደ ንጉሣቸው ተመልሰው እንዲሄዱ አድርግ” አለው። 23ስለዚህም የእስራኤል ንጉሥ ለእነርሱ ታላቅ ግብዣ አደረገላቸው፤ ከበሉና ከጠጡም በኋላ ወደ ሶርያ ንጉሥ መልሶ ላካቸው፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ሶርያውያን በእስራኤል ምድር ላይ ወረራ ማድረጋቸውን አቆሙ።
የሰማርያ መከበብ
24ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ መላ ሠራዊቱን በእስራኤል ላይ በማዝመት፥ የሰማርያን ከተማ ከበበ፤ 25ከበባውም የምግብን እጥረትና ብርቱ ራብ ከማስከተሉ የተነሣ፥ የአንድ አህያ ራስ ዋጋ እስከ ሰማኒያ ጥሬ ብር፥ ሁለት መቶ ግራም የሚያኽል የርግብ ኩስ ዋጋ ደግሞ አምስት ጥሬ ብር ማውጣት ጀመረ።
26አንድ ቀን የእስራኤል ንጉሥ በከተማይቱ የቅጽር ግንብ ላይ በሚመላለስበት ጊዜ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “ንጉሥ ሆይ፥ እባክህ እርዳኝ!” ስትል ጮኸች።
27ንጉሡም “እግዚአብሔር ሊረዳሽ ካልፈቀደ እኔ ምን ዐይነት ርዳታ ልሰጥሽ እችላለሁ? ከአውድማው ወይስ ከወይን መጭመቂያው? ምን ያለኝ ይመስልሻል? 28ለመሆኑ ችግርሽ ምንድን ነው?” ሲል ጠየቃት።
እርስዋም እንዲህ ስትል መለሰችለት፤ “ባለፈው ቀን ይህች ሴት ‘ዛሬ የአንቺን ልጅ እንብላ፤ በማግስቱ ደግሞ የእኔን ልጅ እንበላለን’ ስትል ሐሳብ አቀረበች። 29ስለዚህም የእኔን ልጅ ቀቅለን በላን፤ በማግስቱም ‘ልጅሽን አምጪና እንብላ’ ብዬ ጠየቅኋት፤ እርስዋ ግን ደበቀችው።” #ሰቆ.ኤ. 4፥10።
30ንጉሡም ይህን በሰማ ጊዜ በሐዘን ልብሱን ቀደደ፤ በግንቡ ላይ በመሆኑ በአቅራቢያው የነበረው ሕዝብ ንጉሡ ከልብሱ በውስጥ በኩል ማቅ ለብሶ እንደ ነበር አዩ። 31ንጉሡም ድምፁን ከፍ በማድረግ “የዛሬይቱ ጀንበር ከመጥለቅዋ በፊት የሳፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ራስ ሳይቈረጥ ቢያድር እግዚአብሔር እኔን በሞት ይቅጣኝ!” ሲል ተናገረ። 32ወዲያውኑም ኤልሳዕን ይዞ የሚመጣ መልእክተኛ ላከ።
በዚህም ጊዜ ኤልሳዕ ሊጐበኙት ከመጡ ጥቂት ሽማግሌዎች ጋር በቤት ውስጥ ነበር፤ የንጉሡ መልእክተኛ ከመድረሱም በፊት ኤልሳዕ ሽማግሌዎቹን “ያ ነፍሰ ገዳይ እኔን ለማስገደል አንድ ሰው ልኮአል! እነሆ፥ እርሱ እዚህ በሚደርስበት ጊዜ በሩን ዝጉ፤ ወደ ውስጥም እንዲገባ አትፍቀዱለት፤ ንጉሡም እርሱን ተከትሎ መጥቶ በኋላው ይገኛል” አላቸው። 33ገና ይህን ተናግሮ ሳይጨርስ ንጉሡ ድንገት ከተፍ ብሎ “ይህን መከራ በእኛ ላይ ያመጣብን እግዚአብሔር ነው፤ ታዲያ እርሱ አንድ ነገር ያደርግ ዘንድ ከዚህ በላይ ምን ልጠብቅ?” አለ።
Currently Selected:
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 6: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997