የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 7

7
1ኤልሳዕም “እግዚአብሔር የሚለውን ስማ! ነገ ይህን ጊዜ በሰማርያ ሦስት ኪሎ ምርጥ ስንዴ ወይም ስድስት ኪሎ ገብስ በአንድ ጥሬ ብር ይሸመታል” ሲል መለሰለት።
2በዚህ ጊዜ የንጉሡ የቅርብ ባለሟል የሆነ አገልጋዩ ኤልሳዕን፥ “እግዚአብሔር ራሱ የሰማይ መስኮቶችን ከፍቶ እህልን እንደ ዝናብ ቢያዘንብ እንኳ ይህ ሊሆን ከቶ አይችልም!” ሲል በመጠራጠር ተናገረ።
ኤልሳዕም “ያን እህል በዐይንህ ታያለህ፤ ነገር ግን ከእርሱ ምንም ነገር አትቀምስም!” አለው።
የሶርያ ሠራዊት መሸሽ
3ሰውነታቸው የቆዳ በሽታ የያዛቸው አራት ሰዎች ከሰማርያ ቅጽር በር ውጪ ነበሩ፤ እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “እስክንሞት ድረስ ስለምን በዚህ እንቈያለን? 4ወደ ከተማይቱ መግባት ምንም ጥቅም የለውም፤ እዚያ ከገባን በራብ እንሞታለን፤ እዚህም ብንቀር ከመሞት አንድንም፤ ስለዚህ ተነሥተን ወደ ሶርያውያን ሰፈር እንሂድ፤ እነርሱም ቢሆኑ ከመግደል የከፋ ሌላ ምንም ነገር ሊያደርጉብን አይችሉም፤ ምናልባትም ሕይወታችንን ያተርፉ ይሆናል።” 5ከዚህም በኋላ ቀኑ ሊመሽ ሲል ወደ ሶርያውያን ሰፈር ሄዱ፤ ነገር ግን እዚያ ሲደርሱ ማንም ሰው አልነበረም፤ 6ይህም የሆነበት ምክንያት እግዚአብሔር ሶርያውያንን በፈረሶችና በሠረገሎች የታጀበ የብዙ ሠራዊት ግሥጋሤ የሚመስል ድምፅ አሰምቶአቸው ስለ ነበር ነው፤ ይኸውም ሶርያውያን እንዳሰቡት የእስራኤል ንጉሥ የሒታውያንና የግብጽ ነገሥታትን ከነሠራዊቶቻቸው ቀጥሮ አደጋ ሊጥልባቸው የመጣ መስሎአቸው ነበር። 7ስለዚህም በዚያን ቀን ምሽት ሶርያውያን ድንኳኖቻቸውን፥ ፈረሶቻቸውንና አህዮቻቸውን በጠቅላላም ሰፈራቸውን ሁሉ እንዳለ ትተው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሸሽተው ሄደዋል።
8አራቱ ሰዎች ወደ ሶርያውያን ሰፈር ዳርቻ በደረሱ ጊዜ ወደ አንድ ድንኳን ውስጥ ገቡ፤ በዚያም ያገኙትን ነገር ሁሉ በልተውና ጠጥተው ያገኙትን ብር፥ ወርቅና ልብስ ይዘው ሄደው ደበቁ፤ እንደገናም ተመልሰው ወደ ሌላ ድንኳን በመግባት እንደዚያው አደረጉ፤ 9ከዚህም በኋላ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፥ “መልካም አላደረግንም! እነሆ፥ ዛሬ ታላቅ የምሥራች አግኝተናል፤ ይህንንም መልካም ዜና ደብቀን ልናስቀር አይገባንም! ይህን የምሥራች ሳንነግር እስኪነጋ ብንቈይ በእርግጥ ቅጣት ይደርስብናል፤ ስለዚህም አሁኑኑ ሄደን ለንጉሡ የጦር መኰንኖች እንንገር!” 10ከዚያም በኋላ ከሶርያውያን ሰፈር በመነሣት ወደ ሰማርያ ተመልሰው ሄዱ፤ እዚያም እንደ ደረሱ የከተማይቱን ቅጽር በር ዘበኞች ጠርተው “ወደ ሶርያውያን ሰፈር ሄደን ነበር፤ ነገር ግን ምንም ያየነው ሰው ወይም የሰማነው ድምፅ እንኳ የለም፤ ፈረሶችና አህዮች እንደ ታሰሩ ናቸው፤ ድንኳኖቹም ሶርያውያን ትተዋቸው ስለ ሄዱ ባዶአቸውን ናቸው” ሲሉ ነገሩአቸው።
11ዘብ ጠባቂዎቹም ወሬውን ስለ ነዙት እስከ ቤተ መንግሥት ድረስ ተሰማ። 12ጊዜውም ገና ሌሊት ነበር፤ ንጉሡ ግን ከመኝታው ተነሥቶ ባለሟሎቹ የሆኑትን ባለሥልጣኖች እንዲህ አላቸው፤ “የሶርያውያንን ዕቅድ ልንገራችሁ! እነርሱ በዚህ ስላለው ራብ ያውቃሉ፤ ስለዚህ ሰፈራቸውን ለቀው በገጠር ለመሸሸግ ሄደዋል፤ እኛም ምግብ ፍለጋ ብንወጣ ከነሕይወታችን ማርከው ከተማችንን ይወስዳሉ።”
13ከባለሟሎቹም አንዱ “በዚህች ከተማ ውስጥ የተረፈው ሕዝብ ከዚህ በፊት እንደ ሞቱት ሰዎች ሁሉ ከሞት የሚያመልጥ አይደለም፤ ስለዚህ የሆነውን ነገር ማወቅ እንድንችል ጥቂት ሰዎችን መርጠን ከሞት ከተረፉት አምስት ፈረሶች ጋር እንላክ” ሲል ሐሳብ አቀረበ። 14እነርሱም ጥቂት ሰዎችን መረጡ፤ ንጉሡም እነዚያን ሰዎች በሁለት ሠረገሎች እንዲቀመጡ አድርጎ በሶርያውያን ሠራዊት ላይ የደረሰውን ሁኔታ መርምረው እንዲመለሱ መመሪያ በመስጠት ላካቸው። 15ሰዎቹም ከዚያ ተነሥተው እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ ድረስ ዘልቀው ሄዱ፤ በየመንገዱም ሶርያውያን ሲሸሹ ጥለውት የሄዱትን ልብስና መሣሪያ ሁሉ አዩ፤ ከዚያም በኋላ ተመልሰው መጥተው ይህን ሁሉ ለንጉሡ ነገሩ። 16ሕዝቡም በፍጥነት እየተራወጠ ወጥቶ የሶርያን ሰፈር ዘረፈ፤ እግዚአብሔር አስቀድሞ በተናገረውም መሠረት ሦስት ኪሎ ምርጥ ስንዴ ወይም ስድስት ኪሎ ገብስ በአንድ ጥሬ ብር ተሸመተ።
17በዚህም ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ የከተማይቱ ቅጽር በር የቅርብ ባለሟሉ በሆነው አገልጋዩ ኀላፊነት ሥር እንዲጠበቅ አድርጎ ነበር፤ ነገር ግን ያንን አገልጋይ ሕዝቡ ስለ ረጋገጠው በዚያ ሞተ፤ ይህም የሆነው ንጉሡ ኤልሳዕን ለማነጋገር በሄደ ጊዜ ኤልሳዕ በዚያ አገልጋይ ላይ የተናገረበት የትንቢት ቃል ስለ ተፈጸመ ነው።
18በዚያን ጊዜ ኤልሳዕ ለንጉሡ “በነገው ዕለት በሰማርያ ከተማ ሦስት ኪሎ ምርጥ ስንዴ ወይም ስድስት ኪሎ ገብስ በአንድ ጥሬ ብር ይሸመታል” ብሎ ነግሮት ነበር፤ 19ለዚህም ቃል ያ አገልጋዩ የሰጠው መልስ “እግዚአብሔር ራሱ የሰማይ መስኮቶችን ከፍቶ እህልን እንደ ዝናብ ቢያዘንብ እንኳ ይህ ሊሆን ከቶ አይችልም!” የሚል ነበር። ኤልሳዕም “ያን እህል በዐይንህ ታያለህ፤ ነገር ግን ከእርሱ ምንም ነገር አትቀምስም” ብሎት ነበር። 20እንግዲህ ያ አገልጋይ በሰማርያ ከተማ ቅጽር በር ላይ ሕዝብ ረጋግጦት ለመሞት የበቃው ይህ ትንቢት ስለ ተፈጸመበት ነበር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ